አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ36 አገራት ዜጎች ላይ የጉዞ ዕገዳ ልትጥል ነው

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያን ጨምሮ የ36 አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ለማገድ ሃሳብ እንዳለው ሮይተርስ እና ዋሽንግተን ፖስት የተመለከቱት የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጣዊ ሰነድ አመለከተ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የተፈረመው ለዲፕሎማቶች የተዘጋጀው ሰነድ ላይ በቀጣይ ዜጎቻቸው ላይ ዕገዳ ሊጣልባቸው የታሰቡት 36 አገራት ዝርዝር የሰፈረ ሲሆን፣ አገራቱ ከዕገዳው ለመውጣት ማከናወን የሚጠበቁባቸው ማስተካከያዎችም ተካተውበታል።

ሰነዱ ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሙሉ ወይም ከፊል ዕገዳ የሚጣልባቸው አገራት በመለየት ያሉባቸውን ችግሮች በማስቀመጥ፤ይህ ዕገዳ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት አገራቱ የሚጠበቅባቸውን መመዘኛዎች እና ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉ የሁለት ወራት ጊዜ እንደሚሰጣቸው ተጠቅሷል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለሚመለከታቸው ዲፕሎማቶች የተሠራጨው ሰነድ "[የውጭ ጉዳይ] መሥሪያ ቤቱ የተቀመጡ መመዘኛዎች እና ግዴታዎችን በ60 ቀናት የማያሟሉ ከሆነ ሙሉ ወይም ከፊል የጉዞ ዕገዳ የሚጣልባቸውን አሳሳቢ የሆኑ 36 አገራትን ለይቷል" ማለቱን ሮይተርስ አመልክቷል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ዜጎቻቸው ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ሊደረጉ እንደሚችሉ ከተጠቀሱት 36 አገራት መካከል 25 ከአፍሪካ ሲሆኑ ኢትዮጵያም አንዷ ናት።

ባለፈው ግንቦት ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሶማሊያን ጨምሮ ሰባት የአፍሪካ አገራት ባሉባቸው 12 አገራት ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአገራቸውን እና የሕዝባቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል ትዕዛዝ ፈርመው ተግባራዊ መሆኑ ይታወሳል።

በቀደመው የዕገዳ ውሳኔ ውስጥ የኢትዮጵያ ጎረቤት ከሆኑት ስድስት አገራት መካከል ሦስቱ የተካተቱ ሲሆን ከሁለት ወራት በኋላ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል በተባለው በአሁኑ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሰነድ ውስጥ ኢትዮጵያ ተካታለች።

ይህ ውሳኔ ተግበራዊ የሚሆን ከሆነ ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ዕገዳ የተጣለባቸው ይሆናሉ። ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች መካከልም ከዚህ ዕገዳ ነጻ የምትሆነው ኬንያ ብቻ ትሆናለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሃያ አምስት የአፍሪካ አገራት ከተካተቱበት የእገዳ ውሳኔ ሀሳብ ከቀረበባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል ጂቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ግብፅ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ናይጄሪያ ይገኙበታል።

ሰነዱ ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሊደረጉ በታሰቡት አገራት ላይ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አሳሳቢ በማለት የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጧል።

ከእነዚህም መካከል አገራቱ የዜጎችን ማንነት ለመለየት የሚያስችል አስተማማኝ ሰነዶችን ለማቅረብ ብቃት ማነስ እና ተባባሪ አለመሆን እንዲሁም የፓስፖርታቸው "ደኅንነት አጠያያቂ" መሆን በምክንያትነት ቀርበዋል።

አንዳንድ አገራት ደግሞ ከአሜሪካ እንዲወጡ የታዘዙ ዜጎቻቸውን ለመቀበል አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ተባባሪ አይደሉም የተባሉ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ ቪዛ አግኝተው ወደ አሜሪካ የገቡ ዜጎቻቸው ለመቆየት ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ መቆየታቸውም ለዕገዳው ሰበብ ከሆኑት ውስጥ ይገኛሉ።

በተጨማሪም የአገራቱ ዜጎች በአሜሪካ ውስጥ በተፈጸሙ የሽብር ተግባራት ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው፣ ወይም ፀረ ሴማዊ እና ፀረ አሜሪካ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ መሆን ለዕገዳው ምክንያት መሆኑ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።

ነገር ግን በሰነዱ ላይ ለዕገዳ ምክንያት ሆነው የቀረቡት ጉዳዮች ሁሉንም አገራት የሚመለከት ሳይሆን እንደየአገራቱ ሁኔታ እና ዜጎች ተሳትፎ የሚለያይ መሆኑ ተጠቅሷል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ከሚወዳደሩበት ጊዜ አንስቶ የስደተኞች ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው የነበረ ሲሆን፣ ወደ ዋይት ሐውስ እንደተመለሱ ነበር በርካታ ስደተኞችን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት።

ባለፉት ወራት በአሜሪካ ውስጥ ሳይመዘገቡ የሚገኙ ስደተኞች ታድነው እንዲታሰሩ እና እንዲባረሩ የሚያደርግ ዘመቻ እያካሄዱ ነው። በዚህ እርምጃቸው ምክንያት ትችት እና ከባድ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም በውሳኔያቸው ጸንተዋል።

ትራምፕ ከአሜሪካ ስደተኞችን ለማባረር ከሚወስዱት እርምጃ ጎን ለጎን ደግሞ ባለፈው ግንቦት ወር መጨራሻ ላይ ከሰኔ 1/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ የ12 አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ ዕገዳ ጥለዋል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤታቸውም ይህንን የተለያዩ አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክለውን ዕገዳ በማስፋት የተጨማሪ 36 አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቧል።