በሸዋ ሮቢት የሰው ሕይወት የጠፋበት ከባድ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ነዋሪዎች ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Shewa Robit City
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሰው ሕይወት የጠፋበት ከባድ ግጭት መካሄዱን ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሸዋሮቢት ከተማ ትናንት እሁድ የካቲት 24/2016 ዓ.ም. የተከሰተው ከባድ በግጭት ለሰዓታት የቆየ ነበር።
ከዕኩለ ቀን በኋላ 7፡00 ሰዓት አካባቢ ተጀምሯል የተባለው ውጊያው እስከ ምሽት 4፡00 ሰዓት ገደማ ድረስ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እንደዘለቀ ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አራት የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በሸዋ ሮቢት በመከላከያ እና በአካባቢው ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደው ውጊያ ከነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች አንስቶ የከባድ በመሳሪያዎች ድምጽ ይሰማ እንደነበርም ነዋሪዎች ጠቁመዋል።
“ተኩሱ እጅግ በጣም የሚረብሽ እና ከባድ ስጋት የሚፈጥር ስለነበር ሁሉም በየቤቱ ነው የተቀመጠው” ሲሉ ስለ ውጊያው የተናገሩ አንድ የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ፤ “በከተማዋ ዙሪያ ሁሉ ውጊያ ነበር” ሲሉ ለረጅም ሰዓታት የተካሄደውን ግጭት ገልጸዋል።
የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ውጊያው እንደተጀመረ የተናጉት ሌላ ነዋሪ፣ በአብዛኛው የከተማዋ አካባቢዎች ግጭት መደረጉን አስረድተዋል።
የከተማዋን ነዋሪዎች ከባድ ስጋት ውስጥ የከተታቸው ውጊያው 03 ጫሬ፣ በአዲስ አበባ መውጫ ማደያ ሰፈር፣ ራሳ መስመር፣ የደሴ መስመር መውጫ እንዲሁም መሀል ከተማ አካባቢ እንደ ነበር አራቱም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በተለይ እንደ ፖሊስ ጣቢያ እና “የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ይገኙባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች” ለረጅም ሰዓታት የቆየ ከባድ ውጊያ ተደርጓል ብለዋል።
እሁድ እኩለ ቀን የጀመረውን ግጭት “ትልቅ ጦርነት ነበር” ያሉት ነዋሪ፤ ምሽት 2፡00 ሰዓት አካባቢ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ አብዛኛ ክፍል ገብተው ተቆጣጥረው “የሚፈልጉትን አድርገው ወጡ” ሲሉ ስለሁኔታው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከባዱ የተኩስ ልውውጥ እሁድ ምሽት ካበቃ በኋላ ሰኞ ጠዋትም አልፎ አልፎ ተኩስ እንሚሰማ የተናገሩት ነዋሪዎች፣ ከረፋድ ጀምሮ የመንግሥት ኃይሎች በፓትሮል “መንደር ለመንደር አሰሳ” እያደረጉ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም በነዋሪው ላይ ስጋት መፈጠሩን አመልክተዋል።
“ቤት ዘግተን ነው ቁጭ ያልነው። ያሰጋል፤ በጣም በፍርሃት ውስጥ ነን። በቀደም የሹማምንቱ ግድያ ቀን ምንም በማያውቁ ንጹሃን ላይ ለማመን የሚከብድ ድብደባ ነው ሲፈጸም ነበረው” ብለዋል ነዋሪው።
በከተማዋ የተካሄደው ግጭት አጅግ ከባድ በመሆኑ ነዋሪዎች በቤታቸው ውስጥ ሆነው “አስፈሪ” ያሉትን የተኩስ ልውውጥ ድምጽ ከመስማት ውጪ ስለደረሰ ጉዳት በእርግጠኝነት መናገር አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል።
ቢቢሰ ካናገራቸው ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሚያውቋቸው ብቻ ሦስት ሠዎች መገደላቸውን የተናገሩ ሲሆን “ሌሎችም [የተገደሉ ሠዎች] ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ በውጊያው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ተገድለዋል ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል።
“አንዱ ጋሪ ነጂ፣ አንዱ ሹፌር፣ አንዱ ደግሞ የሰፈር ነዋሪ ነው። ብዙ ሰው ሞቷል” ያሉት ነዋሪው አንዱ ነዋሪ “በፀጥታ ኃይሎች” ጥቃት እንደተገደለ እንደሚያውቁ ገልጸዋል።
“አንዱ መነኸሪያ አካባቢ ነው፤ ሹፌር ነው። አንዱ ፍ/ቤት አካባቢ አድማ በታኞች ያሉበት አካባቢ [ነው] ቤቱ። አንዱ መንገድ ላይ ነው ወድቆ የተገኘው” በማለት የሟቹን ማንነት እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
“ታችኛው ማደያ” በተባለ አካባቢ ሁለት ሠዎች መገደላቸውን ከወዳጆቻቸው እንዳረጋገጡ የተናገሩ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ “መናኸሪያ እየተባለ በሚጠራው የከተማዋ አካባቢም የሞቱ ሰላማዊ ሰዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ” ብለዋል።
“ጉሊት” በተባለ ገበያ ውስጥ ሦስት ሰዎች እና መናኸሪያ ጎሚስታ አጠገብ አንድ ሰው ሞተው መገኘታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ ነዋሪ በበኩላቸው፤ ከቤት ለመውጣት አስፈሪ በመሆኑ እንጂ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል።
ከሟቾቹ መካከል የቀን ሠራተኛ እና ሹፌር እንደሚገኙበት የተናገሩት ነዋሪው፤ የተገደሉትም በተባራሪ ጥይት እንደሆነ ገልጸው ቀብራቸውም ዛሬ ሰኞ ማሪያም እና ሚካኤል በተባሉ የከተማዋ አብያተ ክርስቲያናት መፈጸሙን ተናግረዋል።
በከተማዋ በስፋት ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ የጋሪ እና የባጃጅ እንቅስቃሴዎች ዛሬ እንደሌለ በመግለጽ “መንገድ ላይ የሚንቀሳቀስ ሰው የለም፤ የደፈረ ሰው ብቻ ነው ወደ ውጭ የሚወጣው” ሲሉ በከተማዋ ስላለው እንቅስቃሴ ተናግረዋል።
እሁድ እኩለ ቀን የጀመረው የተኩስ ልውውጥ የረገበው ምሽት 4፡00 ሰዓት አካባቢ መሆኑን የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ የፋኖ ታጣቂዎች “የሚፈልጓቸውን የመንግሥት የካቢኔ አባላትን” ሳይወስዱ እንዳልቀሩ ተናግረዋል።
የተካሄደውን ውጊያ ተከትሎ ዛሬ ሰኞ ከተማዋ ከእንቅስቃሴ ውጪ መሆኗን ነዋሪዎች ረፋድ ላይ የተናገሩ ሲሆን፣ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማም አመልክተዋል።
ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመከላከያ እና በፋኖ ኃይሎች መካከል ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎ ሸዋ ሮቢት ውጥረት ውስጥ እንደነበረች የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “የከተማዋ ሁኔታ ጥሩ አልነበረም” ብለዋል።
ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ እና የሰላም እና ደኅንነት ኃላፊ “በፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን” እና ይህን ተከትሎም የመንግሥት ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ “ከባድ ድብደባ” በመፈጸማቸው ሸዋ ሮቢት ስጋት ላይ ሰንብታለች ብለዋል።
የፋኖ ታጣቂዎች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ የከተማው ሕዝብ “እልህ መወጫ ሆኗል” ያሉት አንድ ነዋሪ፤ ይህ የተለመደ በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ስጋት ውስጥ ነው ብለዋል።
ነዋሪው “ፋኖዎች መጥተው የሆነ ነገር ባደረሱ ቁጥር ስጋት ነው በቃ፤ ሽሽት ነው፤ ዱላ ነው” ሲሉ በሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ የተፈጠረውን የስጋት ስሜት ገልጸውታል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የምትገኘው ሸዋ ሮቢት ከተማን ጨምሮ በምሥራቃዊ የአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙት ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ በተፈጠረ የፀጥታ ስጋት ምክንያት ከአንድ ሳምንት በፊት የትራንስፖርት ገደብ መጣሉ ይታወሳል።
በአማራ ክልል የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈጽመው አካል አንድ ክፍል የሆነው የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ከየካቲት 16/2016 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በደብረ ብርሃን፣ በሸዋ ሮቢት እና በደሴ መካከል የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ወስኗል።
ኮማንድ ፖስቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈውም “ፅንፈኛ” ያላቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ በመሆኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል መሆኑን ገልጿል።
ባለፈው ዓመት መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ለመበተን እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የትጥቅ ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።
የፋኖ ታጠቂዎች በክልሉ ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከአቅሙ በላይ መሆኑን የገለጸው የአማራ ክልል መስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ ሕግ እንዲያስከብር ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ ተሰማርቶ ይገኛል።
በዚህም ሳቢያ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት እየተባባሰ እና ጋብ እያለ የቆየ ሲሆን፣ ከጥቂት ሳምንት ወዲህ ግን በበርካታ ቦታዎች ላይ ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ አርብ በክልሉ ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር ውስጥ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ተካሂዶ የከተማዋ መደበኛ እንቅስቃሴ ተስተጎጉሎ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።












