አሜሪካ ቃለ መሐላ የፈጸሙትን የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ለመያዝ ለሚረዳት 25 ሚሊዮን ዶላር ልትሸልም ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችል መረጃን ለሚሰጧት ሰዎች 25 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደምትሰጥ አስታወቀች።
ይህ የአሜሪካ ጥሪ የተገለጸው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በአወዛጋቢ ምርጫ ለስድስት ዓመታት ለሚቆየው ሦስተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን ቃለ መሐላ በፈጽሙበት አርብ ዕለት ነው።
አሜሪካ በቬንዙዌላ ዲሞክራሲያዊ ሂደትን አደናቅፈዋል በሚል በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የምትፈልጋቸው ፕሬዝዳንቱን ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን እና የመከላከያ ሚኒስትሩም እንዲያዙ መረጃ ለሚሰጡ ተጨማሪ በሚሊዮን ዶላሮችን በሽልማት ለመስጠት ቃል ገብታለች።
ከአሜሪካ በተጨማሪ በቬንዙዌላ "ዲሞክራሲን እና የሕግ የበላይነትን በማደናቀፍ እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ጥሰት" ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ሌሎችም አገራት ዕቀባ ጥለዋል። ከእነዚህም መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ካናዳ ይገኙበታል።
ፕሬዝዳንት ማዱሮ እና መንግሥታቸው ግን በምዕራባውያን አገራት እና በተቃዋሚ መሪዎች የሚቀርቡባቸውን ክሶች በተደጋጋሚ ሲያስተባብሉ እና ሲያወግዙ ቆይተዋል።
አሜሪካ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን እና ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸውን "በዕጽ ዝውውር ሽብርተኝነት" ከአውሮፓውያኑ 2020 አንስቶ ስትከሳቸው እና በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንደምትፈልግ ስትገልጽ ቆይታለች።
የቬንዙዌላ ባለሥልናት አሜሪካ በኮኬይን እንድትጥለቀለቅ በማድረግ አደንዛዥ ዕጾችን አንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም የአሜሪካውያንን ጤና አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርገዋል በሚል ትከሳለች።
ነገር ግን ማዱሮ ይህንን የአሜሪካንን ክስ ውድቅ አድርገውታል።
በባለሥልጣናቷ ላይ ክስ ከማቅረብ በተጨማሪም አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ ጥላ የነበረ ሲሆን፣ ያለፈው ዓመት ምርጫ ሲቃረብ ማዱሮ ነጻ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ያደርጋሉ በሚል ተስፋ ማዕቀቡን አንስታው የነበረ ቢሆንም መልሳዋለች።
ፕሬዝዳንት ማዱሮ አገራቸው ለገጠማት ምጣኔ ሀብታዊ ውድቀት "ሕገወጥ እና የተስፋፊነት ድርጊት ነው" ያሉትን በአሜሪካ መሪነት የተጣለውን ማዕቀብ ተጠያቂ አድርገዋል።
የፕሬዝዳንቱ ተቺዎች ግን የችግሩ ምንጭ ሙስና እና ምጣኔ ሀብቱ በአግባቡ ባለመመራቱ ነው ይላሉ።
አርብ ዕለት ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ቃለ መሐላ የፈጸሙት ፕሬዝዳንት ማዱሮ መጪዎቹ ዓመታት ለአገራቸው "የሰላም፣ የብልጽግና፣ የእኩልነት እና የዴሞክራሲ" እንደሚሆኑ እና ይህንንም እውን እንደሚያደርጉ ቃል ተብተዋል።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር በተደረገው እና ማዱሮ አሸናፊ እንደሆኑበት የተገለጸውን የምርጫ ውጤት ተቃዋሚዎችን ጨምሮ ጎረቤት አገራት ብራዚል እንዲሁም ኮሎምቢያ ሳይቀሩ ተቃወመውታል።
የፕሬዝዳንቱ ሲመተ በዓል ጥብቅ ቁጥጥር የተደረገበት ሲሆን፣ አብዛኞቹ ፈቃድ ያላቸው የቬንዙዌላ መገናኛ ብዙኃን ለመታደም ያልቻሉ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ደግሞ ወደ አገሪቱ ለመግባት አልተፈቀደላቸውም።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኩባ እና የኒካራጓ ፕሬዝዳንቶች ብቻ ናቸው።
በምዕራባውያን እየተደረገባት ባለው ጫና ቬንዙዌላ ከዓለም አቀፍ መድረኮች እየተገለለች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የምዕራባውያን ተቀናቃኝ የሆኑት ኢራን፣ ቻይና እና ሩሲያ የኒኮላስ ማዱሮ የቅርብ ወዳጆች ናቸው።
በምርጫው የ62 ዓመቱ ማዱሮ ማሸነፋቸው ቢገለጽም የተቃዋሚ ፓርቲው ተፎካካሪ እና አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ አገራት ውጤቱን ውድቅ አድርገው፣ አሁን በስደት ላይ የሚገኙትን የተቃዋሚውን ዕጩ ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ የምርጫው አሸናፊ ናቸው በሚል ዕውና ሰጥተዋል።
የኒኮላስ ማዱሮ መንግሥት ግን ስፔን በሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ላይ የእስር ትዕዛዝ ያወጣ ሲሆን፣ ጎንዛሌዝን ለመያዝ የሚያስችል መረጃን ለሚሰጥ ሰው የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት ለማበርከት ቃል ገብቷል።












