ከአሜሪካ የተባረሩ ስደተኞች በኤል ሳልቫዶር ስቅይት እንደ ደረሰባቸው ቬንዝዌላ ገለፀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ቬንዙዌላ ከአሜሪካ ወደ ኤል ሳልቫዶር እስር ቤት የተላኩ ስደተኞች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል በማለታቸው ምርመራ ማድረጓን አስታወቀች።
አርብ ዕለት ከ250 በላይ ቬንዙዌላውያን ወደ ካራካስ ተወስደዋል።
ግለሰቦቹ ከአሜሪካ መባረራቸውን ተከትሎ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በኤል ሳልቫዶር ታስረዋል።
የቬንዙዌላ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ታሬክ ዊልያም ሳብ በእስር ቤቱ ውስጥ "ሥልታዊ ስቅየት" እንደተፈጸመ ገልፀው፣ እነዚህም ጾታዊ ጥቃት፣ በየዕለቱ የሚፈጸም ድብደባ እና የበሰበሰ ምግብ መስጠት ይገኙበታል።
ኤል ሳልቫዶር እስካሁንድረስ ለውንጀላዎቹ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠችም።
ሳአብ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው እና ጥርሶቻቸው የወለቁ እስረኞችን ምስል አሳይተዋል።
ቢቢሲ እነዚህን ውንጀላዎች ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ቬንዙዌላ የኤልሳልቫዶርን ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬልን፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ጉስታቮ ቪላቶሮን እና የእስር ቤት ኃላፊ ኦሳይረስ ሉና ሜዛን ላይ ምርመራ አደርጋለሁ ብላለች።።
ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እና በአሜሪካ ያሉ የሚመለከታቸው አካላት "ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ" አሳስቧል።
ቬንዙዌላ በአሁኑ ወቅት ኤልሳልቫዶር በሄግ ለሚገኘው አይሲሲ ባቀረበችው እስረኞችን ማሰቃየት እና የሕግ ውክልና እንዳያገኙ መከልከል ክስ ላይ ምርመራ እያደረገ ነው።
ቬንዙዌላውያኑ ከአሜሪካ የተባረሩት በመጋቢት ወር ነበር።
ግለሰቦቹ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የወንበዴዎች ቡድን አባል ናቸው ተብለው የተከሰሱ ሲሆን ዘመዶቻቸው እና ጠበቃዎቻቸው ግን ክሱን ያስተባብላሉ።
እነዚህ እስረኞች ታስረው የነበረው በከባድ የሽብርተኛ ወንጀል የተከሰሱ ታሳሪዎች በሚቆዩበት እና በወንበዴ ቡድን አባልነት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለማቆየት በተገነባው እስር ቤት ውስጥ ነበር።
ቡድኑ ጠበቃም ሆነ ዘመዶቻቸውን ማግኘት ያልቻሉ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ የታዩት የቡኬሌ መንግሥት በለቀቃቸው ፎቶግራፎች ላይ ነበር።
በዚህ ምስል ላይ ስደተኞቹ ፀጉራቸውን ተላጭተው እና እጃቸውን በካቴና ታስሮ የሚታይ ሲሆን ይህም ዓለም አቀፍ ቅሬታን ቀስቅሷል።
በሐምሌ ወር አጋማሽ በቬንዙዌላ ውስጥ በተያዙ የአሜሪካ ዜጎች ምትክ ኤል ሳልቫዶር እስረኞቹን ለቅቃለች።
የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን ለጋዜጠኞች የቡክሌ መንግሥት ስምምነቱን ስላመቻቸ ያላቸውን "ትልቅ፣ ጥልቅ ምስጋና" ገልፀዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በቬንዙዌላ ላይ ከባድ ማዕቀቦችን የጣለች ሲሆን፣ በግንቦት ወር ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለቬንዙዌላ ዜጎች ያስቀመጠው ጊዜያዊ ከለላ ሊሰረዝ እንደሚችል ወስኗል።
በዚህ ውሳኔ መሰረትም ወደ 350,000 የሚጠጉ ሰዎችን ይጎዳሉ።















