የቬንዝዌላ መከላከያ ኃይል የአሜሪካን ጥቃት መቋቋም ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶችን ተሸካሚ የሆነው ዩኤስኤስ ጄራርድ አር ፎርድ በላቲን አሜሪካ አቅራቢያ በሚገኝ ውሃ ላይ መድረሱ፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በቬንዙዌላ መካከል እየተባባሰ የመጣውን አለመግባባት የሚያመላክት ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ ከ1989 የፓናማ ወረራ ወዲህ አሜሪካ በቀጠናው ስትገኝ ይህ ግዙፉ መሆኑ ነው።
ማኑኤል ኖሪጋ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት እንደተከሰሱት ሁሉ አሁንም የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ተመሳሳይ ውንጀላ ቀርቦባቸዋል፤ እርሳቸው ግን ይህንን አጥብቀው ያስተባብላሉ።
ዋሽንግተን በበኩሏ በዓለም ላይ ትልቁን እና እጅግ የተራቀቀውን የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ በቬንዙዌላ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ብታሰማራም ዓላማዋን ግልፅ አላደረገችም።
ካራካስ ግን የሚመጣውን አደጋ ለመቀበል የተዘጋጀች ትመስላለች።
ባለፈው ሳምንት የመከላከያ ሚኒስትሩ ቭላድሚር ፓድሪኖ ሎፔዝ በማዱሮ መንግሥት ላይ የተቃጣውን ስጋት ለመከላከል በመላ አገሪቱ የምድር፣ የባህር፣ የአየር፣ የወንዝ እና የሚሳኤል ኃይል፣ ሚሊሻዎቸን ጨምሮ "ግዙፍ ኃይል ማሰማራቱን" አስታውቀዋል።
ፓድሪኖ ሎፔዝ በቴሌቭዥን በተላለፋቸው ንግግር ማዱሮ ወደ 200,000 የሚጠጉ ወታደሮች እንዲሰማሩ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ "ግዙፍ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ" ወደ አካባቢው መምጣት ዶናልድ ትራምፕ በቬንዙዌላ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ ባሏቸው የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የከፈቱት ወታደራዊ ዘመቻ አካል እንደሆነ ይናገራሉ።
በዚህም የተነሳ በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ጀልባዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ከ80 በላይ ሰዎች ሲገደሉ እና ከፊል ሰርጓጅ መርከቦች ላይም ጉዳት ደርሷል።
ነገር ግን አንዳንድ ተንታኞች ይህ እርምጃ ባለፈው ዓመት የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በተቃዋሚዎች እና በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የተጭበረበረ ነው ከተባለ በኋላ የመጣ መሆኑን ይናገራሉ።
ዋሽንግተን ሕጋዊ አይደለም በተባለው ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡትን ማዱሮን ለማዳከም አልፎ ተርፎም ለመጣል የምትወስደው እርምጃ አካል ሊሆን እንደሚችል ይከራከራሉ።
"የቀድሞው ማንነቱ ጥላ"
የማዱሮ ጦር ከዓለማችን ኃያል አገር የሚሰነዘርባቸውን ወታደራዊ ጥቃት መቋቋም ይችሉ ይሆን?
በመስከረም ወር ላይ ማዱሮ ቬንዙዌላን ለመከላከል ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን እና ከዚህ ቁጥር ከጋር የሚስተካከል ሚሊሻ ሊያስታጥቁ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ባለሙያዎች ግን ይህን አኃዝ አጥብቀው ይሞግታሉ።
ከ 2020 እስከ 2023 በቦጎታ የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት የነበሩት ጄምስ ስቶሪ "እውነት አይደለም፤ ትክክለኛው ቁጥሩ በጣም ያነሰ ነው። ማዱሮ ባለፈው ዓመት አራት ሚሊዮን ድምጽ እንኳን ማግኘት አልቻሉም" ሲሉ ለቢቢሲ ሙንዶ ተናግረዋል።
" ሠራዊቱም በጣም ከፍተኛ በሆነ ቁጥር የሚከዱ ወታደሮች የሚገኙበት ነው" በማለት አክለዋል።
የዓለም አቀፉ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም (IISS) ቬንዙዌላ 123,000 ወታደሮች እና 220,000 ሚሊሻ አባላት እና 8,000 ተጠባባቂዎች እንዳሏት ይፋ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስቶሪ እንዳሉት የቬንዙዌላ ወታደሮች እምብዛም ስልጠና የማያገኙ ወይም ደካማ የውጊያ ብቃት ያላቸው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ብዙ የቻቪስታ ሚሊሻ አባላት አልታጠቁም ።
"ምናልባት በሠራዊቱ ውስጥ ብቃት ያላቸው ጥቂት ክፍሎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን እንደ ተዋጊ ኃይል የተለየ ብቃት የላቸውም።"
አክለውም የቬንዙዌላ ጦር "የቀድሞው ሠራዊት ጥላ ነው" ካሉ በኋላ አሁንም "በአካባቢው አንዳንድ ልዩ ድጋፎች" እንዳሉት አምነዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2006 በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሁጎ ቻቬዝ ከሩሲያ ከተገዙት ወደ 20 የሚጠጉ የሱኮይ ተዋጊ ጄቶች በተጨማሪ፣ ቬንዙዌላ በ1980ዎቹ የዋሽንግተን ዋና አጋር በነበረችበት ጊዜ በርካታ የአሜሪካ ኤፍ-16ዎችን አግኝታለች።
"የሱክሆይ ተዋጊ ጄቶች በቀጠናው ውስጥ ካሉት ሁሉ የላቁ ናቸው። እና አንዳንዶቹ አሁንም እየሰሩ ናቸው ። ኤፍ-16ችን በተመለከተ አንድ ወይም ሁለት አሁንም እየሰሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል ስቶሪ።
ፀረ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች
በጥቅምት ወር መገባደጃ ላይ ከአሜሪካ ጋር ያለው ውጥረት እየጨመረ በነበረበት ወቅት ማዱሮ፣ ቬንዙዌላ 5,000 ሩሲያ ሠራሽ ኢግላ-ኤስ ፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤሎችን "በቁልፍ የአየር መከላከያ ቦታዎች" ማሰማራቷን አስታውቀዋል።
ማዱሮ በቴሌቭዥን በተላለፈ ወታደራዊ ዝግጅት ላይ "በዓለም ላይ ያለ ማንኛውም ወታደራዊ ኃይል የኢግላ-ኤስን አቅም ያውቀዋል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢግላ-ኤስ የአጭር ርቀት፣ ዝቅተኛ ከፍታ ያለው ተንቀሳቃሽ የአየር መከላከያ ሲሆን፣ የክሩዝ ሚሳኤሎችን፣ ድሮኖችን፣ ሄሊኮፕተሮችን እና ዝቅ ብለው የሚበሩ አውሮፕላኖችን መምታት የሚችል ነው።
ቬንዙዌላ በቻይና የተሰሩ ቪኤን-4 የታጠቁ ተሽከርካሪዎችም ባለቤት ስትሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጥቃት ሊፈጽሙ የሚችሉ ድሮኖች ያላት ብቸኛዋ የደቡብ አሜሪካ አገር ሆናለች፤ ይህም ኒኮላስ ማዱሮ እአአ በ2022 በወታደራዊ ሠልፍ ላይ እንዲታይ አድርገዋል።
ቬንዙዌላም ከኢራን ፔይካፕ-III (Peykaap-III) ፈጣን ጥቃት ፈጻሚ ጀልባዎችን ገዝታለች። ይህ ጀልባ የጸረ-መርከብ ሚሳኤል ማስወንጨፊያዎችን ይዟል።
አንቶኒዮ ሆሴ ዴ ሱክሬ 100 እና 200 (አንሱ-100 እና አንሱ-200) የተሻሻሉ የኢራን ሞዴሎች ላይ የተመሰረቱ እና በቬንዚዌላ የተመረቱ ድሮኖች ናቸው።
በተጨማሪም አገሪቱ በሩሲያ የተሰሩ ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን ፓንትሲር- ኤስ 1 (Pantsir-S1) እና በክ-ኤም2ኢ (Buk-M2E) መግዛቷ የተዘገበ ሲሆን እነዚህም እንደ የሩሲያ የሕግ ባለሙያ አሌክሲ ዙራቭሌቭ ከሆነ በቅርቡ በኢል-76 የጭነት አውሮፕላኖች ወደ ካራካስ ተወስደዋል።
"በቀላሉ" ሊበተን የሚችል ጦር
ነገር ግን "ቬንዙዌላ አለኝ በምትለው እና በሥራ ላይ ባለው መካከል ትልቅ ክፍተት አለ" ሲሉ የውጭ ፖሊሲ እና መከላከያ ልጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር አንድሬይ ሰርቢን ፖንት ይናገራሉ።
በአሜሪካ እና በቬንዙዌላ መካከል ያለው ውጥረት በግዛቲቱ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ወደ መፈጸም ሊያድግ እችላል የሚሉ ስጋቶች እየተሰሙበት ባለበት በዚህ ወቅት የአገሪቱ የአየር መከላከያ ስርዐት ትኩረትን ስቧል።
ይሁን እንጂ አብዛኛው የአየር መከለከያ እና መቃወሚያ ስርዓት፣ ሩሲያ ሠራሹ የፔቾራ ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፍ ሚሳዔል ስሪታቸው በ1960ዎቹ በመሆኑ፣ ከአገልግሎት ውጪ ናቸው ወይም በአሜሪካ ቴክኖሎጂ "በቀላሉ ጥቅም ላይ" እንዳይውሉ ሊደረግ ይችላል ሲሉ ዶ/ር ሰርቢን ፖንት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሽምቅ ውጊያ
ብዙ ተንታኞች ማዱሮ እና የቅርብ አጋሮቻቸው የሽምቅ ውጊያ ለማድረግ እየተዘጋጁ እንደሆነ ያምናሉ።
በመስከረም ላይ የቬንዙዌላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዲዮስዳዶ ካቤሎ አገሪቱ "ለረዥም ጦርነት" ዝግጁ መሆኗን አስጠንቅቀዋል።
ብዙም ሳይቆይ የማዱሮ መንግኅት የቦሊቫሪያን ብሔራዊ ጦር ኃይሎች (ኤፍኤንቢ) ከዝቅተኛ ማህበረሰቦች የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞች የጦር መሳሪያ አጠቃቀም እንዲያሰለጥኑ ጠይቋል።
ስቶሪ እንዲህ ባለው ዘመቻ ቬንዙዌላውያን ከማዱሮ ጎን ይሰለፋሉ የሚለውን ሀሳብ ውድቅ አድርገውታል።
"ማዱሮ በወታደሩም ሆነ በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅ አይደለም። በዚህም የተነሳ ሰዎች በሽምቅ ውጊያ ውስጥ የሚደግፉት አይመስለኝም።"
ምንም እንኳን የቬንዙዌላ መንግሥት ጦርነቱን እና ፀረ-አሜሪካን ንግግሮችን እያጠናከረ ቢመጣም ዶ/ር ሰርቢን ፖንት ግን ወታደራዊ ኃይሉ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለእውነተኛ ግጭት ዝግጁ እንዳልሆነ ተናግረዋል ።
"ከጎረቤት አገር ኮሎምቢያ ወይም ብራዚል ጋር የሚደረግ ጦርነት የአገሪቱ የጦር መሣሪያ ስርዓት በጣም ጠቃሚ ይሆናል" ካሉ በኋላ ነገር ግን ለአሜሪካ ምንም ዓይነት ስጋት አይፈጥርም ሲሉ ተናግረዋል።















