የፋኖ ኃይሎች "ሰላይ ናቸው" ያሏቸውን ሦስት ሴቶች መግደላቸውን የታጣቂዎቹ አመራር አረጋገጡ

በደብረ ኤልያስ ወረዳ የተገደሉት ሦስት ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Mengistu Amare/facebook

የምስሉ መግለጫ, በታጣቂዎቹ ሰላይ ናቸው በሚል የተገደሉት ሦስቱ ሴቶች

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ በሚገኘው ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሦስት ወጣት ሴቶች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ተገድለው ተገኙ።

ድርጊቱ መፈጸሙን ለቢቢሲ ያረጋገጡት የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ማዕከላዊ ኮማንድ አባል አስረስ ማረ ዳምጤ፤ ሦስቱ ሴቶች "ለጠላት ሲሰልሉ በመገኘታቸው እርምጃ መወሰዱን" በመጥቀስ እርምጃውን ተከላክለዋል።

የደብረ ኤልያስ ወረዳ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ግድያው የተፈጸመው "የቀን ሥራ ላይ" ተሰማርተው በነበሩ ሴቶች ላይ እንደሆነ እና ከመካከላቸው አንዷ "የመስማት ችግር ያለባት" እንደሆነች በመግለጽ ታጣቂዎችን ከስሰዋል።

ከ17 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሦስት ሴቶች ከደብረ ኤልያስ ከተማ ወጣ ብሎ ባለ "ጥጃ ጎጠር መገንጠያ" የተባለ አካባቢ ተገድለው የተገኙት ማክሰኞ ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም. እንደሆነ የወረዳው የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ደምስ አለኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወረዳው የፀጥታ ኃይሎች ሦስቱን የሴቶች አስከሬን ያገኙ ከነዋሪዎች በደረሳቸው ጥቆማ እንደሆነ የወረዳው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሙላት ሙንዬ ገልጸዋል። ሙላት እንደሚናገሩት አስከሬኖቹ የተገኙበት ቦታ "በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ያለ" ነው።

"[አካባቢው] ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ነው። ታጣቂዎች የያዙት አካባቢ ነው። [...] እዚያ የሚተላለፍ ሰው 'ሦስት ልጆች ተመትተው ወድቀዋል፤ ጭንቅላታቸውን ነው የተመቱት' የሚል ጥቆማ ሲደርስ የፀጥታ ኃይል ሄዶ፣ አስከሬናቸውን አምጥቶ፣ ለቤተሰቦቻቸው አስረክቦ እንዲቀበሩ ተደርገዋል" ብለዋል።

ይህንኑ የሚያጠናክሩት የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊው ደምስ በበኩላቸው፤ ሦስቱ ሴቶች "በጥይት ተደብድበው" እንደተገደሉ አስረድተዋል። "የተለያየ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች ፈጽመውባቸዋል" ሲሉም ወንጅለዋል።

ወሲባዊ ጥቃት መፈጸሙ እንዴት እንደተረጋገጠ ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊው፤ "ሐኪሞችን ይዘን ሄደን ነበር። ከዚያ በኋላ የተፈጸመ ድርጊት ካለ በሚል ነበር አስቀድመን ይዘናቸው የሄድነው። ይዘናቸው ከሄድን በኋላ ያለውን ናሙና ወሰዱ፣ ልጆቹን ከፋፍነው አነሱ። ከዚያ በኋላ ሲታይ እንደዚህ ዓይነት ነገር እንደፈጸሙባቸው ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት" ብለዋል።

የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሙላት እንደሚናገሩት የሟቾቹ ማንነት የታወቀው "በመታወቂያቸው" አማካኝነት ነው።

ከሟቾቹ አንዷ የሆነችው ሙያነሽ ተሾመ "የ17 ዓመት" ታዳጊ እንደነበረች የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊው ደምስ ተናግረዋል። ትህትና (ቃልኪዳን) አለኸኝ እና መልካም ታዴ የተባሉት ሁለቱ ሟቾች ደግሞ "18 እና 19" ዓመታቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ሦስቱ ሴቶች ላይ የተፈጸመው ግድያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የፌስቡክ ገጾች ባጋሩት ልጥፍ ነው።

በአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል "ቴዎድሮስ ዕዝ 206ኛ ኮር የሕዝብ ግንኙነት" ስም ፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ጽሁፍ "የጠላትን ተልዕኮ ተቀብለው ለዘጠኝ ወራት መረጃ ሲያቀብሉ በነበሩ ባንዳዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን" ይገልጻል።

በደብረ ኤልያስ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Debre Elias Woreda Communication

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"የፋኖ ካምፕ አለበት በተባለበት ሁሉ እየተዘዋወሩ መረጃ ሲያቀብሉ እንደነበር" በማለት የሚከስሰው የፌስቡክ ልጥፍ፤ "በሕዝቡ ለደረሰው የሕይወት፣ የሀብት እና የንብረት ጉዳት ተጠያቂ" ናቸው በማለት ይወነጅላል። በዚህም ምክንያት "'ሌሎችን ያስተምራል' በማለት በተጠርጣሪዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ወስዷል" ይላል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለተሠራጨው ይህ መረጃ ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ማዕከላዊ ኮማንድ አባል አስረስ ማረ ዳምጤ የጉዳዩን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል።

ሦስቱ ሴቶች "ካለፈው የክረምት ወር ጀምሮ ለረጅም ጊዜ የስለላ ሥራ ሲሠሩ ነው የቆዩት" በማለት የሚከስሱት አስረስ፤ ይህንንም ያደረጉት "በቀን ሠራተኛነት ሽፋን" ነው ይላሉ።

"ይህንን የስለላ ሥራቸውን ሪፖርት የሚያደርጉት በአካባቢው ላሉት የሚሊሻ እና የመከላከያ እንዲሁም የአድማ ብተና አመራሮች መሆኑ በሚገባ የተረጋገጠ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ የፋኖ አመራሩ ገለጻ፤ ሦስቱ ሴቶች የተያዙት "ወታደራዊ ሥልጠና ከሚወስዱ ምልምሎች ጋር በመመሳሰል በሥልጠናው ቦታ ሥልጠና የሚወስዱ መስለው ለምዝገባ በቀረቡበት ወቅት በታየባቸው የሰላይነት ምልክት" የተነሳ ነው።

"ያንን ተከትሎ በተደረገ ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራዎች ተደርገዋል ይጠቀሙባቸው የነበሩ ስልኮችን፣ የነበራቸውን እንቅስቃሴ፣ እነማን ተልዕኮ እንደሰጧቸው ጭምር እነሱም አምነዋል" ብለዋል።

"በተለይ ደግሞ ጅበላሙ ተራ የሚባል ሻለቃ ላይ ጉዳት እንዲደረስ ደምባ፣ አንገታም ጃንተከል እና ሊባኖስ የተባሉ ቀበሌዎች ላይ መረጃ ሲያጣሩ እንደነበር ከራሳቸውም አንደበት ተረጋግጧል፤ ከሌሎች መረጃ ከተቀበሏቸው ሰዎችም ተረጋግጧል፣ ከያዟቸው የግንኙነት መሳሪያዎችም ጭምር ተረጋግጧል" በማለት ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደብረ ሊባኖስ ወረዳ አመራሮች ግን ወጣቶቹ ሴቶች የስለላ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር መባሉን አይቀበሉትም።

የወረዳው የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት እንዲሁም የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች፤ ግድያው የተፈጸመው "ሰሊጥ የመሰብሰብ ሥራ ላይ ተሰማርተው በነበሩ የቀን ሠራተኞች" ላይ እንደሆነ በመግለጽ የታጣቂዎቹን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል።

ከሟቾቹ አንዷ የሆነችው ትህትና ዘመድ እና የወረዳው ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ዘውዱ ደምስም በተመሳሳይ፤ "እንኳ ተልዕኮ ልትቀበል፤ ከመንግሥት አካል ማን ምን እንደሆነ አታውቅም" ሲሉ ይከራከራሉ። ሌላኛዋ ሟች መልካም ታዴም "የቀን ሠራተኛ እና ሻይ ቤት ነው የምትሠራው" ይላሉ።

በታጣቂዎች ፌስቡክ ላይ በተለቀቀው ቪዲዩ ላይ ዘመዳቸው የሆነችው ሟች ስማቸውን በመጥቀስ "የፀጥታ ኃይል፣ አስተባባሪ" እንደሆኑ መናገሯን ያነሳሉ።

"እኔ ደግሞ ሥራዬ ከፖለቲካው ጋር የሚያገናኘኝ ሳይሆን የመንገድ ትራንስፖርት ኃላፊ ነኝ" የሚሉት አቶ ዘውዱ፤ በቪዲዮው ላይ ይህንን የተናገረችው በተፈጸመባት "ድብደባ ምክንያት ነው" ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።

በደብረ ኤልያስ ወረዳ የተገደሉት ሶስት ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Mengistu Amare/facebook

"ድብደባ ደርሶባታል፣ ብዙ መከራ አይታለች፣ ተደብድባለች፣ ተቀጥቅጣለች፣ በወሬ ደረጃ ከአንድ ወር ከሁለት ሳምንት በላይ ታስራለች። [...] የምታውቀኝ እኔ ስለሆንኩ ዘውዱ ብላ 'ተልዕኮ ተሰጥቶኝ ነው፤ እንዲህ ነው' የሚል መልዕክት አስተላልፋለች " ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሁለቱ የወረዳ አመራሮችም በተመሳሳይ የተወነጀሉበትን ድርጊት ያመኑት "ድብደባ ተፈጽሞባቸው ነው" የሚል መከራከሪያ አንስተዋል።

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ማዕከላዊ አመራሩ አስረስ ማረ ዳምጤ በበኩላቸው በሦስቱ ሴቶች ላይ "ድብደባ እና ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሟል" በሚል ቀረበውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።

"የፋኖን ስም ለማጥፋት የአገዛዙ ሰዎች የሚናገሩት ነገር ነው እንጂ ሐሰተኛ ነው" የሚሉት አስረስ፤ በአካባቢው ከሚገኘው ሕዝብ "መካከል መርጠን እነዚህ [ሦስት ሴቶች] ላይ እርምጃ ልንወስድ የምንችልበት አንዳችም የተለየ ምክንያት የለም" ሲሉ ተከላክለዋል።

"የደረሰባቸውም የፆታ ጥቃት የለም። ቃለ ምልልሱንም ሰጡት በነጻነት፤ ያለ ምንም አስገዳጅነት የተሰጠ መረጃ ነው። ሠራዊቱ በተለየ ሁኔታ እነሱ ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚያደርስበት፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ እነሱ ላይ እርምጃ የሚወስድበት ሌላ ምክንያት የለም" በማለት መከራከሪያቸውን አጠናክረዋል።

አስረስ "ስለላ ላይ ተሰማርተዋል" በማለት የሚከስሷቸውን ሴቶች "እንደ ተዋጊ ኃይል" እንደሚቆጥሯቸው ተናግረዋል።

"በሕገ ደንባችን መሠረት ለጠላት ስለላ ሥራ ሲሠራ የተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ የሞት ቅጣት እርምጃ እንደምንወስድ፣ ሌላም አካባቢ ተመሳሳይ እርምጃዎችን እንደምንወስድ ይታወቃል" ብለዋል።

በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች ላይ ግድያን መፈጸም እንደ የጦር ወንጀል ድርጊት ሊቆጠር የሚችል ስለመሆኑ ጥያቄ ቀረበላቸው የፋኖ አመራሩ አስረስ "ምርኮ የተያዘ ሰው፤ በተኩስ ልውውጥ መሃል በፈቃደኝነት እጁን የሰጠ ሰው ሲሆን ነው። ይሄኛው ግን በልዩ ሁኔታ የስለላ ሥራ ሲሠሩ ስለሆነ በቁጥጥር ስር ዋሉት፤ በሕገ ደንባችን መሠረት እንደ ምርኮኛ የሚያዙ አይደሉም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

"በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት እና ምርኮኛ አያያዝ ሕግ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የሚጥስ ነው ብለን አናምንም" ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።