ትራምፕ ማዕቀብ የተጣለባቸው ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከቬንዙዌላ እንዳይወጡ እና እንዳይገቡ ትዕዛዝ አስተላለፉ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ቬንዙዌላ የሚገቡም ሆኑ የሚወጡ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሙሉ እገዳ እንዲጣልባቸው ትዕዛዝ አስተላለፉ።

ፕሬዚዳንቱ በትሩዝ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ መንግሥት የውጭ አሸባሪ ድርጅት ተብሎ መፈረጁን እና የአሜሪካን ንብረቶች በመስረቅ እንዲሁም በ"ሽብርተኝነት፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና የሰዎች ዝውውር" መወንጀሉን ዘርዝረዋል።

"ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቬንዙዌላ የሚገቡና የሚወጡ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ሙሉ በሙሉ እንዲታገዱ አዝዣለሁ" ብለዋል።

ይህ የፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ የመጣው አሜሪካ በቬንዙዌላ የባሕር ዳርቻ ላይ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ከያዘች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

የቬንዙዌላ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የትራምፕን "የተንሻንፈፈ ማስፈራሪያ" ውድቅ እንዳደረገ ገልጿል።

ትራምፕ በዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ ቬንዙዌላ "በደቡብ አሜሪካ ታሪክ ውስጥ እስካሁን ከታዩት ሁሉ ትላልቅ በሆኑ የጦር መርከቦች ሙሉ በሙሉ ተከብባለች" ብለዋል።

አክለውም ይህ ወታደራዊ ከበባ "ይበልጥ እየጨመረ የሚሄድ" መሆኑን ገልጸው "ከዚህ በፊት ካዩት ጋር የሚወዳደር አይደለም" በማለት ዝተዋል።

ትራምፕ የማዱሮን መንግሥት የተሰረቀ የነዳጅ ዘይትን በመጠቀም "ለራሳቸው የገንዘብ ድጋፍ" ያደርጋሉ ሲሉ ከስሰውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክለውም "የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ሽብርተኝነትን፣ የሰዎች ዝውውርን፣ ግድያን እና ጠለፋን" እየተጠቀመ ነው ሲሉም ወንጅለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ቬንዙዌላን በተደጋጋሚ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ሲከስ የቆየ ሲሆን ከመስከረም ወር ጀምሮ የአሜሪካ ጦር ፌንታኒልን እና ሌሎች ሕገወጥ አደንዛዥ ዕጾችን ወደ አሜሪካ እያጓጓዙ ነበር ሲል በጠረጠራቸው ጀልባዎች ላይ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 90 ሰዎችን ገድሏል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ አሜሪካ የጦር መርከቦቿን ወደ አካባቢው አዛውራለች።

በዓለም ላይ ትላልቅ የነዳጅ ክምችት ካላቸው አገራት ውስጥ አንዷ የሆነችው ቬንዙዌላ በበኩሏ ዋሽንግተን ሀብቷን ለመስረቅ እየሞከረች መሆኑን በመጥቀስ ትከስሳለች።

አሜሪካ በትራምፕም ሆነ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዘመን የማዱሮን መንግሥት ለዓመታት ስትቃወም እና ጥብቅ ማዕቀቦችን በመጣል ከሥልጣን እንዲወርዱ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የቬንዙዌላ ነዳጅ ያጓጉዙ የነበሩ ስድስት ተጨማሪ መርከቦች ላይ አዲስ ማዕቀብ ጥላለች።

በአንዳንድ የፕሬዚዳንት ማዱሮ ዘመዶች እና አሜሪካ ሕገ ወጥ አገዛዝ ብላ ከጠራችው መንግሥት ጋር የንግድ ትስስር ያላቸው ድርጅቶች ላይም ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

ከአንድ ቀን በፊት አሜሪካ በቬንዙዌላ የባሕር ዳርቻ ላይ አንድ የነዳጅ ማጓጓዣ መርከብ መያዟን አስታውቃለች።

ዋይት ሐውስ በቁጥጥር ሥር የዋለው ስኪፐር የተባለው መርከብ "ሕገወጥ የነዳጅ ማጓጓዣ" ነበር ያለ ሲሆን ወደ አሜሪካ ወደብ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

የቬንዙዌላ መንግሥት መርከቧ በቁጥጥር ሥር መዋሏን ያወገዘ ሲሆን፣ ማዱሮ በበኩላቸው አሜሪካ "የመርከቧን ሠራተኞች አግታለች" መርከቧን "ሰርቃለች" ሲሉ ከስሰዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በካሪቢያን የባሕር ዳርቻ የባሕር ኃይሏን በማስፈር በአካባቢው ያላትን ወታደራዊ ኃይል አጠናክራለች።

ይህም በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ያካተተ ሲሆን በዓለም ላይ ትልቁ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ የሆነው ዩኤስኤስ ጄራልድ ፎርድ ከቬንዙዌላ በጣም በቅርብ ርቀት በሚገኝ ቦታ ላይ መልህቁን ጥሏል።

የቴክሳስ ተወካይ የሆኑት የኮንግረስ አባሉ ጆአኩዊን ካስትሮ ትራምፕ ያደረጉት "የባሕር ኃይል እገዳ ያለምንም ጥርጥር የጦርነት ድርጊት ነው" ብለዋል።

አክለውም የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ሐሙስ ዕለት "ፕሬዝዳንቱ ከቬንዙዌላ ጋር የሚደረጉ ግጭቶችን እንዲያቆሙ የሚጠይቅ ውሳኔ" ላይ ድምጽ እንደሚሰጡ ተናክረዋል።