በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች “ከባድ ውጊያ” ማገርሸቱን ነዋሪዎች ተናገሩ

የአማራ ክልል ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካለፈው ሳምንት መገባደጃ አንስቶ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ማገርሸቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በጎጃም፣ በሰሜን ሸዋ፣ሰሜን ወሎ እና ጎንደር አካባቢዎች በሚገኙ በርካታ ስፍራዎች ጠንከር ያሉ ግጭቶች እየተካሄዱ ነው ያሉ ነዋሪዎች መንገዶችም መዘጋታቸውን ገልጸዋል።

ከሳምንቱ መገባደጃ ቀናት አንስቶ በመርዓዊ፣ ደቡብ ሜጫ፣ ቋሪት፣ ሰከላ፣ ደጋ ዳሞት፣ አንጾኪያ ገምዛ ወረዳ፣ ሸዋ ሮቢት አካባቢ፣ ላሊበላ ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎች ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከደብረ ብርሃን ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ ከቅዳሜ፣ የካቲት 16/ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት መወሰኑን አስታውቆ ነበር።

ኮማንድ ፖስቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው “ፅንፈኛ” ያላቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል እንደሆነ ገልጿል።

በተመሳሳይም መከላከያ በደቡብ ሜጫ አካባቢ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ ገልጿል።

አክሎም በአካባቢው “ጽንፈኛ” ባለው ቡድን “አመራሮች እና አባላት” ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል።

“ከባድ ውጊያ” ተደርጎባቸዋል ከተባሉ ከተሞች መካከል ባለፈው ጥር በመንግሥት ኃይሎች የጅምላ ግድያ እንደተፈጸመባት በስፋት የተዘገበባት መርዓዊ ከተማ አንዷ ናት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የካቲት 16 2016 ዓ.ም. ቅዳሜ፣ በከተማዋ በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለሰዓታት የዘለቀ ከባድ ውጊያ እንደነበር ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረው “ውጊያው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ውጊያው በከተማዋ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚገኙባቸው አካባቢ መጀመሩን የተናገሩት ነዋሪው፣ ከሁለት ሰዓታት በላይ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።

በዕለቱ ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት አካባቢ የፋኖ ኃይሎች ከተማዋን መቆጣጠራቸውን የገለጹት ነዋሪው፤ ነገር ግን ከተማዋን ይዘው የቆዩት ለሰዓታት ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።

ነዋሪው የፋኖ ኃይሎች ከከተማዋ ቢወጡም የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ጠቅሰው፤ በከተማዋ ከነበረው ሁኔታ ጋር በተያያዘም ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

የተኩስ ድምጽ እሁድ እና ሰኞ ድረስ እንደቀጠለ አመልክተው፣ ከተማዋ አሁንም በስጋት ውስጥ መሆኗን እና ነዋሪውም “በቤቱ ተቆልፎበት ነው ያለው” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎም ከመርዓዊ ወደ ባሕር ዳር እንዲሁም ወደ ፍኖተ ሰላም የሚወስደው ዋና መንገድ ከሰኞ ጀምሮ መዘጋቱንም ተናግረዋል።

በመርዓዊ ከተማ ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎችም በከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ከባድ ውጊያ እንደነበር የደቡብ ሜጫ ወረዳ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መሀል ገነት በተባለችው የወረዳዋ ከተማ ቅዳሜ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ መከላከያ ሲገባ ውጊያው እንደተጀመረ የሚያስረዱት ነዋሪው፣ ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ በአካባቢው የእህል ጎተራዎች እና በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን ተናግረዋል።

ይህንን በተመለከተ መከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ በአካባቢው የተሰማራው ሠራዊት አዛዥ ኮሎኔል ይመር ገበየሁ “ጽንፈኛው ማቃጠል የጀመረውን ቤት ሠራዊቱ በፍጥነት ደርሶ እሳቱን በማጥፋት ሰው እና ንብረት አድኗል” ብለዋል።

ከመርዓዊ በ42 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ከተማዋ “ባዶ ሆናለች” ያሉት ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ ነዋሪ፣ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች በስጋት ቤታቸውን ለቅቀው ወደ ገጠር እና ወደ ጫካ መሰደዳቸውን ገልጸዋል።

መከላከያ ሠራዊት በደቡብ ሜጫ አካባቢ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ የገለጸ ሲሆን፣ ሠራዊቱ “ጽንፈኛ” ባለው ቡድን “አመራሮች እና አባላት” ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አመልክቷል።

በተጨማሪም ሠራዊቱ ከመርዓዊ እስከ ገርጨጭ ድረስ ባለው 23 ኪሎ ሜትር ላይ ተሰማርቶ “የተዘጉ መንገዶችን በመክፈት፣ የተኩስ እና ሌሎች መሰናክሎችን በማስወገድ” በታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከቅዳሜ የካቲት 16 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መንገዱ በተዘጋበት በሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢም ውጊያ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዞኑ በአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ ስር ባሉ ቀበሌዎችም እሁድ የካቲት 17/2016 ዓ.ም. ሌሊት ላይ ውጊያው እንደተጀመረ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን በምትገኘው በታሪካዊዋ ላሊበላ ከተማ ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎችም በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንደነበረ አንድ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የላሊበላ አየር ማረፊያ በሚገኝበት ሽምሻ በተባለ ቀበሌ እና ደጎሳች በተባለ የላስታ ወረዳ ቀበሌ ጋብ ብሎ የነበረው ውጊያ ቅዳሜ ዕለት “ጠንከር” ብሎ ሲካሄድ እንደነበረ ገልጸዋል።

በከተማዋ ዙሪያ ካሉ ቀበሌዎች የከባድ መሳሪያ ድምጾች ይሰሙ ነበር ያሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት ነዋሪ፤ ዕሁድ ዕለትም አልፎ አልፎ ተኩስ ቀጥሎ ነበር ብለዋል።

ባገረሸው ውጊያ ምክንያት በአካባቢው ያለው የሰዎች “እንቅስቃሴ የተገደበ ነው” ያሉት ነዋሪው፤ በላሊበላ ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎች መንቀሳቀስ እንደማይቻል ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ያገረሸው ለተወሰኑ ሳምንታት ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ነው።

የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ ዞኖችን የሚያገናኘው ዋና መንገድ ላልተወሰነ ጊዜ ከማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ውጪ እንዲሆን መደረጉን የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ባለፈው ቅዳሜ መወሰኑ ይታወሳል።

በዚህም ከደሴ - ሸዋ ሮቢት - ደብረ ብርሃን እንዲሁም ከደብረ ብርሃን - ሸዋ ሮቢት - ደሴ የሚደረጉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ የተደረገው፣ ኮማንድ ፖስቱ በአካባቢው “ፅንፈኛ” ያላቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል መሆኑን ገልጿል።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ በኋላ የክልሉን ልዩ ኃይል ለመበተን እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።

የክልሉ መስተዳደርም ሁኔታው ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በመጠየቁ በክልሉ እና እንዳስፈላጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ወደ ክልሉ ተሰማርቶ ይገኛል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በተካሄዱ ወታደራዊ ግጭቶች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ መደበኛ እንቅስቃሴዎች የተስተጓጎሉ መሆናቸውን ነዋሪዎች ሲናገሩ ቆይተዋል።

በተጨማሪም በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል በሚካሄዱ ውጊያዎች እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና የንብረት ውድመት ማጋጠሙ እየተዘገበ ነው።