አሜሪካ በቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ይመራል ያለችውን የወንጀል ቡድን በአሸባሪነት ልትፈርጅ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ዩናይትድ ስቴትስ በቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ይመራል ስትል የምትወነጅለውን 'ዴ ሎስ ሶልስ' የተባለ የወንጀል ቡድን በአሸባሪነት ልትፈርጅ መሆኗን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ አሜሪካ ቡድኑን የውጭ አሸባሪ ድርጅት በሚል ከኅዳር 24/2025 ጀምሮ ለመፈረጅ መወሰኗን ተናግረዋል።
በዚህም የተነሳ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ማዱሮ የቡድኑ መሪ ናቸው ተብለው በመፈረጃቸው ወዲያውኑ እንደ አሸባሪ ይቆጠረሉ።
ማዱሮ ግን ከወንጀል ቡድኑ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው በመግለጽ አስተባብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመቀነስ እና በማዱሮ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል።
የውጭ አሸባሪ ድርጅት የሚለው ስያሜ የአሜሪካ መንግሥት በቡድን እና ተባባሪዎቹ ላይ የበለጠ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድ ያስችለዋል።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ቀደም ሲል በዴ ሎስ ሶልስ ላይ ማዕቀብ የጣለ ቢሆንም፣ አዲሱ የውጭ አሸባሪ ድርጅት የሚለው ስያሜ ግን ጠንካራ እርምጃዎችን ለመውሰድ አቅም የሚሰጥ ነው።
ዴ ሎስ ሶልስ የወንጀል ቡድን እንደ አደንዛዥ ዕጽ ማዘዋወር እና ሕገ ወጥ ማዕድን ማውጣትን በመሳሰሉ ተግባራት ውስጥ የተሳተፈውን ወንጀል ቡድንን ለመግለጽ አሜሪካ የምትጠቀምበት ስም ነው።
ዋሽንግተን ቡድኑ የሚመራው በቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት እንደሆነ እና ከጦር ኃይሉ የተወጣጡ ሰዎችን ጨምሮ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰዎችን ያካትታል ትላለች።
ዩናይትድ ስቴትስ ማዱሮ በአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪነት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃዎችን እስካሁን ድረስ ይፋ አላደረገችም።
ነገር ግን ዩናይትድ ስቴትስ ማዱሮን የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ አድርጋ መፈረጇ በዕጽ አዘዋዋሪዎች ላይ በምትከፍተው ወታደራዊ ዘመቻ እርሳቸውን ወይም በዙሪያቸው ያሉትን ዒላማ ለማድረግ ማሰቧን ያሳያል።
በማዱሮ ላይ ጫና ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ በቬንዙዌላ ውስጥ ያሉትን ዒላማዎች ልትመታ ትችላለች የሚለው ግምት እየጨመረ ነው።
በጥቅምት ወር አሜሪካ ጄራልድ ፎርድን የተባለው ግዙፍ የጦር መከርከብ ወደ ካሪቢያን ካሰማራች በኋላ፣ ማዱሮ አሜሪካን "አዲስ ጦርነት እየፈጠረች" ነው ሲሱ ከስሰዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መወሰናቸውን ቢናገሩም ውሳኔያቸውን ግን እስካሁን ይፋ አላደረጉም።
እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች ሩቢዮ ስለ ሁኔታው ከኮንግረስ አባላት ጋር እንዲወያዩ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
ከማዱሮ ጋር "አንዳንድ ውይይቶችን እናደርግ ይሆናል" እንዲሁም "ከቬንዙዌላ ጋር መናገር ትፈልጋለች" ቢሉም ንግግሮች መቼ እንደሚካሄዱ ተጨማሪ ዝርዝሮችን አልሰጡም።
ማዱሮ ባለፈው ዓመት ጥር ወር የተካሄደውን እና ተጭበርብሯል የተባለውን ምርጫ ካሸነፉ በኋላ የትራምፕ አስተዳደር ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።
ሩቢዮ በመግለጫቸው "ማዱሮም ሆነ ጓዶቻቸው የቬንዙዌላውን ሕጋዊ መንግሥት አይወክሉም" ብለዋል።
በነሐሴ ወር የአሜሪካ መንግሥት ማዱሮን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚረዳ መረጃ ለሚያቀብል ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለመስጠት ቃል ገብቷል።
አክሎም ይህም ግንባር ቀደም "የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ" ነው በማለት ፈርጇቸዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በተጨማሪም ቬንዙዌላ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች እንቅስቃሴን ለመግታት በበቂ ሁኔታ እየሠራች አይደለም ስትል ትተቻለች።
በዚህም የተነሳ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ አሜሪካ ለሚመጣው የፌንታኒል አደገኛ ዕጽ ፍሰት አገሪቱን ተጠያቂ አድርገዋል።
ፌንታኒል ጥሬ እቃውን ከእስያ በማስገባት በዋነኛነት የሚመረተው በሜክሲኮ በመሆኑ ከቬንዙዌላ እንደሚመጣ የሚጠቁም ምንም መረጃ የለም።
የቬንዙዌላ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ አንዳንድ የኮኬይን ዝውውር እንደሚካሄድ ያመነ ቢሆንም ነገር ግን በቀጠናው ውስጥ በጣም ግዙፍ የሕገወጥ ዕጽ ዝውውር የሚካሄድባቸው ማዕከሎች አሉ።
ኮኬይን በብዛት የሚመረተው በኮሎምቢያ፣ በፔሩ እና በቦሊቪያ ነው።
አሜሪካ ከመስከረም ወር ጀምሮ በቬንዙዌላ እና በኮሎምቢያ የባሕር ዳርቻዎች በጀልባዎች ላይ ተከታታይ የአየር ድብደባዎችን ፈጽማለች።
አሜሪካ በአስርት ዓመታት ውስጥ ግዙፍ ነው የተባለውን የጦር ሠራዊት ወደ ካሪቢያን የላከች ሲሆን፣ ቢያንስ 21 የዕጽ አዘዋዋሪዎች መርከቦች ላይ ጥቃቶችን ሰንዝራ 83 ሰዎች ተገድለዋል።















