አሜሪካ የቬንዙዌላ መሪ ኒኮላስ ማዱሮን ለማሰር የ50 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አቀረበች

የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ

አሜሪካ የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ስር ማዋል የሚያስችል መረጃ ለሚያደርሱ ሰዎች የምትሰጠውን ጉርሻ በእጥፍ በማሳደግ 50 ሚሊዮን ዶላር አደረሰች።

ዋሽንግተን ፕሬዝዳንቱን "በዓለም ትልቁ የዕፅ አዘዋዋሪ" ስትል ከሳለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥር ምርጫ በማጭበርበር ወደ ሥልጣን ተመለሱ የሚል ክስ የቀረበባቸው የማዱሮ የረጅም ጊዜ ተቺ ናቸው።

የምርጫው ውጤት በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በሰፊው ተቀባይነት አላገኘም።

የአሜሪካ ጠቅላይ ዓቃቢ ሕግ ፓም ቦንዲ ዋሽንግተን ከዚህ ቀደም ያወጣችውን የ25 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በእጥፍ ማሳደጓን በማሳወቅ፤ ማዱሮ በዕፅ ማዘዋወር ተልዕኮዎች ቀጥታ ተሳትፎ አላቸው ብለዋል።

የቬንዙዌላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቫን ጊል አዲሱን ሽልማት "አሳዛኝ" ያሉ ሲሆን እርምጃውን "የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ" ሲሉም ስም ሰጥተውታል።

"ከየት እንደመጣ ስለምናውቅ አልደነቀንም" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዓቃቢ ሕግ ቦንዲ በወሲብ ወንጀለኛ በሆኑት ጀፍሪ ኤፕስቲን ጉዳይ ለተነሳባቸው ቁጣ "ትኩረት ለማስቀየስ" እየሞከሩ ነው ብለዋል።

በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን የአሜሪካ መንግሥት በማዱሮ እና በቬንዙዌላ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የዕፅ ሽብር፣ ሙስና እና የአደገኛ ዕፅ ዝውውር ላይ ክስ መስርቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በወቅቱ የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር ፕሬዝዳንት ማዱሮ ከኮሎምቢያ አማፂ ቡድን 'ፋርክ' ጋር በመስራት "አሜሪካን ለማጥለቅለቅ ኮኬይንን እንደ መሣሪያ ተጠቅመዋል" የሚል ክስ አቅርቧል።

ሐሙስ ዕለት በኤክስ ማሕበራዊ የትስስር ገፅ ይፋ በሆነ ተንቀሳቃሽ ምስል ዓቃቢ ሕግ ቦንዲ፤ ማዱሮን በቅርቡ ትራምፕ የሽብር ቡድን ብለው ከፈረጁት ከቬንዙዌላ የወሮበላ ቡድን ትረን ዲ አራጓ ጋር እና ሜክሲኮ የሚገኘው አደገኛ የወንጀለኞች መረብ ነው ከሚባለው ሲናዋ ቡድን ጋር ይሰራሉ ብለዋል።

የአሜሪካ የዕፅ ዝውውር አስተዳደር (ዲኢኤ) ከማዱሮ እና ተባባሪዎቹ ጋር የተያያዘ 30 ቶን ኮኬይን፤ ሰባት ቶን የሚሆነው ከማዱሮ ከራሳቸው ጋር በቀጥታ የተገናኘ ኮኬይን መያዙን ተናግረዋል።

ማዱሮ ከዚህ ቀደም በቀጥታ ከዕፅ ዝውውር ጋር ባላቸው ተሳትፎ ከአሜሪካ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።

የዓቃቤ ሕግ ቦንዱ አስተያየት በአሜሪካ እና በቬንዙዌላ መንግሥት መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀው ውጥረት ቅጥያ ሲሆን፤ ዓቃቤ ሕጓ መንግሥታቸው አዲሱ እርምጃውን እና የገንዘብ ማበረታቻው እንዴት አደርጎ ለማስፈጸም እንደወጠነ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

የተባበሩት ሶሻሊስት ፓርቲ መሪ የሆኑት ማዱሮ የሥልጣን መንበሩን እ.አ.አ በ2013 ከሒጎ ቻቬዝ የተረከቡ ሲሆን፤ ተቃዋሚ ቡድኖችን በማፈን፣ በማሳደድ እና ሁከት በመፍጠር በተደጋጋሚ ክስ ይቀርብባቸዋል።

ከወራት በፊት የምርጫ ውጤትን ተከትሎ የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ አሳልፈው ሥልጣናቸው ላይ ቁብ እንዳሉ ናቸው።

ባለፈው ሰኔ ወር ግን የቀድሞ የቬንዙዌላ የወታደራዊ ደኅንነት አለቃ በማድሪድ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በአሜሪካ በበርካታ የዕፅ ዝውውር ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አውሮፓ ሕብረት ፕሬዝዳንቱ ከወራት በፊት ወደ ሥልጣን መመለሳቸውን ተከትሎ በመንግሥታቸው ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።