ጺም ስለሚያበቅሉ ሴቶች ሳይንስ ምን ይላል?

አያንቱ አድማሱ

የፎቶው ባለመብት, MO'AA TV

አያንቱ አድማሱ በእንስሳት ሕክምና ሳይንስ ከወለጋ ዩኒቨርስቲ ነው የተመረቀችው።

ተወልዳ ያደገችው ደግሞ በቄለም ወለጋ ደምቢ ዶሎ ከተማ ነው።

የአያንቱ ፊት በጢም የተሸፈነ ነው። እንደ እኩዮቿ ወንድ ልጆች ጢም ማብቀል የጀመረችው ወደ ጉርምስና እድሜ ከገባች በኋላ ነው።

በእርግጥ አያንቱ ከሕጻንነቷ ጀምሮ አካሏ ላይ በብዛት ፀጉር እንደነበር እና ከጊዜ በኋላ እንደጠፋ ቤተሰቦቿ እየነገሩ ነው ያሳደጓት።

“ቤተሰቦቼ በሕጻንነቴ ገላዬ በፀጉር የተሸፈነ እንደነበር ይነግሩኛል። ከጊዜ በኋላ ግን ወደ ጉርምስና ዕድሜ ስደርስ ጺም ሆኖ እንደ አዲስ በቀለ። በወጣትነት እድሜ ውስጥ ሆኜ ነው እንግዲህ ጺም እንዳለኝ የተረዳሁት።”

አያንቱ ፊቷን ጺም እንደወረሰው በተረዳች ዕለት እንዴት አብከንክኗት ነበር።

ራሷን ጠላች።

“ሰዎች ሲያዩኝ ከሌሎች ሴቶች ተለይቼ ስለምታያቸው ይናገሩኛል። ታድያ ለምን እንደዚህ ሆነ ብዬ እናደድ ነበር። . . .”

በተለይም ከትውልድ አካባቢዋ ወደ ወለጋ ዩኒቨርስቲ፣ ነቀምቴ ከሄደች በኋላ ብዙ ገጠመኞች እንዳሳለፈች ትናገራለች።

“በተወለድኩበት አካባቢ ብዙ ሰዎች ስለሚያውቁኝ ምንም አይሉኝም ነበር። ነገር ግን ለትምህርት ከዚያ አካባቢ ከሄድኩ በኋላ የሸሹኝ ሰዎች ነበሩ። የሚደነግጡም ነበሩ። የሰደቡኝም፤ ያሞገሱኝም አሉ።

“ግማሾቹ ‘ይህች ልጅ ጤነኛ አይደለችም’ ያሉም ነበሩ” በማለት ከትውልድ መንደሯ ከራቀች በኋላ የገጠማትን ታስታውሳለች።

በተለይም የፀጥታ አካላት የአካባቢውን ደኅንነት ለመጠበቅ ፍተሻ ሲያደርጉ በጺሟ የተነሳ፣ ከሌሎች ሰዎች በተለየ እርሷን አጥብቀው እንደሚጠይቋት ትናገራለች።

“ደምቢዶሎ እያለሁ ራሱ መታወቂያዬን ሳልይዝ ሱቅ ሄጄ እቃ ገዝቼ አልመለስም ነበር። ወንድ ነው ፀጉሩን እንደዚህ አሳድጎ ከተማ የገባው በማለት ይመረምሩኝ ነበር።”

ዩኒቨርስቲ ከገባች በኋላም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እያለች፣ አንድ መምህሯ ተማሪዎች ስማቸውን እየተናገሩ ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ጠየቃቸው።

እርሷም እንደ ማንኛውም ተማሪ “አያንቱ እባላለሁ” በማለት ራሷን አስተዋወቀች።

መምህሩ ደግሞ “ስምሽ እና ፊትሽ አንድ አይደለም” በማለት ሴት መሆኗን በጥርጣሬ ማየቱን ታስታውሳለች።

በኋላም “ጺም አለኝ እንጂ እኔ ሴት ነኝ” በማለት አስተማሪዋን ማስረዳቷን ለቢቢሲ ተናግራለች።

የሴት ልጅ ጺም እና ጤና

ጺም ማብቀሏ የፈጣሪ ስጦታ መሆኑን የምታምነው አያንቱ፣ ብዙ ሰዎችም እንዳትላጨው ቢመክሯትም እርሷ ግን ለተወሰነ ጊዜ ስትላጨው ነበር።

“ከፊቴ ላይ ለማጥፋት ብዬ የተለያዩ ቅባቶችን እቀባ ነበር። ቤተሰቦቼ ግን እንዳላጠፋው ይነግሩኝ ነበር። በተለይም እናቴ ‘ልጄ እንደ እናቴ ጺም አላት’ ብላ በጣም ትደሰት ነበር።”

በተለይ የወንድ ጓደኛዋ ጺሟን ወድዶ ለፍቅር እንደጠየቃት ትናገራለች።

ከጓደኛዋ ጋር ፍቅር ከጀመረች በኋላም “ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ስለሆነ እንዳትቆረጪው በማለት ያበረታታኛል” ትላለች።

ይህንኑ ጺሟን በተመለከተ የጤና ባለሙያ ለማናገር ቀጠሮ ይዛ የነበረ ቢሆንም፣ የትምህርት ዕድል በማግኘቷ በቀጠሮዋ ላይ ሳትገኝ ቀርታለች።

“ከዚያ በኋላም ምን ይሰራልኛል ብዬ ተውኩት” ትላለች።

በአምቦ ዩኒቨርስቲ የማህፀን እና ጽንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አዲሱ ግርማ በወንዶች ላይ ብቻ የሚወጣ ፀጉር በሴቶች ላይ ሲወጣ ችግር እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወንዶች በተፈጥሮ በፊት እና በደረታቸው ላይ ፀጉር ይበቅላል። ሴቶች ደግሞ በተፈጥሮ ይህንን ፀጉር አያበቅሉም።

በመሆኑም እንደ አያንቱ ሴቶች ጺም ካበቀሉ የሆርሞን መጠን መዛባት ምልክት መሆኑን እና ሕክምናም ያለው ነው።

ይህ መዛባትም በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰት መሆኑን የሚናገሩት የሕክምና ባለሙያው፣ በሳይንሳዊ ስሙ “ሂርስቲዝም (Hirstism)” እንደሚባል ይባላል።

የ‘ሂርስቲዝም’ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሴቶች ጺም ወይንም በወንዶች ላይ ብቻ የሚበቅል ፀጉር እንዲያበቅሉ የሚያደርጋቸው አንድሮጂን የሚባል የወንዶች ሆርሞን በብዛት በሰውነታቸው ውስጥ በሚፈጠርበት ጊዜ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

“በተለይም የወንዶች ሆርሞን ‘ቴስቴስትሮን’ በሴቶች ላይ በብዛት ሲፈጠር፣ ይህ ችግር እነርሱን ያጠቃል” በማለት ያብራራሉ ዶ/ር አዲሱ።

የወንዶች ቴስቴስትሮን በተፈጥሮ በአነስተኛ መጠን ሆኖ በሴቶች ውስጥ እንደሚገኝ የሚናገሩት ዶ/ር አዲሱ፣ ይህም ብዙ ጠቀሜታ አንዳለው አብራርተዋል።

እንደ ሕክምና ባለሙያው ገለጻ ይህ ሆርሞን በትክክለኛ መጠን ከተገኘ ለሴቶች ጡንቻ ግንባታ እና የአጥንት ጥንካሬ ጠቀሜታ አለው።

እንዲሁም ሴቶች በተራክቦ ወቅት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ይህ የወንዶች ሆርሞን በሴቶች ሰውነት ውስጥ ሁለት ደረጃ እንዳለው ዶ/ር አዲሱ ያስረዳሉ።

“ከአማካኝ መጠኑ ከፍ ካለ የሂርስቲዝም ወይንም ጺም እንዲያበቅሉ ያደርጋቸዋል። በጣም ከፍ ካለ ደግሞ ቪሪላይዜሽን (virilization) የሚል ችግር ያስከትላል።”

“በቪሪላይዜሽን ሁኔታ በውስጥ ያሉ ሴቶች ደግሞ እንደ ወንዶች ራሰ በራ መሆን፣ ድምጻቸው እንደ ወንዶች መጎርነን እና ተፈጥሯዊ ጡንቻቸው እንደ ወንዶች መፈርጠም የመሳሰሉትን ይከሰታል” ይላሉ።

አያንቱ ግን ጺም ከማብቀል ውጪ እስካሁን ድረስ ሌሎች ምልክቶች እንዳልታዩባት ትናገራለች።

የወንዶች ሆርሞን በሴቶች ውስጥ መብዛት ለዚህ ዓይነት መዛባት እንዲጋለጡ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም (polycystic ovary syndrome) የሚባል በሽታ ነው።

በጆንስ ሆፕኪንስ ሜዲስን ድረገጽ ላይ ያለ መረጃ አንደሚያሳየው ከሆነ ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም የሚፈጠረው የሴቶች ኦቫሪ ትክክለኛ ያልሆነ የወንዶች አንድሮጂን ሆርሞን በሚያመነጭበት ጊዜ ነው።

ይህ ደግሞ የሴቶች የወር አበባ ዑደቱን ጠብቆ እንዳይመጣ ያደርጋል።

የሂርስቲዝም በሽታ ምክንያቶች ከ80 ከመቶ በላይ ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም እንደሆነ እና ለሌሎች ችግሮች የሚታዘዙ መድኃኒቶች የወንዶች ሆርሞን በሴቶች ውስጥ እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ዶ/ር አዲሱ ይገልጻሉ።

“ለምሳሌ ለሚጥል በሽታ የሚወሰዱ መድኃኒቶች የወንዶች ሆርሞን በሴቶች ሰውነት ውስጥ ከፍ እንዲል ሊያደርጉ ይችላሉ። የአድሪናሊን ዕጢ ሆርሞኖችም ይህ የወንዶች ሆርሞን በሴቶች ውስጥ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላሉ” ብለዋል።

የሕክምና መፍትሄ አለው?

ጺም እንዲያበቅሉ ወይንም ሂርስቲዝም የሚባል መዛባት ያጋጠማቸው ሴቶች በአፋጣኝ የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ይህ ካልሆ ግን ውሎ አድሮ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል፣ በሦስት ምክንያቶች የሕክምና ክትትል እንዲያደርጉ ዶ/ር አዲሱ ይመክራሉ።

“በተለይም የኦቫሪ ዕጢ ወይንም አድሪናል ዕጢ ይህ ሴቶች ጺም እንዲያበቅሉ የሚያደርገው መዛባት ሴቶችን ለበለጠ የጤና ችግር ሊያጋልጥ ይችላል።

“በሌላ በኩል ደግሞ የፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ችግር ሌሎች እንደ ስኳር በሽታ፣ መካንነት፣ የወር አበባ ዑደት ጊዜውን ጠብቆ እንዳይከሰት በማድረግ እና የማሕፀን ካንሰር የመሳሰሉት በሽታዎችን ሊያስከትል ስለሚችል ነው” ይላሉ።

የዚህ የሂርስቲዝም ተጠቂ ሴቶች የሚያጋጥማቸው ችግር በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሚከሰት መገለል እና ጥቃት ስለሚጋለጡ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንዳለባቸው ይመክራሉ።

ይህን እክል ለማከም በሽታው ከምን እንደመነጨ በምርመራ መረጋገጥ እንዳለበት ዶ/ር አዲሱ ይናገራሉ።

“ይህ በሽታ ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ሊሆን ይችላል። ሆርሞንን በብዛት የሚያመነጭ ዕጢ ሊኖር ይችላል። ስለዚህ በአልትራሳውንድ ታይቶ፣ የቴስቴስትሮን ሆርሞን ተለክቶ፣ ይህንን ምን እንዳስከተለ ከተለየ በኋላ ተገቢውን ሕክምናን ማግኘት ይቻላል።”