ከ30 በላይ ሰዎች በፋኖ በተገደሉበት ደጋ ዳሞት የተከሰተው ምንድን ነው?

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ባለፈው ሳምንት ከ30 በላይ የአካባቢው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የፀጥታ አባላት በፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የአካባቢው አስተዳደር ተናገሩ።
በዞኑ ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማ ኅዳር 26/2017 ዓ.ም. ለሁለት ወራት ለመንግሥት ኃይሎች "መረጃ እና ድጋፍ ሰጪ" በሚል ተጠርጥረው በፋኖ ታጣቂዎች ተይዘው የነበሩ በርካታ የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት "መረሸናቸውን" ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አለማየሁ 20 ከሚሆኑ የወረዳው ካቢኔዎቻቸው ጋር የግድያው ሰለባ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።
መስከረም መጨረሻ በአካባቢው "ከባድ ውጊያ" መደረጉን ተከትሎ መስከረም 29/2017 ዓ.ም. ወረዳው በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባቱን እና የመንግሥት ኃይሎች ወረዳውን ለቀው መውጣታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ "[መከላከያ] የሚሊሻ፣ የፖሊስ አባላትን እንዲሁም ካቢኔዎችን በሙሉ መስመር ላይ ነው ጥሏቸው የሄደው" ሲሉ አንድ ነዋሪ፤ 'ባልተለመደ ሁኔታ' የወረዳው አስተዳደር ከተማዋ ውስጥ መቅረቱን ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ዓለም 20 የሚሆኑ የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች መከላከያ ሠራዊት "ለስምሪት" አካባቢውን ለቆ ሲወጣ "ተቆርጠው" መቅረታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ጨለማ ስለነበር በተለያየ ምክንያት ነው የተወሰኑት ተቆርጠው የቀሩት" ያሉት ኃላፊው፤ "ጽንፈኛ" ያሉት ኃይል "የቀረውን አመራር በሽማግሌ በምንም አሰባስቦ በአንድ ማዕከል ሰብስቦ አሰረ" ብለዋል።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ የፋኖ ኃይል "ማኅበረሰቡን በድለዋል፣ ለመንግሥት መረጃ እና ድጋፍ ሰጥተዋል" ብሎ በመጠርጠር የሥራ ኃላፊዎቹን "በየአቅጣጫው አፈላልጎ" በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተናግረዋል።
የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች "የፋኖ እስረኛ ነበሩ" ያሉት ነዋሪው፤ በወረዳው አስተዳደር ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ከእስረኞች ውስጥ አንዱ ነበርኩ ያሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የወረዳው የግብርና ባለሙያ መስከረም 29 በተደረገባቸው "ጥቆማ" መያዛቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እሳቸውን እና ዘጠኝ ሴቶችን ጨምሮ 115 ሰዎችን በወቅቱ በፋኖ ታጣቂዎች ታስረው እንደነበር ገልጸው፤ "ጠዋት እየገባን ከሰዓት እየመለሱ፤ የሚለቁበት ሁኔታ ነበር" ሲሉ ስለአያያዛቸው ተናግረዋል።
የፋኖ ኃይሎች በተለይም "በግል ጥላቻ" ታስረው የነበሩ ሰዎችን እያጣሩ መልቀቃቸውን እና 57 ሰዎች መቅረታቸውን ገልጸዋል።
የፋኖ ታጣቂ መሪዎች እስረኞቹ ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ ማብራሪያ እና ምክር እንደሰጧቸው የጠቆሙት እስረኛው፣ መጨረሻ ላይ እሳቸውን ጨምሮ 37 እስረኞች መቅረታቸውን ተናግረዋል።
ሌሎች "ተጠርጥረው" የታሰሩ ሰዎችን ጨምሮ የሥራ ኃላፊዎቹ እና የፀጥታ አባላቱ በታሰሩበት የወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ላይ የድሮን ጥቃት ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ እንደተፈጸመ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በጥቃቱ እስረኞች ላይ ጉዳት ባይደርስም በአካባቢው [ከፖሊስ ጣቢያው ጎን] የግለሰብ ቤት በመመታቱ የሦስት ዓመት ህጻን ግን መገደሉን ተናግረዋል።
ይህን ያረጋገጡት እስረኛው "እኛ ካለንበት በ10 ሜትር ርቀት ላይ ድሮን ጣለ" በማለት የጥቃቱ ሰለባ በስም የሚጠቀሱት አንድ ህጻን ልጅ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎም እስረኞቹ "ጎማጣ" ወደ ተባለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደተዘዋወሩ የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ እዚሁ ትምህርት ቤት መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ታሳሪዎቹ "በመንግሥት ታጥቀውታል" የተባለውን መሳሪያቸው ለፋኖ ኃይሎች ማስረከባቸውንም እማኞች ተናግረዋል።

እስረኞቹ ማኅበረሰቡ እንዲያስፈታቸው ሲወተውቱ እና የመንግሥት ኃይሎችም እንዲያስለቅቋቸው በቤተሰቦቻቸው በኩል ሲጠይቁ ነበር ተብሏል።
አቶ ሙሉጌታ "ሩቅ ስለሆነ፤ ከመስመሩ ወጣ ያለስለሆነ የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ካልገባ በስተቀር ማስለቀቅ አይቻልም [ነበር]" ሲሉ እስረኞችን ለማስለቀቅ ጥረት አለመደረጉን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኅዳር 25/2017 ዓ.ም. በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ውጊያ መቀስቀሱን ተከትሎ፤ ሌሊት 9፡00 ሰዓት ላይ የፋኖ ኃይሎች 37ቱን ሰዎች ከታሰሩበት ትምህርት ቤት እንዲወጡ እንዳዘዟቸው ገልጸዋል።
በስም ዝርዝር በሁለት ቡድን እንደተለዩ እማኝነታቸውን የሰጡት እስረኛው፤ ከፈረስ ቤት ከተማ በግምት ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው 'ፈረስ ቤት ሚካኤል' አካባቢ የሚገኝ ትምህርት ቤት እንደተወሰዱ ተናግረዋል።
በአንደኛው ቡድን 31 እስረኞች፤ በሁለተኛው ቡድን ደግሞ ስድስት እስረኞች በመኪና ተጭነው መወሰዳቸውን አመልክተዋል።
". . . ፊት እና ኋላ አድርገውን ነው ይዘውን የሄዱት። [ትምህርት ቤት] ጊቢው ስንደርስ ውረዱ እስኪሉን አልጠበቅንም፤ ወረድን። እናንተ [ሁለተኛው ቡድን] ተመልሳችሁ ውጡ ተባልን፤ ተመልሰን መኪና ላይ ወጣን" ሲሉ የመጨረሻውን ቅጽበት አስታውሰዋል።
የወረዳውን አስተዳዳሪ ጨምሮ 31ዱን እስረኞች የያዘው የመጀመሪያው ቡድን ወደ ትምህርት ቤት ቅጥር ጊቢ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ "እናንተ እለፉ ተባልን። ከዚያ [የተኩስ] ድምጽ ሰማን" ሲሉ ስለ ግድያው እና እሳቸው እንዴት እንደተረፉ ተናግረዋል።
በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበሩት የአካባቢ አመራሮች "ፈረስ ቤት ሚካኤል" በተባለ የከተማው መውጫ ላይ ተወስደው መረሸናቸውን ሦስት ነዋሪዎች እና የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዞኑ ሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ 37 "የፖለቲካ መሪዎች እና የፀጥታ መዋቅሩ አባላት" ለሁለት ወራት ታስረው ገዘንዘብ እንዲከፍሉ እና በማኅበረሰቡ እንዲሸማቀቁ ከተደረጉ በኋላ "በጅምላ ተረሽነዋል" ብለዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ አቶ ዋለ አለማየሁ የወረዳው አስተዳዳሪ፣ ቄስ እንዳለ ገበየሁ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ዘመኑ ይባቤ የእንስሳት ሀብት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ዓይንአለም ስንሻው የውሃ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ወንድይፍራው ጌታነህ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
የሟቾቹን አስከሬን ማኅበረሰቡ ማንሳቱን የጠቆሙ አንድ ነዋሪው፤ በአብዛኛው ቀብር ፈረስ ቤት ከተማ በሚገኙት መድኃኒዓለም እና ገብርኤል በተባሉ አብያተ ክርስቲያናት እና በዙሪያው ባሉ ቀበሌዎች እንደተፈጸመ ገልጸዋል።
"የሚሊሻ ደሞዝ በመክፈል እና መረጃ በመስጠት" ተጠርጥረው ታስረው እንደነበር የተናገሩት የግብርና ባለሙያው፤ "ተገድጄ ማድረጌን በምስክር እና በመረጃ" በመታወቁ በሕይወት መትረፍ ችያለሁ ብለዋል።
ስድስቱ እስረኞች ከፋኖ ኃይሎች ጋር "ቀጸላ" ወደተባለ አቅጣጫ ከተጓዙ በኋላ "ከዚህ በኋላ ስህተት እንዳትፈጽሙ" ተብለው መለቀቃቸውን ተናግረዋል።
ቢቢሲ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂ ቡድን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካም፤ ባለፈው ዓመት አስረስ ማረ ተባሉ የፋኖ አመራር የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን "መሳሪያ ከያዘው ወታደር ለይተን አናያቸውም" ብለው ነበር።
አመራሮቹ "ተዋጊ አይደሉም" የሚሉት አቶ ሙሉጌታ የፋኖ ኃይሎች ከሁለት ወራት በኋላ "የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ሲገባ እነዚህ ሰዎች ወደ መንግሥት ተመልሰው እንዳይቀላቀሉ እና ሥራ እንዳይሠሩ እና አስተዳደሩን ለማዳከም" አስበው ግድያውን ስለመፈጸማቸው አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።
የመንግሥት ኃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን ታጥቀው ኅዳር 27/2017 ዓ.ም. ጠዋት 4፡00 አካባቢ ፈረስ ቤት መግባታቸውን የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ መምህር ማኅበረሰቡ በስጋት ከተማዋን ለቆ መውጣቱን ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው "'የፋኖ ደጋፊ ነበር፤ ፋኖን ስታበላ ስታጠጣ ቆይተሃል' በማለት የተገኘ ንጹሃን እየተገደለ ነው" ሲሉ የመንግሥት ኃይሎች ከተማን ከያዙ በኋላ ሁለት "ንጹሃንን" ገድለዋል ብለዋል።
"ዋስትና የለንም" የሚል ስጋት እንዳላቸው የተናገሩ ሌላ ነዋሪ ስጋታቸውን ማኅበረሰቡ እንደሚጋራቸው ጠቁመው፤ "[ማኅበረሰቡ] ወጥቷል" ብለዋል።
"ሁሉም ማኅበረሰብ ቤቱን ለቆ እና ዘግቶ እየወጣ ነበር። ከከተማ ወደ ገጠር መፍለስ ነበር። . . . አሁንም እየወጣ ነው" ሲሉ ስጋቱን ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ዓለም ማኅበረሰቡ "በስጋት እንዲወጠር ያደረገው ታጣቂ ቡድኑ እንጂ የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር አይደለም" በማለት ንጹሃንን አልተገደሉም ብለዋል።












