አሜሪካ ለሁለተኛ ጊዜ የቬንዙዌላን ነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ስር አዋለች

በአሜሪካ ቁጥጥር ስር የዋለችው የቬንዙዌላ ነዳጅ ጫኝ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, X/Sec_Noem

አሜሪካ በቅርቡ ከቬንዙዌላ የተነሳች ነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች።

ይህን ያስታወቀው የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ነው።

አሜሪካ ነዳጅ የጫነች የቬንዙዌላ መርከብ በቁጥጥር ስር ስታውል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይህ ሁለተኛው ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ ማዕቀብ የተጣለባቸው ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከቬንዙዌላ እንዳይወጡ እና እንዳይገቡ "እገዳ" መጣላቸው ይታወሳል።

ቬንዙዌላ አሜሪካ መርከቧን መያዟን በክፉ ኮንና ሁኔታው "አፈና እና ዘረፋ ነው" ብላለች።

የፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ መንግሥት አሜሪካ ተፈጥሯዊ ሀብቷን ለመዝረፍ እየሞከረች ነው ሲል መክሰሱ ይታወቃል።

"ይህ ድርጊት ቅጣት ማስከተሉ አይቀሬ ነው" ይላል የቬንዙዌላ መንግሥት ያወጣው መግለጫ። አክሎም ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና "ለሌሎች የዓለም መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ መሥሪያ ቤቶች" ቅሬታውን እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

በአሜሪካ የባሕር በር ዘብ የተመራ ኃይል ነው የቬንዙዌላን ነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ስር ያዋለው። መርከቧ በቁጥጥር ስር በዋለች ወቅት ዓለም አቀፍ የውሀ ክልል ላይ ነበረች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ ሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖኤም መርከቧ በቁጥጥር ስር ስትውል የሚያሳይ ቪድዮ በኤክስ ገፃቸው አጋርተዋል።

"ታኅሣሥ 20 ሲነጋጋ በተደረገ ኦፕሬሽን የአሜሪካ ባሕር ዘብ ከጦር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከቬንዙዌላ የተነሳችው ነዳጅ ጫኝ መርከበት በቁጥጥር ስር አውሏል" ይላል ሚኒስትሯ ያጋሩት መልዕክት።

ሚኒስትሩ የለጠፉት 7 ደቂቃ የሚረዝም ቪድዮ የአሜሪካ ሄሊኮፕተሮች ሴንቸሪስ የሚል ስም የተለጠፈባት መርከብ ላይ ሲያርፉ ያሳያል።

"አሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ነዳጅ እንቅስቃሴን መቆጣጠር ትቀጥላለች። ይህ ነዳጅ በቀጣናው የአደገኛ ዕፅ ሽብር እንዲፋፋም ጥቅም ላይ የሚውል" ያሉት ክሪስቲ አክለው "የገባችሁበት ገብተን እናስቆማችኋለን" የሚል ማስጠንቀቂያ ፅፈዋል።

ሴንቸሪስ የተሰኘችው መርከብ ላለፉት አምስት ዓመታት በፓናማ ባንዲራ የምትንቀሳቀስ ሲሆን ከዚህ ቀደም በግሪክ እና ላይቤሪያ ባንዲራ ትንቀሳቀስ እንደነበር ቢቢሲ ማጣራት ችሏል።

መርከቧ አሜሪካ ማዕቀብ ከጣለችባቸው ነዳጅ መርከቦች ስም ዝርዝር ውስጥ አልተካተተችም።

በቅርብ ወራት አሜሪካ በካሬቢያን ባሕር አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን እያጠናከረች የመጣች ሲሆን አደገኛ ዕፅ ሲያዘዋውሩ ነበር ያለቻቸው ጀልባዎች ላይ በወሰድችው እርምጃ 100 ሰዎች ተገድለዋል።

አሜሪካ እኒህ ጀልባቸው አደገኛ ዕፅ ስለመጫናቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ ይፋ አላደረገችም።

የትራምፕ መንግሥት ጀልባዎቹ ላይ በወሰደው እርምጃ ምክንያት ከኮንግረስ ጫና እየደረሰበት ይገኛል።

አሜሪካ የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ካርቴል ዴ ሎስ ሶሌስ የተባለ ድርጅትን ይመራሉ የሚል ክስ ብታቀርብም ፕሬዝደንቱ ይህን ያስተባብላሉ።

በዓለማችን በርካታ የነዳጅ ክምችት በመያዝ አንደኛ የሆነችው ቬንዙዌላ ከነዳጅ ሽያጭ በምታገኘው ገቢ ላይ ጥገኛ ናት።