ከቁጥር ባሻገር፡ ነዋሪውን ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ያለው የሁለት ዓመቱ የአማራ ክልል ግጭት

- ፀሐፊ, በካሳዬ ዳምጤ
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ አማርኛ
ሁለት ዓመታትን ሊደፍን የተቃረበው የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት ባለፉት ሳምንታት መባባሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ። የመንግሥት ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውንም እየገለጹ ነው።
የአገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ክፍል የሆነው የአማራ ክልል ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነትን የቋጨው ፊርማ ሳይደርቅ ያዝ ለቀቅ በሚል ግጭት እየታመሰ ይገኛል።
ከሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰው የአማራ ክልል ግጭት ከነጠቀው ሕይወት ባሻገር ነዋሪዎች መራር መከራ እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በክልሉ ውስጥ ከፍርድ ውጪ ግድያ፣ በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ ከሕግ ውጪ እስራት፣ አስገድዶ ስወራ፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ እንደሚፈፀም ይገልፃሉ።
በክልሉ በግጭቱ ምክንያት ከደረሰው ውድመት ለማገገም 10 ቢሊዮን ዶላር መልሶ ማቋቋሚያ እንደሚያስፈልገው መንግሥት በቅርቡ አስታውቋል።
ምንም እንኳ ለ10 ወራት የዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም. ቢያበቃም ክልሉ በሕግ ባልተራዘመ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (De facto State of Emergency) ስር እንደሚገኝ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ የክልሉን ቀውስ ሲገልጹ "ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ" ይሉታል።
በክልሉ የዕለት ተዕለት እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የተገደበ ሲሆን፤ የትምህርት እና የሕክምና አገልግሎቶች መስተጓጎልን ጨምሮ ማኅበረሰቡ በስጋት ኑሮውን እንዲገፋ ተገዷል።
ባለፉት ስድስት ወራት 148 እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ እንዲሁም 70 ሰዎች ደግሞ በወባ በሽታ ሕይወታቸው ማለፉን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።
4.2 ሚሊዮን ተማሪዎች ወይም 60 በመቶ የክልሉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ የራቁ ሲሆን፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ይናገራሉ።
በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ከሐምሌ 2015 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም. ድረስ ከአምስት ሺህ በላይ ሴቶች ተደፍረው ወደ ሕክምና ተቋማት መምጣታቸውን ገልጿል። አሃዙ ግን ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል።
በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የግጭቱ ዳፋ ያልገባበት ጓዳ፤ ያልነካው ሕይወት ማግኘት ከባድ እንደሆነ ነዋሪዎች ያነሳሉ።
"ሞት ይሻላል"
ጥንታዊቷ የላሊበላ ከተማ ቅርሶችን ለመጎብኘት በሚመጡ ምዕመናን እና እንግዶች ያሸበረቀብ ከተማ ነበረች።
ቱሪዝም ለከተማዋ የደም ስር ነው። አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በቱሪዝም ይተዳደራል።
ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ይህ ገፅታዋ ጥላ ያጠላበት ሲሆን፤ በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ የተቀሰቀሰው ግጭት ደግሞ ይበልጥ ከተማዋን ወና በማድረግ የብዙዎችን ጉሮሮ እንደዘጋ አስጎብኚዎች እና ነዋሪዎች ይናገራሉ።
"[ቱሪዝም] ምንም የለም ማለት ይቻላል። አሁን ሁሉም ነገር ዝግ ነው" ሲሉ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን መበተናቸውን የሚናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ቱሪዝምን ማዕከል አድርገው ኑሯቸውን የመሠረቱ ሰዎች መተዳደሪያ እንደሌላቸው ይገልፃሉ።
"እንቅስቃሴው ቆሟል ማለት ይቻላል። የከተማዋ ነዋሪ፤ አስጎብኚው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል" የሚሉት 165 አስጎብኚዎችን ያቀፈው የቅዱስ ላሊበላ አስጎብኚ ማኅበር ሊቀ መንበር አቶ እስታሉ ቀለሙ ወቅቱን "የመከራ ጊዜ" ይሉታል።
ከ15 ዓመታት በላይ በአስጎብኚነት የሠሩት እና የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ፀጋዬ "ተስፋ አስቆራጭ ነው። የሰው ልጅ ቆሞ ሲሄድ በልቶ የሚያድር ይመስላል። ወጥቼ ስገባ ባለቤቴ [ገንዘብ] ስጠኝ ትላለች። ከየት አመጣለሁ? ዝም ብሎ መናቆር ነው" በማለት ያሉበትን ሁኔታ ሲገልፁ "ሞት ይሻላል" ይላሉ።
"ኑሮ መሮኛል። የልጆቼ ጉዳይ ሆኖብኝ ነው እንጂ መኖር አልፈልግም። አሁን ሞት ይፈለጋል" በማለት ተስፋ ስለመቁረጣቸው ተናግረዋል።
ለሌሎችም እንተርፍ ነበር የሚሉት አስጎብኚዎች ካለፈው ዓመት ወዲህ ግን እርዳታ ፍለጋ እጃቸውን ለመዘርጋት እንደተገደዱ የሚያነሱት አቶ እስታሉ "ስሜት ይጎዳል፤ ሞራልን ይነካል" ይላሉ።
የደረሰባቸውን ችግር "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" የሚሉት አቶ ፀጋዬ ግጭቱ ባስከተለው የኑሮ ውድነት "የተገኘው ገንዘብ እንኳን ምንም መግዛት አልችል አለ። የኑሮ ውድነቱ በጣም ጦፏል" ሲሉ ዳፋውን ይገልፃሉ።
ሌላ የላሊበላ ከተማ ነዋሪም በታሪካዊቷ ከተማ ያለውን ሁኔታ "ከአቅም በላይ ነው፤ ሰው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ነው" ይላሉ።
"ሌላው ቀርቶ የመንግሥት ሠራተኛውም ፆም አዳሪ ነው። የከተማው [ላሊበላ] አስተዳደር ቢጨንቀው ለእፎይታ አንዳንድ ምርቶችን እያመጣ በዱቤ እያከፋፈለ ነው" ሲሉ ግጭቱ በኑሮ ላይ ያሳረፈውን ጫና ገልፀዋል።
ላሊበላ ተደጋጋሚ ግጭቶች የሚካሄዱባት ከተማ ስትሆን፤ ከአንድ ጊዜ በላይ ከተማዋ እና አየር ማረፊያው በፋኖ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በመግባት በረራዎችም ተስተጓጉለዋል።
የከተማዋ ዋነኛ መለያ የሆኑት አብያተ ክርስቲያናት በከባድ መሳሪያ ንዝረት እና ፍንጣሪ ስጋት እንዳደረባቸው የሃይማኖት አባቶች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ላሊበላ ከተማ ከኑሮ መሠረቱ አንፃር የባሰበት ሆነ እንጂ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ኑሮ መራር እንደሆነ ይነገራል።
ጥር 2016 ዓ.ም. በመንግሥት ኃይሎች የጅምላ ግድያ በተፈፀመባት መርዓዊ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ወርሃዊ ደሞዛቸው ሦስት ሺህ ብር መሆኑን በመግለፅ "ለመኖር እየተንገዳገድን" ነው ይላሉ።
የጤፍ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ስለመጨመሩ የሚናገሩት የስድስት ልጆች አባት፤ መሠረታዊ የሸቀጦች ዋጋ መናር ኑሮን የማይገፋ እንዳደረገው ጠቁመዋል።
ክልሉን በቅርበት የሚከታተሉ እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ "አንድ ሸቀጥ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር ወይም ጎንደር የሚደርስ ከሆነ በየቦታው የመንግሥት ሚሊሻዎችም ሆኑ ታጣቂዎች በሚጥሏቸው ቀረጦች [ምክንያት] ነጋዴው ዋጋ እየጨመረ ነው" ይላሉ።
አንድ የባሕር ዳር ከተማ ነጋዴ "እንደ በፊቱ እንደተፈለገው እቃ ማስመጣት የለም። [ምርት] አንድ ወር፤ ሁለት ወር ሊቆይ ይችላል። መንገድ ላይ ሊቆም ይችላል፤ ሊታገት ይችላል። ይህን ታሳቢ አድርገን ነው የምንሸጠው" ሲሉ ይገልፃሉ።
በዚህ ውጣ ውረድ መሀል ግብር እና የኮሪደር ልማት መዋጮን ጨምሮ በመንግሥት የሚጠየቁ ክፍያዎች ሕይወትን ከድጡ ወደ ማጡ ስለማድረጋቸውም ይነሳል።
አስገዳጅ ያልነበረው የጤና መድኅን ክፍያ በክልሉ ግዴታ ሆኖ በእጥፍ ክፍያ እየተሰበሰበ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የኑሮ ጫናው ይበረታባቸዋል የሚባሉት የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይም የፋኖ ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ለወራት ደሞዛቸው እንደሚቋረጥባቸው ይናገራሉ።
መምህራን በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሽኩቻ መሀል መውደቃቸውን በመጥቀስም በደሞዝ መቆራረጥ ምክንያት የቤት እቃዎቻቸውን ሳይቀር እየሸጡ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
በፋኖ ኃይሎች በተያዙ አካባቢዎች የባንክ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፤ በእነዚህ አካባቢዎች የባንክ አካውንት የከፈቱ ሰዎች ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው እንኳ ገንዘባቸውን ማውጣት እንደማይችሉ ይገልፃሉ።
መንግሥት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ደግሞ "የፋኖ ቤተሰብ" በሚል ነዋሪዎች ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ከማገግ ጀምሮ ጥቃት እና ዛቻ እንደሚደርስባቸው የሚናገሩ አሉ።
በዚህ የሕይወት ውጣ ውረድ መሀል ደግሞ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎች ክልሉን የእንባ ምድር እንደሆነ በክልሉ ተለያዩ ክፍል ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ።
የእሳት እራት የሆነችው የአራት ወር ጨቅላ
ቀኑ ረቡዕ ኅዳር 25/2017 ዓ.ም. ነው። ንጋት ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ።
ከባድ መሳሪያ ከተማዋን ሲያናጋት ነዋሪው ከቤት መውጣት አልቻለም። ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት ሁሉ አልጋቸውን ጨምሮ ባገኙት ስርቻ ውስጥ መደበቅ ጀመሩ።
አምስት አባላት ያሉት የአቶ ደመቀ* ቤተሰብም ይህኑ ነው ያደረገው። ተራማማ በሆነው ቅምቦ (ቸርች) በተባለ ሰፈር መኖራቸው ደግሞ ስጋቱን ከባድ አድርጎታል። በሚኖሩበት አካባቢ የከባድ መሳሪያ አረር እየወደቀ ነበር።
በቤቱ ውስጥ የነበረችው አራስ እናት የአራት ወር ጨቅላ ልጇን ይዛ ከሌሎች ቤተሰቦቿ ጋር አልጋ ስር ገብታ ተደብቃለች።
በድንገት ቤታቸው ላይ ከባድ መሳሪያ ወደቀ።
"03፡00 አካባቢ ድብልቅልቅ [አለ]። ከባድ መሳሪያ በጣራ ገባ። የቤቱን እንጨት ጥሶ. . . ወረደ። ቀጥታ [መሳሪያው] መሬት ላይ ሲያርፍ ቤቱ ጭስ በጭስ ሆነ፤ መተያየት አልቻልንም። እሪ ሲሉ ያለቁ ነው የመሰለኝ" በማለት ቅፅበቱን ያስታውሳሉ።
አቶ ደመቀ ከነበሩበት ተነስተው ቤተሰቦቻቸው የተደበቁበት ቦታ ሲሄዱ ስጋታቸው እውን ሆኖ አገኙት።
የአራት ወሯ ጨቅላ ህፃን በእናቷ እቅፍ ላይ ሳለች ባልጠነከረ የራስ ቅሏ ላይ በደረሰባት ጉዳት ሕይወቷ ወዲያው ማለፉን ይናገራሉ።
"ወዲያው ነው ፀጥ ያለችው" ይላሉ አቶ ደመቀ። በህፃኗ ጭንቅላት የገባው "ብርጭቆ ያክላል" ያሉት ብረት (አረር) ለሞቷ ምክንያት ሆኗል።
ይህ ሲሆን ግን ራሳቸው መጎዳታቸውን አላወቁም ነበር። እሳቸውን ጨምሮ የህፃኗ እናት ልጇን ያቀፈችበት ክንዷ ቆስሏል።
ሙሉዓለም የሚል ስም የወጣላት ጨቅላዋ በእናቷ እና በቤተሰቦቿ በቁልምጫ "ማሚዬ" ትባላለች።
ነሐሴ 27/2016 ወደዚህ ምድር የመጣች ነፍስ ኅዳር 25/ 2017 ዓ.ም. በከባድ መሳሪያ የእሳት እራት ሆናለች።
"[የህፃኗ እናት] ውስጧ በጣም ስለተጎዳ አታወራንም። ከዚያ ወዲህ ዝምታ ታበዛለች። እንደተከፋች እና ውስጧ እንደተጎዳ [አውቀናል]" የሚሉት የቤተሰብ አባሉ፤ በዚህም ምክንያት ቤተሰቦቿን ሳትሰናበት ጠፍታ ወደ አረብ አገር መሰደዷን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የአስፈላጊነት እና ተመጣጣኝነት መርሆችን ባላከበሩ የከባድ መሳሪያ እና የድሮን ጥቃቶች ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ተገድለዋል ብሏል።
የፋኖ ኃይሎች ጥቃት ፈጽመው ከወጡ በኋላም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚደርስ 'የበቀል በትር' በስፋት ሪፖርት ተደርጓል።
"[የመንግሥት ኃይሎች] ጥቃት ሲደርስባቸው አካባቢው ላይ ያገኙትን መምታት [መግደል] አለ። ብዙ ቦታ ተመሳሳይ ጥቃቶች አሉ" ሲሉ አንድ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ ይናገራሉ።
ክልሉን ለአምስት ዓመታት ያህል ያስተዳደሩት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው (ዶ/ር) "አብዛኛው የአገሪቱ ጦር በአሁኑ ወቅት የሚገኘው በአማራ ክልል ነው። አየር ኃይሉም፣ ምድር ኃይሉም፣ ኮማንዶ እና ልዩ ኃይል የሚባለውም፣ ፌደራል ፖሊስ እና የክልል ልዩ ኃይሎች በየጊዜው እየተጨመረ በክልሉ ወታደራዊ አገዛዝ የሰፈነበት እና ከፍተኛ ውድመት እየደረሰበት ነው" ሲሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቶችን እንደሚሰነዝሩ ይገልፃሉ።
የክልሉ ማኅበረሰብ በሁሉም አቅጣጫ "መከራ" ውስጥ መሆኑን የሚያነሱት የሰብዓዊ መብት ባለሙያው፤ "አንድን ወረዳ ታጣቂዎች ይዘዋት ቆይተው የመከላከያ ኃይል ሲገባ እነ ማን ከነማን ጋር ምን ያደርጉ ነበር? [በሚል] ሕይወትን የሚያስከፍል እርምጃ ይወሰዳል" በማለት እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎች በሁለቱም ወገኖች እንደሚፈጸሙ ይገልፃሉ።
የፋኖ ታጣቂዎች በተለይም የአካባቢ አመራሮችን እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው የሚሏቸውን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶቹን እንደሚፈጽሙ ይነገራል።
ባለፈው ኅዳር መጨረሻ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ከ30 በላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መግደላቸውን የዓይን እማኞች እና የአካባቢው አስተዳደር ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።
የአማራ ፋኖ በጎጃም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ማርሸት ፀሐዩ "በየወረዳው፤ በየዞኑ ያሉ ካድሬዎች በቀጥታ ከመከላከያ ጋር ተጠርንፈው እኩል ተዋጊ ነው የሆኑት።. . . ከእኛ ጋር ፊት ለፊት ነው የገጠሙት። እነሱ እኛን ሲያገኙ እርምጃ እንደሚወስዱ ሁሉ እኛም እነሱን ስናገኝ እርምጃ እንወስዳለን" ይላሉ።
የእናት ምጥ እና የቤተሰብ ጭንቀት
በአማራ ክልል የጤና መዋቅር 100 የመንግሥት ሆስፒታሎች፣ 923 ጤና ጣቢያዎች፣ 3,725 ጤና ኬላዎች፣ 882 አምቡላንሶች እና ከ1,500 በላይ የግል የጤና ተቋማት ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጤና ተቋማት ጉዳት ስላጋጠማቸው በክልሉ ያለው የጤና አገልግሎት ተናግቷል።
በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ባዘጋጀው ሰነድ ከሐምሌ 2015 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም. ድረስ 969 የጤና ተቋማት ጉዳት እና ዝርፊያ ተፈፅሞባቸዋል። ከአንድ ሺህ የሚበልጡ የጤና ባለሞያዎች ደግሞ ሥራቸውን ለቀዋል፣ ወደ ሌላ አካባቢ ተዘዋውረዋል አሊያም በግጭቱ ተገድለዋል።
የድሮን ጥቃትን ጨምሮ የጤና ተቋማት የጥቃት ኢላማ ከመሆናቸው ባለፈ የጤና ባለሙያዎች "ፋኖን ታክማላችሁ" በሚል ጥቃት እና ዛቻ እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።
ከዚህ ባሻገርም በመድኃኒት እና የሕክምና ግብዓት እጥረት እንዲሁም በእንቅስቃሴ ላይ በሚጣል ገደብ እና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ታካሚዎች ያለ ሕክምና እየቀሩ ነው ይላሉ።
ጥቂት የማይባሉ አምቡላንሶች በመንግሥት ኃይሎች አሊያም በታጣቂዎች እጅ ውስጥ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ።
በሰሜን ጎጃም ዞን ውስጥ በሚገኝ ጤና ጣቢያ የሚያገለግሉ አንድ ባለሙያ በወረዳቸው አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩ ስድስት አምቡላንሶች ውስጥ አሁን አንድ አምቡላንስ ብቻ አገልግሎት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ገዱ (ዶ/ር) ርዕሰ መስተዳደር እያሉ ጤና ላይ በተለይም በወሊድ የሚከሰት የእናቶችን እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ አንድ ወረዳ ከአምስት እስከ ስድስት አምቡላንሶች እንዲኖሩት መደረጉን በማንሳት፤ "አሁን አብዛኞቹን መከላከያ ነው የሚገለገልባቸው" ሲሉ ይከሳሉ።
በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ነፍሰ ጡር የሆኑት ወ/ሮ ብዙወርቅ* ሕክምና በጊዜ ባለማግኘታቸው የጨቅላ ልጃቸው ሕይወት አልፏል።
ምጥ ሲጀምራቸው አካባቢያቸው ወደ ሚገኝ ጤና ጣቢያ ሄደው ተቋሙ ማዋለድ ባለመቻሉ 'ሪፈር' ቢላቸውም በአፋጣኝ መሄድ አልቻሉም ነበር።
"ከመሸ አይኬድም፤ አጉል ሰዓት ሆነ" ሲሉ በአካባቢው ያለውን የደኅንነት ስጋት ያነሳሉ።
ሁለተኛ ልጃቸውን ለመገላገል ከሦስት ቀናት ምጥ በኋላ ሆስፒታል ቢደርሱም "እንኳን ማሪያም ማረችሽ" ለመባል ግን አልበቁም።
"'[ሐኪሞቹ] ቶሎ መጥተሽ ቢሆን [ልጁ] ምንም አይሆንም ነበር። አሁን ተጎዳሽ፤ ልጁም ተጉዳ' አሉኝ። . . . ከሆዴ ውስጥ ሲወጣ ድክም ብሎ ነበር እንጂ ደኅና ነበር" በማለት ልጃቸውን ያጡበትን ቅፅበት የሚያስታውሱት ወ/ሮ ብዙወርቅ፤ "ምን ይደረጋል እንግዲህ?" ይላሉ በጥልቅ ሐዘን።
"በጣም ደም እየፈሰሳት ነበር" የሚሉት ባለቤታቸው ወ/ሮ ብዙወርቅ በሕይወት በመትረፋቸው ደስታቸውን ይገልፃሉ።
በአካባቢው በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት መንገድ ሲዘጋ "ቤተሰብ በየት መጥቶ ይጠይቀን? ቀለብ ማን ያምጣልን? ተቸግርን ነበር" ሲሉ የገጠማቸውን ተጨማሪ ችግርም ይናገራሉ።

በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ በሚገኝ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚሠሩ የእናቶች እና ሕፃናት ጤና ባለሙያ በአምቡላንስ እጦት እና በደኅንነት ስጋት ምክንያት አማራጭ በማጣት እናቶች ቤታቸው እየወለዱ ነው ይላሉ።
"እንኳን በምሽት፣ በቀን ለመምጣትም ምን አለ? ተብሎ ታስቦበት፤ ተጣርቶ ካልሆነ እንዲሁ በፈለጉት ሰዓት ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱበት ሁኔታ [የለም]" የሚሉት ባለሙያው፤ በዚህም የእናቶች እና ሕፃናት ሕይወት እያለፈ ነው ብለዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት ከሆስፒታሉ በቅርብ ርቀት የሚኖሩ እና መንታ ልጆችን ያረገዙ ነፍሰ ጡር እናት ስጋት ስላደረባቸው ቤታቸው ውስጥ እንደወለዱ የሚያነሱት ባለሙያው፤ "ቤተሰቦቿ 'ሞተችብን፤ ደም ፈሰሳት' ብለው" ያለታካሚዋ ሆስፒታል እንደመጡ ያስታውሳሉ።
ቢቢሲ የተመለከተው ለክልሉ ምክር ቤት የቀረበ የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ባለፉት ስድስት ወራት 148 እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን አመልክቷል።
በመድኃኒት እጥረት እንደ ስኳር በሽታ፣ ደም ግፊት፣ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ችግር ውስጥ መግባታቸውን የሚያነሱት አንድ የጤና ባለሙያ፤ የመድኃኒት መቋረጥ በህሙማን ጤና እና ሕይወት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመጥቀስ የችግሩን ስፋት ይገልጻሉ።
ግጭቱ በጤናው ዘርፍ "ከፍተኛ" ተፅዕኖ ማድረሱን የሚያነሱት የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ክልሉ "በተወሳሰበ የሕብረተሰብ ጤና ችግር" ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
"በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር፣ ግብዓቶችን ወደ ሕብረተሰቡ ለማድረስ፣ የጤና ባለሞያዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ችግሮች አሉ" ይላሉ።
እንደ ኮሌራ እና ወባ ያሉ ወረርሽኞች የተቀሰቀሱ ሲሆን፤ ግጭቱ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር ፈተና መደቀኑን ጠቁመዋል።
"ወረርሽኞችን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር በጣም ችግር አለ። ጊዜ ይወስዳሉ፤ ይራዘማሉ። ከተራዘሙ ደግሞ ሰው ይሞታል፤ በፍጥነት ታክሞ ቶሎ እንዳይድን ይሆናል" ይላሉ።
በ2017 ዓ.ም. ስድስት ወራት 1.3 ሚሊዮን ሰዎች ወባ የተገኘባቸው ሲሆን፤ 70 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
ግጭቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ መጪው ጊዜ የሚያስፈራቸው ባለሙያዎች ወደ ኋላ እየተመለስን ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን፤ አቶ በላይ ግን ይህን ለማለት ሳይንሳዊ ጥናት ያስፈልጋል ይላሉ።
ግጭቱ ባደረሰው የደኅንነት ስጋት ምክንያት በርካታ የረድኤት ድርጅቶችም ስራቸውን አቋርጠዋል።
በክልሉ በሁለት ዞኖች ሕፃናትን ጨምሮ 200 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የጣለ ከፍተኛ የምግብ እጥረት የተከሰተ ሲሆን፤ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ በቂ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተደራሽ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
"ሁሉም ማኅበረሰብ ነው የታሰረው"
በክልሉ ታወጆ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ እና አዋሽ አርባን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች "ማንነታቸው ተለይቶ" በዘፈቀደ መታሰራቸውን የመብት ተሟጋቾች አስታውቀዋል።
አዋጁ ከተነሳ በኋላ ደግሞ በአማራ ክልል በተደራጀ መልኩ ከመስከረም 19/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከስድስት ሺህ በላይ ሰዎች "ለፋኖ ድግፍ ታደርጋላችሁ" በሚል ለወራት በዋናነት በአራት ማቆያ ጣቢያዎች ታስረዋል።
ከእነዚህ ታሳሪዎች መካከል የወሎ ዩኒቨርስቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አያሌው ታለማ አንዱ ናቸው።
እርሳቸው እና ሌሎች 13 የዩኒቨርስቲው መምህራን በሌሊት ቤታቸው በፀጥታ ኃይሎች ከተከበበ በኋላ ከኮምቦልቻ ወጣ ብሎ በሚገኝ ጮሬሳ በተባለ ወታደራዊ ካምፕ ለአምስት ወራት 'ያለ ሕግ' መታሰራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንደ አዳራሽ 100 የሚሆኑ ሰዎችን በሚይዝበት ካምፕ ከታዳጊዎች ጀምሮ እስከ ሽማግሌዎች፤ ከእናቶች ጀምሮ እስከ አካል ጉዳተኞች ድረስ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ታስረዋል።
እስረኞቹ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ሐኪሞች፣ መምህራን፣ ካህናት፣ ዳኞች፣ የባንክ ሠራተኞች እንዲሁም የመንግሥት አመራሮች እና ፖሊሶች መሆናቸውን የሚናገሩት ዶ/ር አያሌው፤ "ሁሉም ማኅበረሰብ ነው የታሰረው" ይላሉ።
እስረኞቹ ለአንድ ወር ያህል ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ "የፋኖ ተዋጊ፣ ሎጀስቲክ አቅራቢ፣ መረጃ ሰጪ እና አክቲቪስት" ተብለው በአራት ቡድኖች ተለይተው እሳቸውን ጨምሮ 200 የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም. ደሴ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ይገልጻሉ።
ያቺ ዕለት "በሕይወቴ ያዘንኩባት ቀን ናት" የሚሉት ዶ/ር አያሌው፤ "መንገድ ዘግቶ ሰው አግቶ ብር መቀበል፤ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ማቃጠል፤ ማኅበረሰቡ ልጆቹን እንዳያስተምር መከልከል. . . ድርጊቶችን በመፈፀም እና ሕገ መንግሥቱን በኃይል የመናድ ወንጀል ላይ ተሳትፈዋል" የሚል ክስ በጥቅል ቀረበብን ይላሉ ዩኒቨርስቲ መምህሩ በሐዘን።
"የጥቅል ክሱን" በግል እንዲያቀርብ የተጠየቀው ፖሊስ ዶ/ር አያሌውን "ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ አባላት ይመለምላል" ብሎ የከሰሰ ቢሆንም "በማስረጃ እጦት" ፍ/ቤት በዋስ እንዲለቁቀ ፈቅዶላቸዋል።
ነገር ግን የዋስትና መብታቸውን እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመጣስ እርሳቸውን ጨምሮ እስረኞች ከደሴ ማረሚያ ቤት በር ላይ ተወስደው ድጋሚ ስለመታሰራቸው ይናገራሉ።
እስረኞች ከእስሩ ባለፈ የባንክ ሂሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ በመዝጋት፣ ድርጅቶቻቸውን በማሸግ እና ደሞዝ በማቋረጥ ቤተሰቦቻቸው ለችግር መጋለጣቸውን "የሞት ፍርድ" ይሉታል።
የጤና ባለሙያ የሆኑት የወ/ሮ ገንዘቤ ተገኘ* ባለቤት በግል ክሊኒካቸው "ፋኖን ያክማል" ተብለው ለወራት ሲታሰሩ አራት ልጆች ያለው ቤተሰባቸው እንደተመሰቃቀለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስሩን ተከትሎ ክሊኒካቸው መታሸጉን እና የባንክ ሂሳባቸው ደግሞ እንዳይንቀሳቀስ መታገዱን ገልፀዋል።
በዚህም የክሊኒኩን ስድስት ሠራተኞ ያሰናበቱ ሲሆን፤ "ከፍተኛ ስቃይ" ደርሶብናል ይላሉ።
"ለልጄ የከፈትኩት አካውንት ውስጥ ትንሽ ብር ነበር። በዚህ ተንቀሳቀስኩ። ይቺም አለቀች" የሚሉት ወ/ሮ ገንዘቤ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ከሰዎች ለመበደር መገደዳቸውን ይገልጻሉ።
የ64 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ባለቤታቸው በእስር ቤት የሳምባ ምች (ኒሞኒያ) ታመው የነበረ ሲሆን፣ "ብቻዬን በየቦታው ስንከራተት ትልቅ ጉዳት ደርሶብኛል" የሚሉት ወ/ሮ ገንዘቤ፤ ክሊኒካቸው ሲታሸግ የላብራቶሪ ኬሚካሎች እና መድኃኒቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፎ ኪሳራ እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል።
የወ/ሮ ገንዘቤ ባለቤት እና ዶ/ር አያሌውን ጨምሮ እስረኞች ያልፍርድ ከወራት እስር በኋላ "የተሃድሶ ሥልጠና" እንዲወስዱ ተደርጎ በሦስት ዙር ተለቀዋል።
ይሁን እንጂ እስካሁን ያልተለቀቁ እና አድራሻቸው ያልታወቀ እስረኞች እንዳሉ አንድ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ ተናግረዋል።
'መጨረሻ የሌለው'
አማራ ክልል 13 ዞኖች እና በርካታ የከተማ አስተዳደሮች ያሉት ክልል ሲሆን፤ የክልሉ ሕዝብ ከ32 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ይታመናል።
በክልሉ ለሁለት ዓመት በዘለቀው ግጭት ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች የሕዝቡ የዕለት ተዕለት እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች የተገደቡ አሊያም በተፋላሚ ወገኖች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው።
በሌሊት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እንደማይችሉ የሚናገሩ አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ "የነገ ቀዳሾች ዛሬ [ቤተ ክርስቲያን] ገብተን እናድራለን" ይላሉ።
ግጭቱ "ለሥርዓት አልበኝነት" በር ከፍቷል የሚሉት አንድ የመብት ተሟጋች፤ ይህም እስርን እና ማዋከብን ጨምሮ ግድያ፣ ለገንዘብ ሲባል የሚፈጸሙ እገታዎችን እና ዘረፋዎችን አስፋፍቷል ይላሉ።
በክልሉ ግጭቱን ለመሸሽ እና ግጭቱ ከወለዳቸው ወንጀሎች ለማምለጥ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆነ ይነገራል።
"ቤቱን እየዘጋ በርካታ ሰው ሄዷል" ሲሉ አንድ የመርዓዊ ከተማ ነዋሪ ስደቱን ይገልጻሉ።
ስደቱ 'ሃብታሞች ወደ ከተማ፤ ደሃዎች ወደ ገጠር' ነው።
አዲስ አበባ እና ባሕር ዳር ለስደተኞቹ ዋነኛ የከተማ መዳረሻዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ቤተሰብ ይዞ እና ሥራ ፈትቶ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች መኖር ፈተና ስለመሆኑ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር የሺጥላ ወንድሜነህ "የአገረ መንግሥቱ አወቃቀር፣ የሥልጣን፣ የሀብት ክፍፍል፣ የውክልና ጉዳይ እና ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገው የሽግግር ሂደት የፈጠረው ተግዳሮት ነው ግጭቱን ያስነሳው" ይላሉ።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ገዱ (ዶ/ር) የፖለቲካን ጥያቄ በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት የተደረገ እንቅስቃሴ የክልሉን ቀውስ ፈጥሯል ብለው ያምናሉ።
በተለያዩ አካባቢዎች "አማራ ተኮር ጥቃቶች" እልባት እንዲሰጣቸው ጥያቄዎች በርትተው ምላሽ ሳይሰጣቸው የትግራይ ጦርነት መፈንዳቱን የሚናገሩት ገዱ፤ ይህ ጦርነትም በክልሉ ሲዛመት ጠባሳ እና ተጨማሪ ቅራኔ መፍጠሩን ይናገራሉ።
በትግራይ ጦርነት ወቅት ብቅ ያለው የፋኖ እንቅስቃሴ ምንም እንኳ አስቀድሞ በመንግሥት ቢወደስም፤ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ግን በስጋት መታየት መጀመሩን ያነሳሉ።
ስምምነቱን ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎች "ኢ-መደበኛ ኃይል" በሚል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ "ትጥቅ ማስፈታት" የተባለው እርምጃ ግን ለትጥቅ ግጭቱ መነሳት ዋነኛው ምክንያት ነው።
በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ የተደራጁት የፋኖ ታጣቂዎች "የአማራ ሕዝብን የኅልውና አደጋ ለመከላከል" ነፍጥ ማንሳታቸውን የሚናገሩ ሲሆን፣ መንግሥት በአንፃሩ "ፅንፈኛ እና ሽፍታ" በሚል ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ይገልጻል።
በአሁኑ ወቅት ክልሉ በሁለት ኃይሎች መካከል ሲሆን፤ የመንግሥት ኃይሎች ዋና ዋና ከተሞችን ሲቆጣጠሩ፤ የፋኖ ኃይሎች ደግሞ በአመዛኙ በአንዳንድ አነስተኛ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ።
በክልሉ ያለው የደኅንነት ስጋት ከነዋሪው አልፎ የአካባቢ አመራሮች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር በካምፕ እንዲኖሩ እና የስራ እንቅስቃሴያቸውንም በእጀባ እንዲያከናውኑ አስገድዷቸዋል።
"የሚጨመር መሰረተ ልማት የለም፤ የሚወድም ግን አለ። የሚገነባ ትምህርት ቤት የለም፤ የሚወድም አለ። . . . ክልሉን ለመመመለስ አስቸጋሪ በሚሆን ደረጃ እየወደመ ነው" የሚሉት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር ገዱ አንዳርጋቸው፣ ክልሉ ወደ ኋላ 30 እና 40 ዓመታት እየሄደ ነው ይላሉ።
መውጫ መንገዱ ምን ይሆን?
አማራ ክልልን ለቀውስ የዳረገው ግጭት መቼ እንደሚያበቃ አይታወቅም።
የክልሉ ነዋሪዎች መውጫ መንገዱ የጨለመባቸው ይመስላል። ተስፋቸው ደጋግመው የሚያነሱት ፈጣሪያቸው እንጂ በተለይ በመንግሥት ተስፋ ስለመቁረጣቸው አስረግጠው ይናገራሉ።
"እግዚአብሔር የሚመልሰው ካልሆነ ሰው አይመልሰውም" ይላሉ አንድ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ።
የፖለቲካ ሳይንስ መምሕር የሆኑት ዶ/ር የሺጥላ ወንድሜነህ የክልሉን ቀውስ የሚፈታው ቁልፍ የሚሏቸው የችግሮች ምንጭ በንግግር እልባት ሲያገኙ ነው ብለው ያምናሉ።
"ችግር በኃይል አይፈታም" የሚሉት ዶ/ር የሺጥላ "ሁለቱም ወገኞች የሚታመኑ አደራዳሪዎችን በመመምረጥ፣ እርስ በእርሳቸው መተማመንን በመገንባት፤ በድርድር የሚመጣውን ማናቸውንም ውጤት ለመቀበል ዝግጁ መሆን፤ ድርድር ሰጥቶ መቀበል ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ አካባቢውን ብቻም ሳይሆን አገሪቱንም ከጥፋት መታደግ ይቻላል" ይላሉ።
"ቀውስ ቀውስን ይወልዳል" ለሚሉት ዶ/ር ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ቀውስ ወደ ሌሎች ክልሎች የሚዛመት እንደሆነ በማንሳት መውጫ መንገዱ ንግግር አሊያም የሰላም ስምምነት ሳይሆን "ሥርዓታዊ ለውጥ" ይላሉ።
አክለውም "በድርድር ቢፈታ ደስታውን አልችለውም ነበር። የኔ ምርጫ በፖለቲካ መንገድ ቢፈታ ነው። ነገር ግን አሁን ያለው አገዛዝ ችግሮችን በፖለቲካዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎት የለውም። ለድርድር ታማኝም አይደለም።"
መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች በአማራ ክልል ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን፣ በፋኖ ኃይሎች በኩል ያለው ፍላጎት በግልጽ አይታወቅም። በዚህም ምክንያት አስካሁን ንግግር ለመጀመር የተጀመረ ነገር ስለመኖሩ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።
በዚህ ዘገባ ውስጥ የክልሉ ባለሥልጣናት እንዲሁም የገዢው ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊን አስተያየት ለማካተት ቢቢሲ ለሳምንታት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
*በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው የተቀየረ












