በሻር አል-አሳድን ከሥልጣን ያስወገደው አማጺ ቡድን መሪ አቡ መሐመድ አል-ጃውላኒ እንዴት እዚህ ደረሰ?

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሶሪያ አማጽያን መሪ የሆነው አቡ አሕመድ አል-ጃውላኒ ከጂሃዲስት ንቅናቄ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳቋረጠ ይናገራል።
ትክክለኛ ስሙ አሕመድ አል-ሻራ ነው። በይፋዊ ሰነዶች ላይ ይህንን ስም መጠቀም ጀምሯል።
እውነተኛ ስሙን መጠቀም የጀመረው ፕሬዝዳንት በሻር አል-አሳድ ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ነው።
ትክክለኛ ስሙን መጠቀም ተቀባይነቱን ለመጨመር የሚያደርገው ጥረት አካል ነው።
የሚመራው ታጣቂ ቡድን ሃያት ታህሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) የሶሪያ መዲና ደማስቆን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞችን ተቆጣጥሯል።
በውስጡ የተለያዩ አማጺ ቡድኖችን ይዟል። አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል መቆጣጠራቸውንም አስታውቀዋል።
ጃውላኒ ባለፉት ዓመታት የአቋም ለውጥ አሳይቷል።
ለሕዝብ በሚያደርጋቸው ንግግሮች እና በቃለ ምልልሶቹ ለውጡን ማየት ይቻላል።
ከጂሃዲስት አለባበስ ይልቅ የምዕራባውያን አለባበስ ሲመርጥም ይስተዋላል።
ለመሆኑ አል-ጃውላኒ ማነው? ለምንስ ተለወጠ?
ጃውላኒ ከአይኤስ እና ከኢራቅ ጋር የነበረው ትስስር
እአአ በ2021 ከፒቢኤስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ጃውላኒ በ1982 ሳዑዲ አረቢያ መወለዱን ገልጿል።
አባቱ የነዳጅ መሃንዲስ ነበሩ።
በ1989 ወደ ሶሪያ ተመልሰዋል።
ጃውላኒ ያደገው በደማስቆ በሚገኘው ሚዜህ አካባቢ ነው።
የጂሃዲስትነት ጉዞው የተጀመረው በኢራቅ ሲሆን፣ በኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) በኩል ከአል-ቃይዳ እና ከኢስላሚክ ስቴት ኢራቅ (አይኤስአይ) ጋር ትስስር ነበረው።
በ2003 በአሜሪካ መሪነት በኢራቅ ላይ ወረራ ተፈፀመ።
በ2005 ጃውላኒ በቡካ ካምፕ ታስሮ ነበር። ከጂሃዲስት ኃይሎች ጋር የነበረው ትስስሩ የጠነከረው በዚህ ወቅት ነበር።
ኋላ ላይ የአይኤስ መሪ ከሆነው አቡ በከር አል-ባግዳዲ ጋር ተዋውቋል።
በ2011 ጃውላኒ ወደ ሶሪያ ሄዶ አል-ኑስራ ግንባርን እንዲመሠርት አል-ባግዳዲ ላከው።
በ2012 ይህ ቡድን በሶሪያ ዋነኛ ተዋጊ ሆኖ ነበር። ከአይኤስ እና ከአል-ቃይዳ ጋር ያለው ትስስር ግን ይፋ አልሆነም።
በ2013 የአል-ባግዳዲ ቡድን አይኤስአይ ከአል-ኑስራ ጋር ተጣምሮ ኢስላሚክ ስቴት ኦፍ ኢራቅ ኤንድ ዘ ሌቫንት (አይኤስአይኤልእና አይኤስአይኤስ) ይመሥረት ሲል ትስስራቸው ታወቀ።
ጃውላኒ ግን አይኤስአይ ከሚፈጽመው የጭካኔ ድርጊት መራቅ ስለፈለገ ተነጣጠሉ።
ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት የፈጠረውም ለዚህ ነበር። ኑስራ ግንባርን የአል-ቃይዳ የሶሪያ ክንፍ አደረገው።
የአይኤስ ቡድን ከሚፈጽማቸው ድርጊቶች ራሱን ለመነጠል ይፈልግ ነበር። ዋነኛ ግቡም በሶሪያ ተቀባይነት ማግኘት ሆነ።
የጂሃድ አካሄድን በተለየ መንገድ ነበር የሚተረጉመው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከአል-ቃይዳ ጋር ጥምረት
በአውሮፓውያኑ 2013 አል-ኑስራ ግንባር የአል-ቃይዳ የሶሪያ ክንፍ ሲሆን፣ ከአይኤስ ጋር ያለው ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ወደቀ።
ጃውላኒ ይህንን የወሰነው ከሶሪያ ድጋፍ ላለማጣት ነበር። ሆኖም ግን ከአል-ቃይዳ ጋር መጣመር እምብዛም ለውጥ አላመጣም።
አል-ኑስራ በ2015 ኢድሊብ እና ሌሎች ግዛቶችን ሲይዝ ሌሎች ቡድኖችም ከእሱ ጋር መጣመር ጀመሩ።
የአማጺ ቡድኑ የመጀመሪያ ስም ጃባት ፋታህ አል-ሻም ነበር። ከዚያም በ2017 መጠሪያው ሃያት ታህሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) ሆኗል።
አል-ቃይዳ ጃውላኒ ክህደት እንደፈፀመበት ይናገራል። በዚህ ክፍፍል ሁራስ አል-ዲን የተባለ የሶሪያ የአል-ቃይዳ ክንፍ ተፈጥሯል።
በ2020 ይህንን ቡድን ኤችቲኤስ አስወግዶታል። የቡድኑ አባላት ግን አሁንም በቀጣናው ይገኛሉ።
ኤችቲኤስ በኢድሊብ ያለውን የአይኤስ እንቅስቃሴም ዒላማ አድርጓል። "ከአክራሪነት የመውጣት" ፕሮግራሞ ያካሂድም ነበር።
ጃውላኒ በዚህ መንገድ ታጣቂ ቡድኖችን ለማዋሀድ ሞክሯል። እርስ በእርስ የሚደረግ ሽኩቻን በመቀነስ በሶሪያ እንዲሁም በአማጺ ቡድኑ ውስጥ ታዋቂነቱ እና ተደማጭነቱ ጎልቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቡድኑ ከአል-ቃይዳ ጋር ተለያይቶ ስሙን ቢለውጥም የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎችም አገራት አሸባሪ ቡድን ብለው ፈርጀውታል።
ጃውላኒ ያለበትን ለሚጠቁም አሜሪካ 10 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት የገባችው ቃልም እስካሁን ባለበት ይገኛል።
ቡድኑ ያሳየው ለውጥ የታይታ ነው ብለው ምዕራባውያን ያምናሉ።
በኢድሊብ 'መንግሥት' ምሥረታ
ኤችቲኤስ በጃውላኒ ሥር አራት ሚሊዮን ደገማ በሚኖርባት የሶሪያ ከተማ ኢድሊብ ዋነኛ ኃይል ሆነ።
አካባቢው በወታደራዊ ኃይል ቁጥጥር ሥር ነው የሚለውን ስጋት ለማስወድ ጃውላኒ የሲቪል ግንባር ፈጥሯል።
በ2017 ይህንን ግንባር ሲሪያን ሳልቬሽን ገቨርንመንት (ኤስጂ) ብሎታል። የወታደራዊ ኃይሉ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ክንፍም ሆኗል።
ኤስጂ እንደ መንግሥት መዋቅር ነበር የሚንቀሳቀሰው። ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች ሚኒስትሮችም በጤና፣ በትምህርት እና ሌሎችም ዘርፎች ተመድበዋል።
አስተዳደሩ የእስላማዊ ሕግን በመከለተል ሸሪዓን ይተገብራል።

የፎቶው ባለመብት, Salvation Government
ጃውላኒ ከሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ፣ የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ካምፕን በመጎብኘት እንዲሁም በ2023 የመሬት መንቀጥቀጥ ሲነሳ የውጭ አገራትን እርዳታ በማሰባሰብ ገጽታውን መገንባት ጀመረ።
ኤችቲኤስ በአስተዳደር እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ለውጥ በማሳየት መረጋጋትን መፍጠር እንደሚችል አሳየ።
ታሊባን በ2021 ወደ ሥልጣን ሲመለስ ለቡድኑ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
ጂሃዲስት እንቅስቃሴን ከፖለቲካ ጋር በማጣመር እና ግብን በመምታት ረገድ ታሊባንን እንደ አርዓያ እንደሚመለከትም ኤችቲኤስ አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Salvation Government
ጃውላኒ በኢድሊብ ያሳየው አመራር ጂሃድን በስፋት ተግብሮ መምራት እንደሚችል የሚጠቁም ነበር።
ለመረጋጋት፣ ለሕዝብ አገልግሎት እና ለመልሶ ግንባታ ቅድሚያ በመስጠት ኢድሊብን እንደ ምሳሌ አሳይቷል።
የራሱን የፖለቲካ ሕልም በማሳካት እና የቡድኑን ተቀባይነት በማስፋት ረገድም አካሄዱ ጠቅሞታል።
ሆኖም ግን በጃውላኒ አመራር ሥር ኤችቲኤስ ሌሎች ታጣቂ ቡኖችን አስወግዷል፤ አግልሏልም።
እነዚህ ቡድኖች ጂሃዲስት እና ሌሎችም አማጺያን ናቸው። እነዚህን በማስወገድ ኤችቲኤስ የኃይል ይዞታውን አጠናክሯል።
ኤችቲኤስ የገጠመው ተቃውሞ
አማጺ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ጥቃት እስከሚከፍትበት ጊዜ ድረስ ጃውላኒን የሚቃወሙ ሰልፎች ይካሄዱ ነበር።
ተቃውሞዎቹ የመጡት ከእስላማዊ ንቅናቄዎች እና ከሶሪያ የመብት ተሟጋቾች ነበር።
አስተዳደሩን ከአሳድ አምባገነናዊ አገዛዝ ጋር ያነጻጸሩትም አሉ።
የአሳድ አስተዳደር እንደሚያደርገው አማጺ ቡድኑም ተቃዋሚዎችን ያፍናል በሚል ይተቻል።
ተቃዋወሚዎች ኤችቲኤስን 'ሻቢሀ' ሲሉ ይጠሩታል። ይህ ቃል የሚገልጸወ ለአሳድ ታማኝ የሆኑ ቡድኖችን ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኤችቲኤስ ከመንግሥት ኃይሎች፣ ከተገለሉ ጂሃዲስቶች እና የውጭ ኃይሎች ጋር ውጊያ የማያደርገው ዓለም አቀፍ ገጽታውን ለመጠበቅ ነው ሲሉ ተቃዋሚዎች ይተቻሉ።
ኤችቲኤስ በቅርቡ ጥቃት መፈጸም ሲጀምር፣ የተቃዋሚዎች ጥያቄ የነበረው ቡድኑ በኢድሊብ ሐሳባቸውን በመግለጻቸው ያሰራቸውን ሰዎች እንዲፈታ ነበር።
ኤችቲኤስ የሚቀርብበትን ትችት መነሻ አድርጎ ለውጦችን አሳይቷል።
በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚከሰስ የደኅንነት ቡድኑን አስወግዷል፣ አልያም በድጋሚ አዋቅሯል።
ዜጎች ቡድኑን በተመለከተ ቅሬታ የሚያሰሙበት አሠራርም ዘርግቷል።
ኤችቲኤስ በአንድ አስተዳደር ሥር መዋቀር ለውጥ የሚያመጣ እና የሶሪያን መንግሥት የሚገረስስ እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቷል።
ኤችቲኤስ እና የሲቪል ክንፉ የሆነው ኤስጂ ዘመናዊነታቸውን ለማሳየት ሞክረዋል። በዚህም አገሬው እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳመን ጥረዋል።
የእስላማዊ እንቅስቃሴ ማንነታቸውን ጠብቀው ነው የዘለቁት። በዚህም ደስተኛ የሆኑ ደጋፊዎች አሏቸው።
በ2023 በመገበያያ ማዕከል ፌስቲቫል መካሄዱን 'ከሞራል ያፈነገጠ' ብለው ቡድኑን የተቹ ነበሩ።
በፓራሊምፒክ መነሻ የሆነ ክንውን መካሄዱም ያላስደሰታቸው ቡድኖች ኤችቲኤስ አካሄዱን እንዲያጤን አሳስበዋል።
እነዚህ አጋጣሚዎች ኤችቲኤስ እስላማዊ አካሄዱን ነጻነትን ከሚሻው ከሶሪያ ሕዝብ ጥያቄ ጋር እንዴት አጣጥሞ መቀጠል ይችላል? በሚለው ላይ ጥያቄ ያጭራሉ።
አዲስ መንገድ
ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን አሁን ላይ ያተኮረው የጃውላኒ ጂሃዲስት መነሻ ላይ ነው። አንዳንድ አማጽያን ትግሉ እንዳይቀለበስ በሚል ከኃላፊነት እንዲነሳ ይጠይቃሉ።
ቡድኑን አክስሞ ከሥልጣን እንደሚወርድ ከዚህ ቀደም የተናገረ ቢሆንም፣ አሁን በሕዝብ አደባባይ የሚታየው አካሄዱ ይህንን ፍላጎት አያንፀባርቅም።
ዕድሉን እየተጠቀመበት ነው ብለው የሚተቹት ቢኖሩም እንኳን፣ ኤችቲኤስ አማጺያንን አስተባብሮ መላው አገሪቷን መቆጣጠር መቻሉ ጃውላኒን ጠንካራ አድርጎታል።
ጃውላኒ እና ኤስጂ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እምነት እንዲጥልባቸው ማስተማመኛ እየሰጡ ነው።
በሶሪያ ላሉ እና የተገለሉ አናሳ ቡድኖች ደኅንነታቸው እንደሚጠበቅ ቃል ገብቷል። እንደ ሩሲያ ላሉ ጎረቤት አገራት በሰላም መፍትሄ መፈለግን አማራጭ አድርጎ አቅርቧል።
ሩሲያ በሶሪያ ያላት ወታደራዊ መቀመጫ ባለበት እንደሚቀጥል ጃውላኒ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኤችቲኤስ ከ2017 ወዲህ 'ለዘብተኛ ጂሃዲስት' እየሆነ መምጣቱን የሚያሳዩ ነጥቦች ናቸው።
ጃውላኒ እየተከተለ ያለው አካሄድ እንደ አይኤስ እና አል-ቃይዳ ያሉ ግትር ቡድኖች የሚያራምዱት ዓለም አቀፍ የጂሃድ ንቅናቄ መዳከም እንዲሁም ዘላቂነት ማጣት ማሳያም ይሆናል።
ሌሎች ቡድኖችም የእሱን የለውጥ መንገድ እንዲከተሉ ሊያነሳሳ ይችላል።
የተሻለ የፖለቲካ አካሄድ ያለው ጂሃድን በማቀንቀን ከተለመደው አካሄድ የተለየ መንገድን የሚያሳይ አልያም ደግሞ ፖለቲካዊ ውጤት እስከሚገኝ ድረስ የተወሰደ አማራጭ ሊሆን የሚችልበትም ዕድል አለ።












