ከሥልጣን የተወገዱት የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሻር አል አሳድ ወደ ሞስኮ ኮበለሉ- የሩሲያ ሚዲያዎች

የበሻር አል አሳድ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሥልጣን በኃይል የተወገዱት የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሻር አል አሳድ እና ቤተሰባቸው በሩሲያ ባለሥልጣናት ጥገኝነት ከተሰጣቸው በኋላ ሩሲያ መግባታቸውን የክሬምሊን ምንጭን ዋቢ አደርገው የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሩሲያ ለአሳድ እና ለቤተሰባቸው "በሰብዓዊነት" በመመርኮዝ ጥገኝነት ሰጥታለች ሲሉ የሩሲያ የዜና ወኪሎች ኢንተርፋክስ፣ ቲኤስኤስ እና ሪያ ኖቮስቲ ስማቸው ያልጠቁሱትን ምንጭ በመጥቀስ ዘግበዋል።

እሁድ ማለዳ የሶሪያ ታጣቂዎች መዲናዋን ደማስቆን ተቆጣጥረው የአሳድ መንግሥት መገርሰሱን ከገለጹ በኋላም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ያሉበትን ማወቅ አልተቻለም ነበር። ታጣቂዎቹ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው ባልተጠበቀ ሁኔታ ግስጋሴያቸውን ጨምረው መብረቃዊ በሆነ ሁኔታ ሶሪያን የተቆጣጠሩት።

የቢቢሲ የሩሲያ አገልግሎትን ጨምሮ በርካታ ምንጮች እንደዘገቡት አል አሳድ በሶሪያ ከሚገኘው ላታኪያ ከተባለው የሩሲያ የጦር ሰፈር በተነሳ የሩሲያ አውሮፕላን ከአገር ሳይወጡ እንዳልቀሩ መዘገባቸውን አልጀዚራ አስፍሯል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አል አሳድ የት እንዳሉ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ነገር ግን "ሞስኮ ውስጥ አለ ይባላል" ሲሉ በዋይት ሐውስ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ገልጸዋል።

"የአገዛዙ ውድቀት መሠረታዊ የፍትህ እርምጃ ነው። ለረጅም ጊዜ በጭቆና ሲሰቃዩ ለነበሩ የሶሪያ ሕዝቦች በሚኮሩበት አገራቸው የተሻለ ወደፊትን ለመገንባት ታሪካዊ ዕድል ነው" ብለዋል ባይደን።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት ቀደም ብሎ አል አሳድ ሥልጣን መልቀቃቸውን እና ከሶሪያ መውጣታቸውን አስታውቆ ነበር።

ታጣቂዎቹ አል አሳድ ከአገር ፈርጥጠዋል ብለዋል ካወጁ በኋላ ሕዝቡ የቀድሞውን መሪያቸውን ቤት ዘርፈዋል።

አማጺያኑ "የደማስቆ ከተማ ነጻ ነች" ማለታቸውን ተከትሎም በርካቶች ደስታቸውን በጎዳናዎች ላይ ሲገልጹ እና ሲጨፍሩ ታይተዋል።

የሩሲያ የዜና ወኪሎች በተጨማሪም ሥልጣን የተቆጣጠሩት የሶሪያ ታጣቂ አመራሮች በአገራቸው ለሚገኙ የሩሲያ ጦር ሰፈሮች እና ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮኖች ደኅንነት ዋስትና መስጠታቸውን ዘግበዋል።

"የሩሲያ ባለሥልጣናት ከታጣቂዎቹ የሶሪያ ተወካዮች ጋር እየተነጋገሩ ነው። የታጣቂዎቹ አመራሮች በሶሪያ ግዛት በሚገኙ በሩሲያ ወታደራዊ ማዕከላት እና የዲፕሎማቲክ ተቋማት ደልንነት ዋስትና ሰጥተዋል" ሲል ታስ የተሰኘው የዜና ወኪን የክሬምሊንን ምንጭ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ሩሲያ በሶሪያ ጦርነት በንቃት የተሳተፈች ሲሆን፣ ለአልሳድ ወግና በታጣቂዎቹ ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃቶችን ፈጽማለች እንዲሁም ለሰላማዊ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆናለች ተብላ ትከሰሳለች።

ታጣቂዎቹ በአውሮፓውያኑ 2015 የአልአሳድን ሥልጣን ስጋት በጣሉበት ወቅት የሩሲያ ድጋፍ የጦርነቱን አቅጣጫ ቀይሮታል። በፍጥነት እየገሰገሱ የነበሩትን ታጣቂዎችን በመግፋት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል እንዲወሰኑ አድርጓቸው ነበር።

የእሁዱ ክስተት ከ13 ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ሲሆን፣ ለአምሳ ዓመታት የቆየውን የአል አሳድ ቤተሰብ አገዛዝ እንዲያከትም አድርጎታል።

የሶሪያ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 2011 ሲነሳ በአል አሳድ ላይ በአብዛኛው ያልታጠቀ ሕዝባዊ አመጽ ሆኖ ነበር የጀመረው።

ነገር ግን በመጨረሻም ከእርስ በርስ ጦርነት አልፎ የተለያዩ የውጭ አገራት ኃይሎች የተሳተፉበት እንዲሁም በመቶ ሺዎችን ሕይወት የቀረጠፈ እና ሚሊዮኖችን ወደተለያዩ አገራት እንዲሰደዱ አድርጓል።