የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ ስደተኞችን ወደ ሦስተኛ አገር እንዲያባርሩ ፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን ከአገራቸው ባለፈ ወደ ሦስተኛ አገር ማባረር እንዲችል መንገዱን ጠርጓል።
የታችኛው ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገር ሲባረሩ የሚገጥማቸውን ችግር እንዲያስረዱ "ትርጉም ያለው እድል" እንዲሰጥ የወሰነውን ውሳኔ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ስድስት ለሦስት በሆነ ድምፅ ሽሮታል።
ሦስት ለዘብተኛ የፍርድ ቤቱ ዳኞች " ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ" ነው ያሉትን ብይን ተቃውመዋል።
ጉዳዩ ባለፈው ግንቦት የምያንማር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኩባ፣ ሜክሲኮ፣ ላኦስ እና ቬትናም ስምንት ስደተኞችን ወደ ደቡብ ሱዳን የሚወስድ አውሮፕላን ውስጥ እንዲሳፈሩ መደረጉን ተከትሎ የመጣ ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች "ከከፉትም የከፉ" ናቸው ብሏል።
የቦስተን የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ ብራየን መርፊ ባለፈው ሚያዚያ ስደተኞቹ በሦስተኛ አገር ማሰቃየት ወይንም ግድያ ይፈፀምብናል ብለው ካመኑ ጉዳያቸውን እንዲያሰሙ እድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ይህም እድል ሌሎች ሕጋዊ አቤቱታዎቻቸው ውድቅ ቢደረጉ እንኳ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዳኛ ሶኒያ ሶቶማየር፣ ኢሌና ኬጋን እና ኬትማጂ ብራውን ጃክሰን ሰኞ እለት በአብላጫ ድምፅ የፀደቀውን እና ያልተፈረመውን ውሳኔ "ከባድ ጥሰት" ሲሉ ተችተውታል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ውሳኔው "ለአሜሪካ ሕዝቦች ደኅንነት እና ጥበቃ ድል ነው" ብሏል።
የተቋሙ ቃል አቀባይ ትሪሺያ ማክሊን "ማባረሪያ አውሮፕላኖች ያሟሙቁ" ሲሉ ከውሳኔው በኋላ ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ስምንቱ ስደተኞች በአሜሪካ ግድያ፣ እሳት ቃጠሎ እና በጦር መሳሪያ ዝርፊያን ጨምሮ "አስከፊ ወንጀሎችን" የፈፀሙ ናቸው ብሏል።
የስደተኞቹ ጠበቃ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባስገቡት ማመልከቻ አብዛኞቹ ስደተኞች ወንጀለኛ ተብለው የተፈረደባቸው አይደሉም ብለዋል።
ከሳሾቹን የወከለው ብሔራዊ የኢሚግሬሽን ሙግት ትብብር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ "አስፈሪ" ብሎታል።
የትብብሩ ስራ አስፈፃሚ ትሪና ሪልሙቶ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደንበኞቻቸውን "ለስቃይ እና ሞት" ያጋለጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
ትራምፕ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰዱት የታችኛው ፍርድ ቤት የወሰነውን ባለፈው ወር የቦስተን ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ባለመቀልበሱ ነው።
በባይደን የተሾሙት ዳኛ ብራየን መርፊ የአሜሪካ መንግሥት ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገር ሳያባርር የአሜሪካ የጦር ሰፈር ባለበት ጅቡቲ እንዲያቆዩ ጠይቀዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጆን ሳወር ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ለአደገኛ ወንጀለኞች ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ለመመስረት ተገደዋል ብለዋል።
ዓቃቢ ሕጉ አክለውም አደገኛ ወንጀለኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ አገራት ለመቀበል ፈቃደኛ ስለማይሆኑ መንግሥት ብዙ ጊዜ እንደሚቸገር፤ ይህም ስደተኞቹ "ሕግ አክባሪ አሜሪካዊያንን ዳግሞ እየጎዱ" በአሜሪካ እንዲቆዩ አድርጓል ሲሉ አብራርተዋል።
የሰኞው ውሳኔ አያሌ ስደተኞችን ለማባረር ለወጠኑት የሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ሌላ ድል ነው።
ባለፈው ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 350 ሺህ ስደተኞች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እና ለቬኑዚዌላ ዜጎች ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ ጥበቃ እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፏል።
በሌላ ውሳኔ ባለፈው ግንቦት ወር ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ የኩባ፣ ሄቲ፣ ኒካራጉዋ እና ቬንዙዌላ ስደተኞች ለሁለት ዓመት በአሜሪካ ሲቆዩ የሚሰጣቸውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፕሬዝዳንቱ በጊዜያዊነት እንዲያቋርጡም ወስኗል።















