ከአገራቸው ጦርነት ሸሽተው በኢራን ግጭት አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ሱዳናውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ባልተጠበቀ መልኩ በኢራን ላይ የከፈተችው ጥቃት ኢራናውያንን ብቻ ሳይሆን በአገራቸው ያለውን ጦርነት ሸሽተው መጠለያ ብለው የመጡ ሱዳናውያንን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል።
ሱዳናውያኑ በተጠለሉባት ኢራን ውስጥ ሕይወታችንን እናቆያለን፣ ትምህርት፣ ሥራ እናገኛለን በሚል ተስፋ ነበር ያቀኑት።
ከእነዚህ መካከል ሱዳናዊው የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው እና ለደኅንነቱ ሲል ስሙን መጠቀም ያልፈለገው ሳሊም ማህሙድ አንዱ ነው።
ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሁለት ዓመት ያለፋት ሲሆን፣ በአገር ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሲፈናቀሉ ሌሎች ደግሞ ከሱዳን ወጥተው ወደ ተለያዩ አገራት ተሰደዋል።
ከአገራቸው ጦርነት ሸሽተው ኢራን የደረሱት ሱዳናውያን ደግሞ እስራኤል በከፈተችው ጥቃት ደኅንነታቸው ሌላ ፈተና ገጥሞታል።
"የተቀበለችኝ ኢራን አዲስ የጦር አውድማ ሆነች"
ሳሊም ኢስፋሃን በተሰኘችው ከተማ ነዋሪ ነው፤ ከተማዋ ጸጥ ያለች እና ያንቀላፋች የነበረች ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የማያባራ የእስራኤል አየር ጥቃት ዒላማ ሆናለች።
ሌሊቱ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እና የፍንዳታ ድምጾች ሞልተውታል ይላል።
"አሁን ሁለት ሸክሞች አሉኝ፤ በጦርነት የምትናወጠው አገሬ ሱዳን እና በአገርነት የተቀበለችኝ ኢራን አዲስ የጦርነት አውድማ ሆናለች" ሲል ያስረዳል።
የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው ሳሊም የመጀመሪያው የእስራኤል ጥቃት እምባዛም አላስደነገጠውም ነበር፤ ነገር ግን በፍጥነት መባባሱ ግራ አጋባው።
እንደ ሌሎች ኢራንን አዲሷ መኖሪያቸው ያደረጉ ሱዳናውያን በአገሩ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና በጦር ሠራዊቱ መካከል እየተደረገ ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነትን ሸሽቶ ነው የመጣው።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ያፈናቀለው የሱዳን ጦርነት አገሪቱን የዓለማችን የከፋ ሰብአዊ ቀውስ መገኛ እንዳደረጋት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ሳሊም በኢስፋሃን፤ ከተማዋን ያናወጠ ፍንዳታ ካየ በኋላ በቀጣዩ ቀን 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው የካሻን ከተማ አቀና።
ጥቃቶቹ መቀጠላቸውን ተከትሎ ቀላል ባይሆንም አማራጭ ያለው ኢራንን ለቆ ወደ ማሌዢያ ሄዶ ትምህርቱን ለመጨረስ እያሰበ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጦርነት እየተናወጠች ወዳለችው አገሩ ሱዳን መመለስ ለሳሊም የሚታሰብ አይደለም።
እስራኤል ከሳምንት በፊት በመላው ኢራን ባሉ የኒውክሌር ተቋማት፣ ወታደራዊ ስፍራዎች እና የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ እየፈጸመቻቸው ያሉ ጥቃቶች እንደቀጠሉ ነው።
የእስራኤል ጥቃቶች በበረቱበት በአሁኑ ወቅት አንዳንዶች ከወታደራዊ ይዞታዎች በመራቅ ጸጥ ወዳሉ እንደ ካሻን እና ያዝድን ወደ መሳሰሉ ከተሞች እያቀኑ ነው።
ከአምስት ዓመት በፊት ከእስራኤል ጋር ግንኙነቴን አሻሽያለሁ ያለው በሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት የተቋቋመው የሱዳን መንግሥት እስራኤል በኢራን ላይ ያደረሰችን ጥቃት አጥብቆ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።
የኢራንን ሉዓላዊነት እንደሚደግፍ እና በማንኛውም አገር ላይ የሚደርስን ወታደራዊ ጥቃት በመቃወም ነው አቋሙን የገለጸው።
ቴህራን የሚገኘው የሱዳን ኤምባሲ ከአገሪቱ መውጣት ለሚፈልጉ ዜጎች መንገድ እንዳመቻቸው አስታውቋል።
ኤምባሲው 200 ያህል ዜጎች መመዝገቡን የሚናገሩት በኢራን የሱዳን አምባሳደር አብዱላዚዝ ሳሌህ 25ቱ በመጀመሪያው ዙሪያ እንደሚወጡ አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሁለት ጦርነቶች መካከል የቆሙት ሱዳናውያን
ኢራን ውስጥ የሚኖሩ ሱዳናውያን በአጠቃላይ ወደ አንድ ሺህ እንደሚገመቱ ተመራማሪ እና ጋዜጠኛ የሆነው አቴፍ ሐሰን ለቢቢሲ ተናግሯል።
አብዛኞቹ የሚኖሩት ቆም በተሰኘችው ከተማ ነው።
በኢራን ዋነኛው የእስልምና ቅርንጫፍ የሆነው የሺዓ እስልምና እና የባህል ማዕከል የሆነችው ይህች ከተማ ሕግን፣ የእስልምና አስተምህሮን እንዲሁም የፋርስ ቋንቋን ማጥናት የሚፈልጉ ተማሪዎች ይጎርፉባታል።
በቴህራን አዲስ ለሚመጡ ነዋሪዎች በማስተርጎም እና በአስተማሪነት የሚሠራው ሱዳናዊው አንዋር ባለፉት ቀናት የተከሰቱት ሁኔታዎች ያሉበትን አካባቢ እንደቀየሩት ይናገራል።
"ባለፈው ሳምንት ሁሉም ነገር ተቀይሯል። በቴህራን በአሁኑ ወቅት የምንሰማቸው ተከታታይ ፍንዳታዎች እንዲሁም ጎን ለጎን የማስጠንቂያ ደወሎችን ብቻ ነው" ይላል።
አንዋር አክሎም "መጠለያ ብዬ የተሰደድኩባትን አገር እንደገና እሸሻለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም" ይላል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከሦስት ቀናት በኋላ በቴህራን ናርማክ ሰፈር እስራኤል ያደረሰችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ ከፍተኛ ፍንዳታዎች መከሰታቸውን ይናገራል።
በቀጣዮቹ ሰዓታትም ዜናው ሁሉ ቀጣዩ የእስራኤል ጥቃት እና የኢራን አጻፋዊ የሚሳዔሎች ምላሽ ሆኗል መሆኑን ይናገራል።
አንዋር በማግስቱ ለደኅንነቱ ሲል ከቴህራን በስተምዕራብ 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው እና የጦር ሰፈሮች ወደሌሉባት የካራጅ ከተማ ለመሄድ ወስኗል።
"ከዚህ በፊት ከማውቃቸው ኢራናዊ ቤተሰብ ትንሽዬ ጊዜያዊ አፓርታማ ተከራዬሁ። እነሱም በጣም ነው የተባበሩኝ፤ እንግዳ ተቀባይ ናቸው።"
"ምንም እንኳን አሁን ብረጋጋም ሕይወቴ ከውጥረት ነጻ ሊሆን አልቻለም። ሆኖም ቢያንስ የማስጠንቀቂያ ደወሎች አይሰሙም፤ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የሉም" ሲል ያስረዳል።
ከቴህራን ከመውጣቱ በፊት የኮሙኒዩኬሸን አገልግሎት መድከሙን፣ ሆስፒታሎች ተጨናንቀው በአጠቃላይ የነበረው ሰብዓዊ ሁኔታ እያሽቆለቆለ እንደነበር ይገልጻል።
ነገር ግን ሁሉም ሱዳናውያን አይደለም የኢራን ሁኔታ ያስጨነቃቸው።
በቴህራን ነዋሪ የሆነው እና ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረው ሱዳናዊው አሊ ኑር የእስራኤል ጥቃት በተወሰኑ ስፍራዎች ላይ ያተኮረ እንጂ ሙሉ መዲናዋን እንደማያካልል ለቢቢሲ ገልጿል።
በኢራን በፀጥታ ሁኔታ ላይ የሚወጡ ሪፖርቶች አብዛኛውን ጊዜ የተጋነኑ እንደሆኑ የሚሰማው አሊ፤ በዚህም የተነሳ አገሪቱን ለቅቆ ለመውጣት ሃሳብ የለውም።
"ኢራንን ለቅቆ በጦርነት በአስከፊ ሁኔታ እየተናወጠች ወዳለችው ሱዳን መመለስ ምንም ትርጉም የለውም" ሲል ያስረዳል።















