'ሁለቱንም ፆታ ይዤ በመፈጠሬ መገለል እና ፆታዊ ጥቃት ደርሶብኛል'

የ28 ዓመት ወጣት ናት፤ ንግሥቲ አሰፋ ትባላለች።
ላለፉት 15 ዓመታት በቤተሰቦቿ እና በምትኖርበት ማኅበረሰብ መገለል እና እንግልት ደርሶባታል።
ከሁለት ዓመት በፊት በፕሪቶሪያ ስምምነት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ በጎረቤቶቿ ምክንያት ፆታዊ ጥቃት እንዲደርስባት መደረጉን ትገልጻለች።
ንግሥቲ ስለ አፈጣጠርዋ ስታወራ እንደ ዕድሜ እኩዮቿ የወር አበባ እንደማታይ፣ ጡቶቿ ሙሉ በሙሉ ያላደጉ መሆናቸው፣ ተክለ ሰውነቷ ግን የሴት በመሆኑ ፀጉሯን ሹርባ መሠራት እንደምታዘወትር ትናገራለች።
ስትፈጠር በመራቢያ አካሏ አካባቢ የነበረው የወንድ ብልት ግን ከሰውነቷ ጋር ዕኩል ማደግ ስላልቻለ በ2004 ዓ.ም በሕክምና እንዲወገድ ተደርጓል።
"ሰዎች በማይገባ ቦታ ላይ ሊነካኩኝ፣ ሊያሰቃዩኝ ስለሚሞክሩ በመፍራት እና በመገለለል ነው ስኖር የቆየሁት። ቤቴንም 11፡00 ሰዓት ላይ ነው የምዘጋው። በሚደርስብኝ ስድብ እና ማንቋሸሽ ምክንያት አእምሮዬ ተጎድቷል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ታሪክ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ከፆታዊ ጥቃት ጋር የተገናኘ ይዘት አለው።
"እትብቴ እንጂ በክብር የተቀበረው እኔ ክብር የለኝም "
ንግሥቲ አሰፋ ከቤተሰቧ እና ከዘመዶቿ ርቃ በትግራይ ክልል እምባ አላጄ ወረዳ መኖር ስትጀመር ገና 13 ዓመቷ ነበር።
ለትዳር ያጯት ሰዎች ለሽምግልና ጎረቤት ጋር ሲሄዱ 'አይ፤ እሷ እኮ በሽተኛ ናት' ብለው ሲመልሷቸው የዘጠኝ ዓመት ልጅ እንደነበረች ታስታውሳለች።
በወቅቱ በትምህርቷ፣ በተለይ በሒሳብ ጎበዝ እንደነበረች እና ሁልጊዜም ከክፍሏ አንደኛ ትወጣ ስለነበር፤ በሒሳብ ትምህርት ደካማ የሆኑ ሴት ጓደኞቿን ስለምታስጠና "መምህርት ንግሥት" ብለው ይጠሯት ነበረ።
'ንግስቲ ለትዳር አትበቃም' የሚል ወሬ ከቤተሰቦቻቸው የሰሙ አብረዋት እረኝነት የሚውሉ የጎረቤት ልጆች 'ፍናፍንት ናት' እያሉ ያሟት ጀመር።
በእረኞች ዘንድ እና ቤት ውስጥ የሚነገረው ሐሜትም ትምህርት ቤት ደርሶ ተማሪዎች በጥቁር ሰሌዳ ላይ በመጻፍ ይሳለቁባት ነበር።
በዚህ ምክንያት መገለል እና መሸማቀቅ ይደርስባት ስለጀመረ፣ ከምትኖርበት ቀበሌ እና ወረዳ ርቆ ወደሚገኝ ትምህርት ቤት እየሄደች ትምህርቷን ለመከታተል ብትሞክርም ብዙም ሳትገፋበት አምስተኛ ክፍል ስትደርስ ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገደደች።
"ከዚያ በኋላ ከጓደኛ ወይም ከሌላ ሰው ጋር መቀራረብ አልቻልኩም። በስድቦቹ ምክንያት የእኔ የሆነውን ከወሰደ ሰው ጋር እንኳ የእኔ ነው ብዬ የምሟገትበት አቅም አልነበረኝም።"
ቤተሰቧም አፈጣጠርዋን እንደ ኃጢአት በመቁጠር ከልጃቸው ይልቅ ማኅብረተሰቡ ለሚሰጣቸው እና ለሚነፍጋቸው 'ክብር' አደሉ።
"እትብቴ ነው በክብር የተቀበረው እንጂ እኔን ዞር ብሎ የሚያየኝ ሰው የለም" በማለት በዚህ ምክንያት ለበርካታ ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች መጋለጧን ትናገራለች።
ንግሥቲ በዚህ ምክንያት የደረሰባት መገለል ከልጅነቷ ይጀምራል፤ የ13 ዓመት ልጅ ነበረች።
ሰዎች መታከም እንደምትችል ሲናገሩ ሰምታለች፣ ስለዚህ ከ15 ዓመታት በፊት ለሕክምና ወደ መቀለ ከተማ ሄደች።
"ምንድን ነው የምሆነው? የሚል ሃሳብ ስለነበረኝ እራሴን ከማጠፋ ቀዶ ሕክምና በማደርግበት ወቅት ብሞት ይሻላል በሚል ዕጣ ፈንታዬን ለመቀበል የሪፈራል ደብዳቤ ይዤ ወደ ሆስፒታል ሄድኩኝ" በማለት ቀዶ ሕክምና እንዲደረግላት በራሷ ፍቃድ መወሰንዋን ገልጻለች።
'በሰዎች ጥቆማ ምክንያት ፆታዊ ጥቃት ደርሶብኛል'
ከሁለት ዓመታት በተካሄደው የትግራይ ጦርነት ወቅት በርካታ ሴቶች የፆታዊ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል።
ንግሥቲም ኅዳር 21 2013 ዓ.ም ላይ ወደ ምትኖርበት መንደር በገቡት የመንግሥት ወታደሮች ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባት ተናግራለች።
"የአካባቢዬ ሰዎች ናቸው የጠቆሙብኝ፤ ባል ሳይኖረኝ የሚሊሻ ሚስት ናት ብለው ወታደሮች ወደ ቤቴ እንዲመጡ አደረጉ። ወታደሮቹ 'ባልሽን አምጪ' አሉኝ፤ እኔ ግን የማህፀን ችግር ስላለብኝ ባል የለኝም አልኳቸው።"
ንግሥቲ አሁን ባላት ተፈጥሯዊ ሁኔታ ምክንያት ትዳር አለመመሥረቷን ገልጻለች።
"ከዚያም ልብሴን ገፈፉኝ፣ 'በጩቤ እንቅደደው?' ብለው ተሳለቁብኝ። የመሳሪያቸው አፈ-ሙዝ ለመክተትም ሞከሩ። ከዚያ በኋላ ግን ሦስት ሆነው በመቀመጫዬ ደፈሩኝ። መቀመጫዩ ለስድስት ወራት ወደ ውጪ ተግልብጦ ነበር። ሽንቴን መቆጣጠርም አቅቶኝ መግል ነበር የሚፈሰው" ትላለች።
በዚህም ምክንያት ሽንቷን መቆጣጠር እንደምትቸገር እና በምትሸናበት ወቅት በመርፌ ለማስወገድ እንደምትሞክር ነው የምትናገረው።
"ማኅበረሰቡ ስለሚያገለኝ በጦርነቱ ወቅት ብቻ ሳይሆን በባሎቻቸው ጭምር ጥቃት የደሰረባቸው ሴቶች የሚመለከት ጥናት ይካሄዳል በተባለበት ወቅት የቀበሌው አስተዳዳሪዎቹ እኔም የጥቃቱ ሰለባ ነኝ ስላቸው 'ምን ኖሮሽ ነው የምትደፈሪው' ብለው አገለሉኝ" በማለት ትከሳለች።
በዚህም ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ራሷን ለማጥፋት ያሰበችባቸው ጊዜያት እንዳሉ ትገልጻለች። በተደራራቢ ችግሮች ምክንያትም ለከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግሮች መጋለጧን ተናግራለች።
"የእኛ ማኅበረሰብ እንደ እኔ ያለ ፍጡር ይቅር እና የዓይን፣ የእጅ እና የእግር ጉዳት ያለበትን ሰው እንኳን 'አንተ ሰንካላ፣ ቆራጣ' ብሎ ነው የሚያንቋሽሸው" በማለት እሷ የተፈጠረችበት ሁኔታ እንደ አካል ጉዳት እንደምትቆጥረው ገልጻለች።
"አንቺ [ጠያቂዋን ጋዜጠኛ] ሌሎች ሰዎችም ጋር ያለ ነው እያልሽኝ ነው፤ እኔ ግን አይመስለኝም። እኔ እውነትም ኃጢአተኛ ነኝ እንዴ? እያልኩ ነው ራሴን የምጠይቀው።
"ኅብረተሰቡ ልጅ መውለድን ነው እንደ ቁም ነገር የሚቆጠረው። ቆሞ የሚሄድ ሰው ቁም ነገር አለው ብሎ የሚያምን ሰው የለም" በማለት ማኅበረሰብ ውስጥ የሰረጹ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችን የሚያሳድሩባት ጫና ከባድ መሆኑን ትናገራለች።
የሁለቱ ፆታ የመራቢያ አካል ይዞ መወለድ ምንድን ነው?
እጅግ ጥቂት ሰዎች የሁለቱ ፆታ የመራቢያ አካላት ይዘው ሊወለዱ እንደሚችሉ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በመቀለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የጽንስ እና ማህጸን ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር እና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሃሌ ተካ በዋይ ክሮሞዞም ውስጥ የሚገኝ ኤስአርዋይ (SRY) የሚባል ጂን የሰው ልጆችን ፆታ እንደሚወስን ይናገራሉ።
ዶ/ር ሃሌ በመጀመሪያ፣ ሴቶች ኤክስኤክስ (XX) ክሮሞዞም፤ ወንዶች ደግሞ ኤክስዋይ (XY) ክሮሞዞም እንደሚኖራቸው ያስረዳሉ።
የወንዱ ኤክስ (X) እና የሴቷ ኤክስ (X) ሲዳቀሉ XX የያዘ ጽንስ ይፈጠራል።
የወንድ ዋይ (Y) ክሮሞዞም ከሴት ኤክስ (X) ክሮሞዞም ጋር ሲዋሃድ ደግሞ ኤክስ ዋይ (XY) የያዘ ጽንስ ይፈጠራል።
በዋይ ክሮሞዞም ውስጥ የሚገኘው፣ ኤስ-አር-ዋይ (SRY) የሚባል ጂን በሰዎች እና በሌሎች አጥቢ እንስሳት ላይ የሚገኝ ሲሆን ፆታን ይወስናል።
ይህ ማለት 'ኤስ-አር-ዋይ' በሚኖርበት ወቅት የሚፈጠረው ጽንስ ወንድ ሲሆን፣ ይህ ጂን በማይኖርበት ወቅት የምትፈጠረው ጽንስ ደግሞ ሴት ትሆናለች ማለት ነው።
"ወንድ ወይም ሴት መሆንን የሚወስነው በዋይ ክሮሞዞም ላይ የሚገኘው የ'ኤስ-አር-ዋይ' ጂን ነው" ሲሉ ዶክተር ሃሌ ያብራራሉ።
ስለሆነም የሁለቱንም ፆታ የመራቢያ አካል ይዘው የሚፈጠሩ ሰዎች፣ የሁለቱም ፆታዎች ክሮሞዞም ተደበላልቀው ሲወለዱ የሚያጋጥም እንደሆነ ዶ/ር ሃሌ ያስረዳሉ።
እንደ ሕክምና ባለሙያው ገለጻ ከሆነ፣ አንድ ሕፃን ሲወለድ የሚያሳስት (የሁለቱም ፆታ የመራቢያ የአካል ክፍሎች) ይዞ ሲወለድ፣ የጤና ባለሙያው በልጁ ፆታ ላይ ሙሉ ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም።
"የመራቢያ አካል (ብልት) በውጭ ብቻ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሰው ከውጭ ብልት ካለው ከውስጥ ደግሞ በአልትራሳውንድ ወይም በሌሎች መሳርያዎች ሲታይ ልጅ የሚያድግበት ማህጸን ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ከቤተሰብ ጋር መነጋገር እና ምን ሆኖ ይደረግ የሚለውን መወሰን ይቻላል።"
ውሳኔው እንደ ወንድ ለማደግ ከተፈለገ ሴት የሚያስመስሉ የአካል ክፍሎች (ለምሳሌ፡ የኦቫሪ ሆርሞኖች) በቀዶ ሕክምና መወገድ አለባቸው።
እንደ ዶክተር ሃሌ ገለጻ ግን የአንድን ሰው ፆታ የሚወስኑት ውጫዊ የመራቢያ አካላት ብቻ አይደሉም።
"ከውጭ የሚታየውን የሴት ብልት በማስወገድ ብቻ ያ ልጅ ወንድ ሆኖ ያድጋል ማለት አይደለም። የወንድ ልጅ ውጫዊ ሁኔታዎችን የሚወስኑት በዓይን የሚታየው የወንድ ልጅ ብልት አይደለም። የሚያመነጫቸው ሆርሞኖች እንጂ" ካሉ በኋለ ሴት ልጅ ሆና እንድታድግ ከሆነ ፍላጎቱ ብልቱን ብቻ ማስወገድ ሳይሆን ሆርሞን የሚያመነጨው አካል መወገድ እንደሚኖርበት ያስረዳሉ።
በመሆኑም ውጫዊው ገጽታ ብቻውን መላውን የሰው ልጅ የመራቢያ ሥርዓት ሊለውጠው አይችልም ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።
የተኮላሸው የንግሥቲ ህልም
አሁን ንግሥቲ ሰዎች ተገቢ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ ሊነካኳት ስለሚሞክሩ፣ በመቀመጫዋ የተደፈረች እያሉ ስለሚያወሩባት ደኅንነት አይሰማትም።
በክልሉ ደግሞ በርካታ ሰዎች መሳሪያ ስለያዙ እና ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ስላለ በቀላሉ ለሌሎች ጥቃቶች ተጋላጭ ያደርገኛል ብላ ትሰጋለች።
"አሁን በፍርሃት ምክንያት ቤቴን 11:00 ላይ ነው የምዘጋው፤ ሰዎች በማይሳደቡበት፣ ጊዜያቸውን በሥራ የሚያሳልፉ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ለመኖር እመኛለሁ። አሁን ላይ ግን ማንም ሰው ሊሰብረው የማይችል በር ያለበት ቤት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ" ትላለች።
ንግሥቲ ላለፉት አራት ዓመታት ማኅበራዊ ኑሮዋ ማሽቆልቆሉን ገልጻለች።
አብዛኛው ጊዜ በቤት ውስጥ እንደምታሳልፍ፤ አልፎ አልፎ ደግሞ ከእረኛ ሕጻናት ጋር እንደምትውል ትናገራለች።
"ምክንያቱም የሚያስቀኝ ሰው እፈልጋለሁ፤ ሕጻናት ደግሞ የሆንኩትን የደረሰብኝን ስለማያውቁ አእምሮዬን የሚጎዳ ነገር አይናገሩኝም።"
በትምህርቷ ጎበዝ የነበረችው ንግሥቲ እንደ አጀማመሯ ቢሆን ኖሮ በትግራይ ክልል ውስጥ የተሻለ የትምህርት ዕድል በሚሰጥበት ቀላሚኖ አዳሪ ትምህርት ቤት ከሚገቡት ተማሪዎች አንዷ ትሆን እንደነበር በመግለጽ በጥልቅ ሐዘን ይሰማታል።
"ስምንተኛ ክፍል ብደርስ ኖሮ ቃላሚኖ እገባለሁ የሚል ግምት ነበረኝ፤ ተምሬ አካል ጉዳተኞች እና ሴቶች እኔ ያሳለፍኩትን መከራ እንዳያዩ በሙያዬ አስተዋጽኦ ለማድረግ ነበር ምኞቴ" ስትል በሐዘን ትናገራለች።















