ቴህራን የአሜሪካን ጦር ሠፈሮች እና ቁልፍ ቦታዎች ልታጠቃ ትችላለች?

የእስራኤል እና የኢራን ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ኢራን ላይ ሰኔ 6/2017 ዓ.ም. ጥቃት መፈጸም ጀምራለች

ኢራን እና እስራኤል አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ሚሳኤል መተኮስ ከጀመሩ ሳምንት ሞልቷቸዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዩናይትድ ስቴትስ ግጭቱን ትቀላቀል እንደሆነ ሲጠየቁ "አደርገው ይሆናል፣ አላደርገውም ይሆናል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች እና ዘጋቢዎቹ በሁለቱ አገራት ግጭት ዙርያ ከተመልካቾች እና አንባቢዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት እየፈጸመች ያለችው ለምንድን ነው?

የእስራኤል መንግሥት በዚህ ጉዳይ ምርጫ እንደሌለው ነው የሚናገረው።

ባለፉት ጥቂት ወራት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋን እያፋጠነች መሆኗን እና የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለመግታት የታለሙ ንግግሮች የትም እንዳልደረሱ ስለዚህም ይህ የመጨረሻው አማራጭ እንደሆነ ማመኑን ይገልጻል።

ከኢራን የኅልውና ስጋት እንደተጋረጠባቸው ተናግረዋል፤ እንዲሁም ኢራን የእስራኤልን መንግሥት ለማጥፋት አስቀድማ ቃል ስለገባች የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከታጠቀች ትጠቀመዋለች ብለዋል።

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት ተቃርባለች የሚለው ሌሎች በቀጠናው የሚገኙ አገራት የሚጋሩት አቋም አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እንዲሁም የአሜሪካ የስለላ ድርጅት መረጃ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልታመርት ነው የሚል ተጨባጭ መረጃ አላቀረቡም።

እስራኤል በቴህራን የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የተጎዳ የመኖርያ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሁለቱ አገራት መካከል ግጭቱ የተጀመረው እስራኤል የኢራንን ወታደራዊ እና የኒውክሌር ተቋማት ካጠቃች በኋላ ነው

የኢራን ሰላማዊ ዜጎች ወዴት ይሂዱ?

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ነዋሪዎች ከኢራን ዋና ከተማ ቴህራን የተወሰኑ አካባቢዎች ለቅቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያዎችን አውጥቷል።

ነገርግን እነዚህ አካባቢዎች እጅግ በጣም ጥቅጥቅ ያሉ እና ብዙ ሰዎች የሚኖሩባቸው ናቸው።

እጅግ በጣም ብዙ መንገዶች ከቴህራን ለመውጣት እና ወደ ሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል ለመሄድ በፈለጉ ሰዎች ተጨናንቀው የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።

ነገር ግን በእነዚያ አካባቢዎች የእስራኤል መንግሥት ጥቃቶቸን እየፈጸመ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እስራኤል የጥቃት አድማሷን ማስፋቷ ሲሆን በዚህም የተነሳ የትኛውም አካባቢ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ተብሎ ሊወሰድ አይችልም።

በቴህራን መንግሥት የባቡር መስመሮችን 24 ሰዓት ክፍት ማድረጉን እና ዜጎች ወደ መጠለያዎች መሄድ እንደሚችሉ ገልጿል።

ቴህራን 10 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ሲሆን እነዚህን ሁሉ ሕዝቦች ማስወጣት ቀላል አለመሆኑን ማሰብ ይቻላል።

በቴህራን የተሰባሰቡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን 10 ሚሊዮን ሰዎች ይኖራሉ

አሜሪካ በሁለቱ አገራት ግጭት ውስጥ ብትሳተፍ ኢራን የአሜሪካ ዒላማዎችን ታጠቃለች?

በእርግጥ አደጋ አለ። ያ ብቻ ሳይሆን አሜሪካ ላይ የሚያስከትላቸው መዘዞች ቀላል አይሆኑም።

በመካከለኛው ምሥራቅ በ19 አካባቢዎች ከ40,000 እስከ 50,000 የሚደርሱ የአሜሪካ ወታደሮች አሉ።

በቆጵሮስ መቀመጫቸውን ያደረጉ የአሜሪካ ሠራተኞች እና በባህሬን ውስጥ የአሜሪካ የባህር ኃይል ተቋም አሉ።

ሁሉም አሜሪካ እንዴት እና በምን ያህል መጠን ለመሳተፍ እንደምትወስን ይወሰናል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢራን የሚደገፉ ኃይሎች በሁለቱ አገራት ግጭት ውስጥ ይሳተፋሉ?

አይመስለኝም፤ ከእንግዲህ አይሆንም።

ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ፣ እስራኤል ኢራን የነበራትን ብዙ የመጀመሪያ የመከላከያ መስመሮችን በተደራጀ ሁኔታ መትታለች።

በጋዛ ውስጥ ሐማስን አዳክማለች፤ በሊባኖስ የሚገኘውን የሂዝቦላህን የጦር መሳሪያ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሳለች። ሶሪያ በሽር አል አሳድ ከስልጣን በመውረዳቸው ከእንግዲህ በኋላ የኢራን አጋር አይደለችም። ስለዚህ ከእንግዲህ ለእስራኤል ስጋት የሚሆኑበት ዕድል የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁቲዎች በአንፃራዊ ሁኔታ በየመን የተገደቡ ናቸው። ስለዚህ እነሱ በደንብ የተቀናጁ አይደሉም።

የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ናቸው

የኢራኑ መሪ ማን ነው? ምን ያህልስ ድጋፍ አለው?

የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ናቸው። እርሳቸው የሃይማኖት ሰው ናቸው፤ ይሁን እንጂ ከኢራን ፕሬዝዳንት የበለጠ ስልጣን አላቸው።

የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሲሆኑ ከአሜሪካ ጋር ድርድር ማድረግን ጨምሮ በአገሪቱ ውስጥ ውሳኔ ሰጪ ናቸው።

ነገር ግን የመላው ኢራናውያን ድጋፍ የላቸውም። ኢራናውያን ተከፋፍለዋል፤ ክፍፍሉ ደግሞ እየሰፋ ነው።

ኢራን በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞዎችን ያስተናገደችው ከሁለት አመት በፊት ነው። ሴቶች መብታቸውን እና ነጻነታቸውን በመጠየቅ በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ ተሳትፈዋል።

ነገር ግን ይህ አገዛዝ አሁንም ከስርዓቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው የታጠቁ ኃይሎችን ጨምሮ ደጋፊዎች እንዳሉት ችላ ማለት የለብንም።

የኢራን መንግሥት ከሥልጣን ቢወገድ ምን ይከሰታል?

ለዚህ ግልጽ መልስ የለውም።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥትን ለመተካት በጋራ የሚሰራ ተቃዋሚ እንደሌለ አይተናል።

አሁን በውጭ አገር የሚኖረው የኢራን የቀድሞ ሻህ ልጅ ሬዛ ፓህላቪን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮች አሉ።

እሱ ከኢራን ውስጥ እና ውጭ ደጋፊዎች ያሉት ቢሆንም ስንት ናቸው የሚለውን በትክክል መናገር አይቻልም።

በውስጡም የለውጥ አራማጆችን ጨምሮ ተቃዋሚዎች አሉት። ከዛሬ 40 ዓመት ገደማ በፊት ወደ ተገረሰሰው የኢራን ንጉሣዊ አገዛዝ መመለስ ላይፈልጉ ይችላሉ።

ስለዚህ ይህ ነው የሚባል ምትክ ስለመኖሩ ግልጽ አይደለም።

እስራኤል በሄዝቦላህ ላይ የፈጸመችው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፎርዶ የት ነው የሚገኘው? ምንድን ነው?

ፎርዶ ከቴህራን በስተደቡብ 200 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ኢራን ካላት ሁለት ወሳኝ የኒውክለር ማበልጸጊያ ተቋማት አንዱ ነው።

የተገነባው በተራራ ሆድ ውስጥ ሲሆን ኢራን የበለፀገውን የዩራኒየም ክምችቷን ለማሳደግ ስትጠቀምባቸው ከነበሩት ቁልፍ ተቋማት አንዱ ነው።

ፎርዶ በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ተመትቷል። ሆኖም ጥቃቱ የበለጠ ተጋላጭ ለማድረግ በዙርያው የሚገኙ ወደ አየር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን እና የአየር መከላከያ መሳርያዎችን ብቻ እንደሆነ ይታመናል።

ኢራን የኒውክሌር ቦምብን ለመስራት ምን ያህል ተቃርባለች?

ኢራን የኒውክሌር ቦምብ እየገነባች ለመሆኑ እና ላለመሆኑ እቅጩን የሚያውቁት ሰዎች የአገሪቱ ታማኝ የኒውክሌር ተመራማሪዎች፣ ውስጠ አዋቂ የደኅንነት ሹማምንት እና ራሳቸው ታላቁ መሪ ኻሚኒ ብቻ ናቸው።

የተረፈው ግምት ነው።

ይሁን እንጂ የማስጠንቀቂያ ደውሉ የተደወለው በዚህ ወር የመንግሥታቱ ድርጅት ተቆጣጣሪ የሆነው ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጄንሲ ኢራን ከ20 ዓመታት ገደማ በኋላ የመሳሪያ ማስፋፋትን የሚከለክላትን ግዴታ ጥሳ መገኘቷን አግኝቷል።

ኢራን በጥቅሉ 400 ኪሎ ግራም ወይም 60 በመቶ የዩራኒየም ክምችት ያላት ሲሆን ይህም ለሲቪል የኒውክሌር ዓላማ ከሚያስፈልገው መጠን በላይ ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት ኤጄንሲ ኢራን ሙሉ ለሙሉ ለመተባበር አሻፈረኝ ማለቷን እና የኒውክሌር ግብዓቶችን የኒውክሌር መሳሪያ ለመስራት ተጠቅማለች የሚለውን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።

ይህም ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ለመስራት እየተሯሯጠች ነው ማለት አይደለም።

የእስራኤል ጦር ባለፈው ሳምንት "ባለፉት ጥቂት ወራት የደኅንነት መረጃዎች ኢራን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኒውክሌር ቦምብ ባለቤት ለመሆን መቃረቧን ያሳያሉ" ብሏል።

የቅርብ አጋሯ መረጃ ግን ይህን አያሳይም።

ባለፈው መጋቢት ወር የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ኃላፊ ቱልሲ ጋባርድ ለአገሪቱ ምክር ቤት "ኢራን መሳሪያ መስራት የሚያስችል ያልተጠበቀ የዩራኒየም ክምችት ቢኖራትም የኒውክሌር መሳሪያ እየሰራች መሆኑን አላየንም" ብለዋል።

ኢራን የኒውክሌር መርሐ ግብሯ ሙሉ ለሙሉ ሰላማዊ ነው በማለቷ ፀንታለች።

እስራኤልስ የኒውክሌር መሳሪያ አላት?

እስራኤል 90 የኒውክሌር ተተኳሽ (አረር) እንዳላት ይገመታል፤ ነገር ግን ትክክለኛ መልሱን አናውቅም።

አገሪቱ የኒውክሌር አቅሟን በሚመለከት አረጋግጣም ሆነ ክዳ አታውቅም።

እስራኤል በመላው ዓለም የኒውክሌር መስፋፋትን ለመቆጣጠር የተፈረመው ኒውክሌርን ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የማዋል ስምምነት አካል አይደለችም።

የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን ሦስት ክፍሎች ያስፈልጋሉ።

የመጀመሪያው የዩራኒየም ማበልፀግ 90 በመቶ መድረስ፤ ሁለተኛ ተተኳሹን የማዘጋጀት አቅም ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ተተኳሹን ወደ ኢላማ ማድረሻ መንገድ ነው።

በእስራኤል በኩል ከላይ የተገለፁትን ሁኔታዎች የሚያሳይ ግልፅ ማሳያ የለም።