ትራምፕ አሜሪካ ከቬንዝዌላ ጋር ጦርነት ውስጥ የምትገባ አይመስለኝም አሉ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ እና ቬንዝዌላ ጦርነት ውስጥ የሚገቡ አይመስለኝም አሉ።

ትራምፕ "ጦርነት መነሳቱን እጠራጠራለሁ፤ የሚነሳ አይመስለኝም። ግን በጣም እየጎዱን ነው" ሲሉ ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ጦርነት የሚነሳ አይመስለኝም ቢሉም የቬንዝዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በሥልጣን የሚቆዩት 'ለአጭር ጊዜ' እንደሆነ ገልጸዋል።

አሜሪካ በካሪቢያን አቅራቢያ አደንዛዥ ዕፅ ያዘዋውራሉ ያለቻቸው ጀልባዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች።

ወደ አሜሪካ የሚገባው አደንዛዥ ዕፅ እንዲገደብ እርምጃ መውሰድ ግዴታቸው መሆኑን ትራምፕ ገልጸዋል።

አሜሪካ ጥቃት እየፈጸመች ያለቸው የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመግታት ሳይሆን የማዱሮን መንግሥት ለማውረድ ነው በሚል በርካቶች እየተቹ ይገኛሉ።

ትራምፕ ትችቱን አጣጥለው ጥቃት የሚፈጸመው "በብዙ ምክንያት ነው" ብለዋል።

አሜሪካ ባለፈው መስከረም ወር በካሪቢያን እና ምሥራቅ ፓሲፊክ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 64 ሰዎች መገደላቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ "ጥቃት ሲፈጸምበት ያያችሁት ጀልባ ባጠቃላይ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር 25,000 ሰዎች የሚገድል እና ቤተሰብ የሚበትን ነው" ብለዋል።

ትራምፕ በእግረኛ ጦር ዜንዝዌላ ውስጥ ጥቃት ያደርሱ እንደሆነ ተጠይቀው "ያንን አደርጋለሁ ለማለት አልችልም። ቬንዝዌላን ምን እንደማደርጋት አልነግራችሁም። ጥቃት አደርሳለሁ ወይም አላደርስም የሚለውን አልገልጽም" ሲሉ መልሰዋል።

ማዱሮ ከዚህ ቀደም "አሜሪካ አዲስ ጦርነት እየጫረች" ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በበኩላቸው አሜሪካ ጥቃት የምትፈጽመው ላቲን አሜሪካን "ለመቆጣጠር" ነው ሲሉ ትራምፕን ወንጅለዋል።

ትራምፕ "ከመላው ዓለም ሰዎች እንዲመጡ አንፈቅድም። ከኮንጎም ይመጣሉ፣ ከደቡብ አሜሪካም ይመጣሉ። ከቬንዝዌላ የሚመጡት ደግሞ ወንጀለኞች ናቸው" ብለዋል።

ትራምፕ በተለይም 'ትሬን ደ አርጉዋ' የተባለው የወንጀለኞች ቡድን "እጅግ የከፋው ነው" ብለውም ተናግረዋል።

አሜሪካ ትልቁን የጦር መርከቧን ከሜድትራኒያን ወደ ካሪቢያን ባሕር ማስጠጋቷን ተከትሎ ማዱሮ "አዲስ ውስጣዊ ጦርነት እየጫሩ ነው። 'ዳግመኛ እጃችንን ጦርነት ውስጥ አናስገባም' ቢሉም አዲስ ጦርነት እየቀሰቀሱ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።

የአሜሪካ መከላከያ ጸሐፊ ፒት ሄግሴት እስከ 90 ተዋጊ ጀቶችን የሚይዘው ግዙፍ የጦር መርከብ (USS Gerald R Ford) ወደ ካሪቢያን እንዲጠጋ አዘዋል።

አሜሪካ በካሪቢያን አካባቢ ያለውን ወታደራዊ ይዞታዋን እያሰፋች ነው። በአካባቢው ከጦር መርከቦች በተጨማሪ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከብ እና ኤፍ-35 የጦር ጀት አከማችታለች።

አሜሪካ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚያስችል መረጃ ለሚያደርሱ ሰዎች የምትሰጠውን ጉርሻ በእጥፍ አሳድጋ 50 ሚሊዮን ዶላር ማድረሷ አይዘነጋም።

ማዱሮ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን 'መሪ ናቸው' ሲሉ ትራምፕ ቢከሱም ማዱሮ ግን አስተባብለዋል።