"ከትራምፕ ወረራ ይልቅ ምግብ መግዛት አለመቻላችን ያሳስበናል"

የኒኮላስ ማዱሮ አስተዳደር ከአሜሪካ ስጋት ተደቅኖበታል። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቬንዝዌላ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በተደጋጋሚ ዝተዋል።
ቬንዝዌላውያን ግን ከትራምፕ ወረራ በበለጠ የምግብ እጥረት ያሰጋቸዋል።
ኩዊንታ ክራስፖ ዋነኛው የአገሪቱ የገበያ ማዕከል ነው። ሸማቾች የሚወያዩት ስለ ትራምፕ ወረራ አይደለም። የኑሮ ውድነት ፈትኗቸዋል። ምግብ መግዛት ተቸግረዋል።
አሌሀንድሮ ኦርላኖ "ወረራ አይኖርም፤ ይልቁንስ የዶላር ዋጋ መናር አሳስቦናል" ይላል።
ባለፉት ሳምንታት ትራምፕ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ቬንዝዌላ አስጠግተዋል። በዓለም ትልቁን የጦር መርከብ ካሪቢያን ባሕር ላይ አሠማርተዋል።
ከሰሞኑ ቢያንስ አራት ግዙፍ አየር መንገዶች ወደ ቬንዝዌላ ሊደረጉ የነበሩ በረራዎች ሰርዘዋል።
የአሜሪካ አቪየሽን ባለሥልጣን "በቬንዝዌላ አቅራቢያ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አለ" ሲል አስጠንቅቋል።
አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ያዘዋውራሉ ያለቻቸው ጀልባዎች ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ከ80 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
በካሪቢያን እና በምሥራቅ ፓስፊክ አሜሪካ የምትሰነዝረውን ጥቃት ቀጥላለች። አሜሪካ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመግታት እርምጃውን እንደምትወስድ ብትገልጽም፤ ማዱሮ የጥቃቶቹ ዓላማ እሳቸውን ከሥልጣን ማውረድ እንደሆነ ይናገራሉ።
አሌሀንድሮ ውጥረቱ እምብዛም አያሳስበኝም ይላል። ለአምስት ዓመታት በኩዊንታ ክራስፖ አትክልት ነግዷል።
"አያችሁ እንዴት ኦና እንደሆነ?" ሲል የሸማቾች ቁጥር መቀነሱን ይገልጻል።

የምግብ ዋጋ መናር አገሬው ገበያ እንዳይወጣ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። የቬንዝዌላ መገበያያ ቦላቪር 80% ዋጋውን ማጣቱን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) መረጃ ይጠቁማል።
የአንድ ኪሎ ዶሮ አነስተኛ ከሚባለው ደመወዝ በአራት እጥፍ ይበልጣል። የመንግሥት ሠራተኞች የተለያየ ድጎማ ቢሰጣቸውም የተለወጠ ነገር የለም።
የ74 ዓመቷ ኮንስዌሎ አሜሪካ እና ቬንዝዌላ ወደ ጦርነት ያመራሉ ብለው አያምኑም።
"የሚሆነው ነገር ይሆናል፤ መለወጥ አይቻልም። የእውነት ነው ወይስ የውሸት ብሎ ማሰብ ራሱ ያሳምማል። ከመሸበር ይልቅ መረጋጋት ይሻለኛል። መጨነቅ ለጤናም አይበጅም" ይላሉ።
ጦርነት ይነሳል ብለው ቢሰጉ እንኳን ምግብ ገዝተው ለማከማቸት የሚበቃ ገንዘብ እንደሌላቸው ይናገራሉ።
አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እንደሚሉት፤ የዋጋ ንረት 20% ጨምሯል።
በአይኤምኤፍ ግምገማ መሠረት የሸቀጦች ዋጋ የ548% ጭማሬ አሳይቷል። በቀጣዩ የአውሮፓውያኑ ዓመት ከዚህም በላይ እንደሚሆን ይገመታል።

አንዳንዶች የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የመንግሥት ለውጥ ያመጣል ብለው ስለሚያምኑ አወንታዊ ጎኑ ያመዝንባቸዋል።
አንድ ነጋዴ "ፈርተናል፤ ዝም ብለናል፤ ትንፍሽ ብንል ያስሩናል። ድሮ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እጽፍ ነበር። አሁን ግን ማን እንደሚያሳስረኝ ስለማላውቅ ዝምታን መርጫለሁ" ብለዋል።
አንድ ሌላ ቬንዝዌላዊት ደግሞ "ተስፋ አለን፤ ስለምንፈራ ግን አንናገርም። ማንም ሰው ከቤቱ ውጭ በአደባባይ አያወራም። በተወሰነ ደረጃ ግን ደስተኛ ነን" ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
የማዱሮን መንግሥት በይፋ መተቸት የተለመደ አይደለም።
እአአ በ2024 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ አገር አቀፍ ተቃውሞ ተቀስቅሶ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለምርጫው ዕውቅና ነፍጓል።
አሜሪካ እንዲሁም የቬንዝዌላ ተቃዋሚዎችም ምርጫውን ያሸነፉት ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ ናቸው ብለው ያምናሉ።
በተቃውሞው ምክንያት ከ2,000 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን መንግሥት አስታውቋል።884 ሰዎች ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ አሁንም እስር ላይ ናቸው።
የ40 ዓመቷ ባርባራ ማዱሮ "ሁላችንም ለውጥ እስከሚመጣ እንጠብቃለን። ለዓመታት ተሰቃይተናል" ትላለች።
ኬክ ጋጋሪዋ ባርባራ እንደምትናገረው፤ ቬንዝዌላውያን በአደባባይ ለመናገር ቢፈሩም ለውጥ ይፈልጋሉ።
የ53 ዓመቷ የላብራቶሪ ሠራተኛ ኤስተር ጉዋዝራ "ምን እየተፈጠ እንደሆነ ስላልገባኝ ጨንቆኛል። [አሜሪካ] ብትወረንም ችግር የለውም ብለው ብዙዎች ያስባሉ። ነገር ግን በርካታ ንጹኃን ሊገደሉ ይችላሉ" ትላለች።
ሀቪየር ጃራሚሉ 57 ዓመቱ ነው። ለመጪው የፈንጆች ገና ጌጣጌጥ ይሸጣል።
አሜሪካ ወደ ካሪቢያን ያስጠጋችው የጦር መርከብ (USS Gerald R Ford) ያሳስበዋል።
"ጥቃት ይፈጽሙብናል ብዬ አላስብም። መግባት ከፈለጉ ቀጥታ መግባት ይችላሉ" ይላል።
ትራምፕ ከማዱሮ ጋር ለዲፕሎማቲክ ውይይት ዝግጁ ነኝ ብለዋል። ሆኖም ግን ወታደራዊ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
ሀቪየር በበኩሉ "እኛን የበለጠ የሚያሰጋን የምግብ ጉዳይ ነው። ቬንዝዌላ ችግር ውስጥ ገብታለች። የዋጋ ንረት በቁም እየገደለን ነው" ይላል።















