አሜሪካ የቬንዝዌላን ነዳጅ በሚያመላልሱ ስድስት መርከቦች ላይ አዲስ ማዕቀቦች ጣለች

የፎቶው ባለመብት, US Department of Justice
አሜሪካ የቬንዝዌላን ነዳጅ ያመላልሳሉ የተባሉ ስድስት መርከቦች ላይ አዲስ ማዕቀቦች ጣለች። በቬንዝዌላ የባሕር ዳርቻ የነዳጅ ታንከርም በቁጥጥር ሥር አውላለች።
አሜሪካ 'ሕገ ወጥ' ያለችው የፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ አስተዳደር ላይ በማነጣጠር የፕሬዝዳንቱ ዘመዶች እና የንግድ አጋሮች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት እንዳሉት የተያዘው መርከብ "በሕገ ወጥ መንገድ ነዳጅ የሚያመላልስ" ነው።
'ዘ ስኪፐር' የተባለው መርከብ ነዳጅ ወደ አሜሪካ ወደብ እንደሚያመላልስ ጠቅሰዋል።
የመርከቡ መያዝ እና አዲስ ማዕቀቦች መጣላቸው በአሜሪካ እና በቬንዝዌላ መካከል ያለውን ውጥረት አባብሷል።
አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ያመላልሳሉ ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ በተከታታይ ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች። ግዙፍ የጦር መርከቧንም በካሪቢያን ባሕር አሰማርታለች።
ቬንዝዌላ ወደ አሜሪካ ለሚገባው አደንዛዥ ዕፅ ተጠያቂ ናት በሚል አሜሪካ ትከስሳለች።
ቬንዝዌላ በዓለም ትልቅ የሆነ የነዳጅ ክምችት ያላት አገር ናት። አሜሪካ የነዳጅ ሃብቷን ለመመዝበር እንደምትፈልግ ወንጅላለች።
ፕሬዝዳንት ማዱሮ ቬንዝዌላ "የነዳጅ ቅኝ ግዛት" አትሆንም ብለዋል።
የዋይት ሀውስ ፕረስ ሴክሬተሪ በበኩላቸው አሜሪካ "የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመግታት" ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
አሜሪካ ተጨማሪ መርከቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ዕቅድ እንዳላት ባይናገሩም "ማዕቀብ የተጣለባቸው መርከቦች በጥቁር ገበያ የሚቸበቸብ ነዳጅ ይዘው እንዲዘዋወሩ አንፈቅድም። ይሄ ነዳጅ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ይደግፋል" ብለዋል።
አሜሪካ ተገቢውን ሕጋዊ ሒደት አልፋ በቁጥጥር ሥር ያዋለችው መርከብ ላይ የተጫነውን ነዳጅ እንደምትወስድ ተናግረዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከማዱሮ ጋር በስልክ በመነጋገራቸው "ትራምፕ አልተጨነቁም" ሲሉም አክለዋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ጸሐፊ ስኮት ባሴት እንዳሉት የማዱሮ ባለቤት፣ የወንድም ልጆች እና የንግድ አጋሮች ላይ ማዕቀብ ተጥሏል።
ማዕቀብ የተጣለው የፕሬዝዳንቱን "አምባገነን እና ጨቋኝ ቁጥጥር" ለመናድ ነው ብለዋል።
በኤክስ ባሰፈሩት ጽሑፍ የትራምፕ አስተዳደር የቬንዝዌላን መንግሥት እና አጋሮቹን "በወንጀል ተጠያቂ በማድረግ ይቀጥላል" በማለት አክለዋል።
ዋይት ሀውስ በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮች በሌሊት የቬንዝዌላን መርከብ ሲይዙ ይታያል።
የቬንዝዌላው ፕሬዝዳንት "በካሪቢያን ላይ አዲስ የወንጀል እና የባሕር ላይ ምዝበራ ዘመቻ ከፍተዋል" ብለዋል።
በመርከቡ ላይ የነበሩ ሠራተኞች "እንደታገቱ" ገልጸው መርከቡም "ተሰርቋል" ሲሉ አክለዋል።















