የአማራ ክልል ግጭት፡ "ልጆቼ እንደ እኔ ሳይማሩ እንዳይቀሩ ነበር ስታገል የነበረው፤ መላም የለው"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ህልሟ ሐኪም መሆን ነበር።ለዚያም ነበር ትምህርቷን ተግታ ስትማር የነበረው።
እንያት* የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እየተከታተለች የነበረው ከምትኖርበት እና በምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ ከምትገኘው አነስተኛ መንደር በእግር የሁለት ሰዓት መንገድ በመጓዝ ነበር።
ይህ አላማረራትም፤ በዚህ ሁኔታ አልፋ ስምንተኛ ክፍልን ተሻግራለች። አሁን ግን ቤት ከዋለች ሦስተኛ ዓመቷን ይዛለች።
እያደር ይሻል ይሆን በሚል ተስፋ ወደ ትምህርቷ የምትመለስበትን ጊዜ ብትጠባበቅም ጭራሽኑ እየባሰ እንደመጣ ትናገራለች።
በዚህም ምክንያት ለትምህርቷ ቅድሚያ በመስጠት ገፍታው የነበረውን ጋብቻ ያለ ዕድሜዋም ቢሆን እየተመኘችው ነው።
"ታዲያ ካልተማርኩ ምን እሰራለሁ? ምን መላ አለው ? ሁሉም ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል" ትላለች።
ይህ የእርሷ ዕጣ ብቻ አይደለም። ታናናሾቿም ምንም እንኳን በአቅራቢያቸው ትምህር ቤት ቢኖርም ደጁን ከረገጡ ሦስተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል።
ደብተር እና ብዕራቸውን ትተው ከብት ሲጠብቁ ነው የሚውሉት።
በአካባቢው በድንገት የሚከሰተው ተኩስ እና ግጭትም የሕፃን ነፍሳቸውን ያሸብረዋል። በሰማይ ላይ የሚበር ነገር ሁሉ የሚጥልባቸው አንዳች ነገር ያለ ይመስላቸዋል።
በመንግሥት ውትወታ በአቅራቢያቸው ያለው ትምህርት ቤት ተከፍቶ መምህራን በግዳጅ እንዲያስተምሩ ቢደረግም ተማሪዎቹም ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ፣ ወላጆቻቸውም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ አልደፈሩም።
እንያት እንደምትለው ትምህርት ቤቶቹ አጠገብ ወታደሮች ሰፍረዋል።
"ሕፃናት ይማሩ የሚባለው እዚያው ወታደሮቹ በሰፈሩበት አጠገብ ነው። ወደ ከተማ ሄደን እንዳንማር እዚያም ሰላም የለም ነው የሚባለው።የሰዎች መታገትን ስንሰማ እንፈራለን" ትላለች።
እንያትን ጨምሮ የአራት ልጆች እናት የሆኑት አንቺንአሉ* "ወታደሮች መሣሪያ ይዘው በተጠጉበት ትምህርት ቤት ሕፃናት መንፈሳቸው ሳይረበሽ እንዴት ደርሰው ይመጣሉ?" ሲሉ ይጠይቃሉ። በድንገት የሚከሰተው ግጭትም አላስተማምን ብሏቸዋል።
በአንድ ወቅት ያጋጠማቸውን ክስተትም ያስታውሳሉ።
"ልጆቻችንን ትምህርት ቤት ላክን፤ ወዲያው ግን ድንገት ግጭት ተከሰተ። ልጆችም ወደ እናታቸው፤ እናቶችም ወደ ልጆቻችን መሮጥ ያዝን።ሁላችንም መንገድ ላይ ልንቀር ነበር" ይላሉ።
ከዚያ ወዲህ ደፍረው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ መምህር በበኩላቸው በአማራ ክልል፣ በተለይ ግጭት በበረታባቸው አካባቢዎች ትምህርት ከተቋረጠ ዘንድሮ ሦስተኛ ዓመቱን መያዙን ይናገራሉ።
በዚህም ምክንያት ሕፃናት እና ታዳጊዎች ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለያለዕድሜ ጋብቻ፣ ለወሲባዊ ብዝበዛ ተዳርገዋል ይላሉ።
መምህሩ እንደሚሉት በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የወታደሮች እና የታጣቂዎች 'ሚስት' የሆኑ እንዲሁም ወደ ከተማ በመሄድ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ አሉ።
ወንዶቹም በክልሉ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን አሊያም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን ለመቀላቀል እንደተገደዱ ጠቅሰዋል።
የፌደራል መንግሥት የክልሉን ልዩ ኃይል እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በ2015 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ግጭት አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠሉ እየተነገረ ነው።
ግጭቱ ከቀጠፈው የሰው ሕይወት እና ካደረሰው የንብረት ውድመት ባሻገር ማኅበራዊ፣ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሏል።
በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ አስከፊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የክልሉ መንግሥት ገልጿል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ መስከረም ላይ ባጋራው መረጃ በ2018 ዓ.ም. 7. 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢያቅድም ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉት 3.48 ሚሊዮን ተማሪዎች መሆናቸውን አስታውቋል።
ቢሮው በተደጋጋሚ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ጥሪ ቢያቀርብም ያቀደውን ማሳካት አልቻለም።
ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ባለመመለሳቸው ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች እየተደረጉ መሆኑንም ቢሮው አክሏል።
ዓለም አቀፉ የሕፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ባወጣው ሪፖርት ላይም በአገሪቱ ያለውን መፈናቀል፣ ጥቃት እና ግጭትን ጨምሮ በበርካታ ምክንያቶች 9 ሚሊዮን ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ገልጿል።
ከዘጠኝ ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ወይም 20 በመቶ የሚሆኑ የአገሪቷ ትምህርት ቤቶች በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት መውደማቸውንም ሪፖርቱ ጠቅሷል።
በተለይ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያለው ሁኔታ የከፋ ሲሆን በእነዚህ ሥፍራዎች ሕፃናት ለጉልበት ሥራ፣ ለያለዕድሜ ጋብቻ እና ለብዝበዛ መዳረጋቸውን አመልክቷል።
"አስተምረን ውጤቱን አላገኘው ስንል ተስፋ ቆረጥን"
አንችንአሉ አልተማሩም። የትምህርት ቤትን ደጅ ረግጠው አያውቁም።በልጅነታቸው ነው ተድረው የልጆች እናት የሆኑት። አሁን የአራት ልጆች እናት ናቸው።
ሁለቱ መዋዕለ ሕፃናት፣ አንዱ ሦስተኛ ክፍል፣ አንዷ ደግሞ ዘጠነኛ ክፍል ደርሰው ነበር።
"እኔ 'መሃይም' ሆኜ ቀረሁ ሳያስተምሩኝ። እነሱን ለማስተማር እየደከምኩ ነበር። እንዲህ ሆነው ቀሩ። ምን መላ አለው?" ይላሉ ተስፋ በራቀው አንደበታቸው።
በልጆቻቸው ተስፋ ነበራቸው።
"ልጆቼ ተምረው፤ ከዚያም ሥራ ይዘው፤ ሁሉን ነገር ያውቁልኛል በሚል የምችለውን እያደረኩ ነበር" ይላሉ።
የበኩር ልጃቸው እንያትም "ያንች መክሰልና መጥቆር ይበቃል። ተምሬ ሥራ እይዛለሁ።ካልተቻለ ነግጄ እተዳደራለሁ" ስትል ነበር የሚመጡላትን የጋብቻ ጥያቄዎች ወደ ጎን ብላ ትምህርቷ ላይ የበረታችው።
አሁን ግን ልጆችም ወላጆችም ተስፋቸው የተሟጠጠ ይመስላል።
"አስተምረን አስተምረን ዳር ሳይደርሱ ሲቀሩ ከባድ አይደለም ወይ? ምን እናድርግ ?" ሲሉም ይጠይቃሉ አንችንአሉ።
ልጃቸው ጠዋት ማታ ለምትጠይቃቸው ጥያቄም መልስ አጥተዋል።ዓመታት እየተቆጠሩ በመጡ ቁጥር ደግሞ ተስፋቸው እየተመናመነ መጥቷል።
"ይህን ያህል ተምሬ አሁን ምን ልሁን፣ ያለ አንድ ሥራ ተቀምጨ ምን ልሁን?" የእንያት የዘወትር ጥያቄ ነው።
ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የጉልበት ብዝበዛ፣ የወሲብ ንግድ . . .
አንችንአሉ የልጆቻቸው ቤት መቅረት እጅጉን ያሳስባቸዋል።
አንጻራዊ ሰላም ወዳለበት ከተማ ልከው ለማስተማር አልመው የነበረ ቢሆንም ይህም ግን የሚያረጋጋ ሆኖ አላገኙትም።በከተማም ሰላም እንደሌለ እና ጥቃት ደረሰ ሲባል ነው የሚሰሙት።
ከዚህም ባሻገር ገበያ በሄዱ ቁጥር ምፅዋት የሚጠየቁበት የእገታ ክስተትም በልጆቻቸው ይደርስ ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው።
"እዚሁ አጠገባችን ይሻላል ብለን እንጂ ቤትም ሆኖ ሰላም የለም" ይላሉ አንችንአሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ድንገት በሚከሰቱት ግጭቶች ምክንያት የግብርና ሥራ፣ ከብት ጥበቃ አሊያም የዕለት ተዕለት መደበኛ ክንውንን ለመፈፀም አዳግቷል።
በአካባቢያችን ሁሉም ልጅ ይማር ስለነበር ከብት የምንጠብቀው ወላጆች ነበርን የሚሉት አንችንአሉ፣ አሁን ግን ይህንን ሥራ የሚሠሩት ልጆች መሆናቸውን ይናገራሉ።
እንያት እንደምትለውም ይህንን ኃላፊነት ለመወጣትም አስቸጋሪ ነው።
"የሚወረወረው [ድሮን] ስለሚጣል ብዙ ጊዜ በር ዘግተን ነው የምንቀመጠው" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Enarge communication info
በክልሉ የትምህርት መስተጓጎል አብዝቶ የሚያሳስባቸው መምህር እንደሚሉት በተለይ በገጠሩ አካባቢ በመንግሥት ወታደሮች እና በፋኖ ታጣቂዎች ካምፕ ሆነው የሚያገለግሉ ትምህርት ቤቶች አሉ።
ቢቢሲ ይህንን ያላረጋገጠ ሲሆን መንግሥትም ሆነ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን በዚህ ላይ ያሉት ነገር የለም።
ሆኖም ሰላማዊ ሰዎች የሚገለገሉባቸውን መሠረተ ልማቶች ለጦር ካምፕነት መጠቀም እንዲሁም በእነርሱ ላይ ጥቃት ማድረስን በተመለከተ እርስ በርሳቸው ሲካሰሱ ይሰማል።
ከአንድ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአገሪቱ ከ5500 በላይ ትምህርት ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆናቸውን ገልጾ ነበር።
ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል አብዛኞቹ በአማራ ክልል እንደሚገኙ የጠቀሰው ኮሚሽኑ፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ከወደሙት በተጨማሪ በትጥቅ ግጭት ውስጥ ባሉ አካላት የጦር ካምፕ ሆነው እያገለገሉ ነው ብሏል።
የኮሚሽኑ የሴቶች፣ የሕጻናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገ/ሐዋሪያ በወቅቱ ለቢቢሲ ሲናገሩ የተማሪዎች ለዓመታት ከትምህርት ገበታ መራቅ እያደረሰ ያለውን ኪሳራም አንስተዋል።
"ለሦስት፤ አራት ዓመታት ትምህርት ቤት ያልገቡ ተማሪዎች አሉ። ከሕይወታቸው ላይ ይህን ያህል ዓመት እንደመስረቅ ነው። ይህንን ዓመት አንመልስላቸውም። በትውልድ ላይም እየሆነ ያለው ነገር ትክክል አይደለም። እንደ አገርም በጣም ትልቅ ነገር እያጣን ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው መምህርም የተማሪዎች ከትምህርት መራቅ ወደ ፊት የከፋ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
"ሴት ልጆች ያለ ዕድሜያቸው እየተዳሩ ነው፣ አንዳንዶች ደግሞ ወደ ከተማ በመሄድ በወሲብ ንግድ ላይ እየተሰማሩ ነው፤ ሕፃናት በቤት ውስጥ ሥራ የጉልበት ብዝበዛ እየደረሰባቸው ነው" ሲሉም የታዘቡትን አጋርተዋል።
ይህንን እንያት እና አንችንአሉም ያስረግጣሉ።
በእነርሱ አካባቢ በርካታ ሴት ልጆች ያለ ዕድሜያቸው እንደተዳሩ እና ሕፃናትም በሰው ቤት በከብት እረኝነት ተቀጥረው ለመሥራት እንደተገደዱ ተናግረዋል።
እንያት የእርሷን እና የሌሎች እኩዮቿን ህልም ያጨለመው ግጭት ቆሞ ፊቷን ወደ ትምህርቷ መመለስ ትፈልጋለች።
*ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው የተለወጠ















