አሜሪካ በሶሪያ በሚገኘው አይኤስ ላይ "ከባድ" ድብደባ ፈጸመች

የአሜሪካ አየር ኃይል ንብረት የሆነው ኤፍ-35 ተዋጊ ጄት (ፎቶ ፋይል)

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

አሜሪካ በሶሪያ ውስጥ በሚገኘው የኢስላሚክ ስቴት ቡድን (አይኤስ) ላይ "ከፍተኛ ጥቃት" መፈፀሟን ገለጸች።

የአሜሪካ ጦር ኃይል ድብደባውን የፈጸመው አይኤስ በወታደሮቹ ላይ ለፈጸመው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በሚል መሆኑን አስታውቋል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) ተዋጊ ጄቶች፣ ሄሊኮፕተሮች እና መድፎች "በማዕከላዊ ሶሪያ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ከ70 በላይ ዒላማዎችን መምታታቸውን" አስታውቋል።

ከዮርዳኖስ የሚነሱ የጦር አውሮፕላኖች በጥቃቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ ተብሏል።

በጥቃቱ የአይኤስ መሠረተ ልማቶች እና የጦር መሣሪያ ማከማቻዎች ናቸው የተባሉ ቦታዎች ትኩረት እንደተደረገባቸው እና "ከ100 በላይ ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ" መዋላቸው ተነግሯል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ ታህሳስ 13 በፓልሚራ ከተማ ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች እና አንድ አስተርጓሚ የተገደሉበትን የአይ ኤስ ጥቃት ተከትሎ በቡድኑ ጠንካራ ይዞታዎች ላይ "በጣም ከባድ ጥቃት እየሰነዘርን ነው" ብለዋል።

በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በኢንዶ-ፓስፊክ የሚገኙ የአሜሪካን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚመራው ሴንቴኮም በኤክስ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ኦፕሬሽን ሃውኬይ ስትራይክ አርብ ዕለት ምሽት መጀመሩን አስታውቋል።

የሴንቴኮም አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር "በቀጠናው ውስጥ አሜሪካውያንን እና አጋሮቻችንን ለመጉዳት የሚሞክሩ አሸባሪዎችን ያለማቋረጥ ማሳደዳችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በበኩላቸው "የጦርነት መጀመሪያ አይደለም፤ የበቀል ማሳያ ነው" ብለዋል።

"በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ አሜሪካውያንን ዒላማ ካደረግክ የቀረውን አጭርና በጭንቀት የተሞላ ሕይወትህን ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታድንህ፣ እንደምታገኝህ እና ያለ ርህራሄ እንደምትገድልህ እያወቅክ ትኖራለህ።"

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር "ዛሬ ጠላቶቻችንን አድነናል፤ ገድለናል። ብዙዎቹን። እና ደግሞ እንቀጥላለን" ሲሉ አክለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ አሜሪካ "ቃል እንደገባሁት በገዳይ አሸባሪዎች ላይ ከባድ የበቀል እርምጃ እየወሰደች ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም የሶሪያ መንግሥት "ሙሉ በሙሉ ድጋፍ እያደረገ ነው" ሲሉ በጽሑፋቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዩኬ የሚገኘው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ቡድን በራቃ እና በዴይር ኢዝ ዞር ከተሞች አቅራቢያ የሚገኙ የአይኤስ መገኛዎች ዒላማ መሆናቸውን ተነግሯል።

አንድ ታዋቂ የአይኤስ መሪ እና በርካታ ተዋጊዎች መገደላቸውንም ቡድኑ ጨምሮ ገልጿል።

አይኤስ በይፋ አስተያየት ያልሰጠ ሲሆን ቢቢሲ የጥቃቱ ዒላማዎችን ማረጋገጥ አልቻለም።

ሴንቴኮም ቀደም ሲል በፓልሚራ በአሜሪካ ወታደሮች ላይ የተፈጸመው ጥቃትን ያደረሰው በአይኤስ ታጣቂ መሆኑን ገልጾ "በተኩስ ልውውጥ ወቅት ተገድሏል" ብሏል።

በጥቃቱ ሌሎች ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች የቆሰሉ ሲሆን የፔንታጎን ባለሥልጣናት ድርጊቱ የተፈጸመው "የሶሪያ መንግሥት ቁጥጥር በማያደረግበት አካባቢ" እንደሆነ ተናግረዋል።

የሶሪያ ሰብዓዊ መብቶችን የሚከታተለው ቡድን ግን አጥቂው የሶሪያ የጸጥታ ኃይሎች አባል መሆኑን ተናግሯል።

እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ቡድን የለም። ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ማንነትም ይፋ አልተደረገም።

የአሜሪካ አየር ኃይል ባልደረባ በኤፍ-15 ተዋጊ ጄት ላይ መሣሪያ ሲገጥም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ አየር ኃይል ባልደረባ በኤፍ-15 ተዋጊ ጄት ላይ መሣሪያ ሲገጥም

እአአ በ2019፣ በአሜሪካ የሚደገፈው የሶሪያ ተዋጊዎች ጥምረት አይኤስ በሶሪያ የሚቆጣጠረውን የመጨረሻውን ግዛት እንዳጣ አስታውቋል፤ ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቡድኑ አንዳንድ ጥቃቶችን ፈጽሟል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ቡድኑ አሁንም በሶሪያ እና ኢራቅ ከ5,000 እስከ 7,000 የሚደርሱ ተዋጊዎች አሉት።

የአሜሪካ ወታደሮች እአአ ከ2015 ጀምሮ በሶሪያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ይህም በአይኤስ ላይ ለሚደረገው ዘመቻ ሌሎች ኃይሎችን ለማሰልጠን ይረዳል።

ሶሪያ በቅርቡ አይኤስን ለመዋጋት ዓለም አቀፍ ጥምረቱን የተቀላቅላለች ሲሆን ከአሜሪካ ጋር ለመተባበርም ቃል ገብታለች።

በኅዳር ወር የሶሪያ ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ ዶናልድ ትራምፕን በዋይት ሐውስ ባገኙበት ወቅት ጉብኝታቸው ለሁለቱ አገራት "አዲስ ዘመን" መምጣቱን አመላካች ነው ብለዋል።