ኤርትራዊው ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞች ማቆያ ማዕከል ውስጥ ሕይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፉዐድ ሰይድ አብዱልካዲር የተባለ ሰነድ አልባ ስደተኛ በአሜሪካ ፔንሲልቬኒያ እስር ቤት ውስጥ ሳለ መሞቱን የአሜሪካ የስደት እና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት (አይስ) አስታወቀ።
የ46 ዓመቱ ኤርትራዊ በወንጀል ውስጥ ተሳትፎ እስር ቤት መግባቱን ተከትሎ ከአገር እንዲባረር በመወሰኑ ፊሊፕስበርግ በሚገኘው ሞሻኖን ቫሊ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ታስሮ ነበር።
ኤርትራዊው ስደተኛ ሕይወቱ ያለፈው ታኅሣሥ 5/2018 ዓ.ም መሞቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የሞቱ ምክንያት ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ፉዐድ በማዕከሉ ውስጥ ሳለ የደረት ሕመም እንዳጋጠመው ተገልጿል።
በተቋሙ ውስጥ የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች እርዳታ አድርገውለት ወደ ሆስፒታል የወሰዱት ቢሆንም ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም ተብሏል።
የፔንሲልቬኒያ ግዛት ፖሊስ እና ክሊርፊልድ ካውንቲ በሞቱ ምክንያት ዙሪያ ምርመራ እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል።
ፉዐድ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የተወለደ ኤርትራዊ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 30/2018 የአሜሪካ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቷል።
እስካሁን ድረስ የአሜሪካ ዜግነት ለማግኘት ስለመጠየቁ የሚያሳዩ መረጃዎች የሉም።
ሚያዝያ 3/2024 የሰሜን ኦሃዮ አካባቢ ፍርድ ቤት ፉዐድ በቀረበበት የማጭበርበር እና የስርቆት ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኘው የ21 ወራት እስር ፈርዶበታል።
ፉዐድ በእነዚህ ወንጀሎች እስከ 10 ሺህ ዶላር የሚደርስ ኪሳራ አድርሷል ተብሏል።
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 23/2024 ሕገወጥ ስደተኞችን ከአገር የሚያስወጡ የአሜሪካ የስደት እና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት (አይስ) ሠራተኞች ፉዐድ የታሰረበት ማረሚያ ቤት በመሄድ ካገኙት በኋላ ከአገር እንዲባረር በመወሰን ወደ ሞሻኖን ቫሊ ማቆያ ማዕከል ተዛውሯል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት አንድ የአፍጋኒስታን ስደተኛ በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ አባላትን በጥይት ተኩሶ አንዷን ከገደለ እና ሌላኛውን ካቆሰለ በኋላ የትራምፕ አስተዳደር በሕገወጥ ስደተኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ቀጥሏል።
ይህንን ተከትሎም የትራምፕ አስተዳደር አፍጋኒስታናውያንን ጨምሮ የበርካታ አገራት ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ ሂደት በማቆም የሕገወጥ ስደተኞችን ቁጥር የሚገድብ ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።
በዚህም የአሜሪካ መንግሥት ኤርትራን እና ሶማሊያን ጨምሮ ከ19 አገሮች የመጡ ስደተኞች የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ላይ ዳግም ፍተሻ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በተጨማሪም ከሁሉም አገራት የሚቀርቡ የጥገኝነት ማመልከቻዎችን ላልተወሰነ ጊዜ ያገደ ሲሆን፣ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ከሦስተኛ ዓለም አገር" በሚመጡ ስደተኞች ላይ "ዘላቂ እገዳ" ለመጣል ማቀዳቸውን ይፋ አድርገዋል።
ይህንን ተከትሎም የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የተለያዩ ወንጀሎችን የፈጸሙ እና "በጣም አደገኛ ስደተኞች" ተብለው የሚታሰቡ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ግለሰቦችን ዝርዝር አውጥቷል።
የትራምፕ አስተዳደር ከአሜሪካ ለማስወጣት እያሳደደ ያለው በስደተኞች ችሎት ከአሜሪካ እንዲወጡ የተወሰነባቸው ስደተኞች ሆነው፣ በተጨማሪም በወንጀል ወይንም በሌላ ጉዳይ የሚፈለጉ ግለሰቦችን ናቸው።
አስተዳደሩ ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሞከረ ያለው ጥገኝነት ጠያቂዎች የወንጀል መዝገብ ላይ ስማቸው የሰፈሩትን ጭምር ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ሰነድ አልባ ስደተኞችም ቢሆኑ በፍርድ ቤት ከአገር እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ብቻ ከአገር አስወጣለሁ ሲል መናገሩን የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኤርትራ ጨምሮ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ናቸው ባሏቸው የአስራ ሁለት አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ የሚያደረጉትን ጉዞዎችን የሚከለክል ትዕዛዝ መፈረማቸውን ይታወሳል።















