ለሞት አደጋ የሚያጋልጠው ‘ቢቢኤል’ የተባለው የመቀመጫ መጠን የሚያሳድገው ሕክምና

ካይሮ ናካቴ-ቺርዋ

የፎቶው ባለመብት, Cairo Nakhate-Chirwa

ካይሮ ናካቴ-ቺርዋ ባለፈው ሰኔ ነው ‘ቢቢኤል’ የተባለውን መቀመጫ የሚያሳድግ ሕክምና ያገኘችው።

በውጤቱ ደስተኛ ናት። “መቀመጫዬን አሳድጎልኛል” ትላለች። ነገር ግን ይህ ሕክምና አደጋ እንዳለው ስትሰማ ስጋቷ መጨመር ጀምሯል።

ይህን ሕክምና ያገኘችው አሊስ ዌብ መሞቷን ተከትሎ በሕክምናው ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ብራዚሊያን በት ሊፍት አሊያም ቢቢኤል ያለቀዶ ጥገና ሊደረግ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ይህ ሕክምና የሚደረገው የመቀመጫ መጠንን የሚያሳያድግ ፈሳሽ በመርፌ በመስጠት ነው።

ይህ ሕክምና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ቁጥጥር አይደረግበትም። በድብቅ የሚሰጡት ሕክምናዎች ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ባለሙያዎች ይጠይቃሉ።

ካይሮ ባለፈው ሰኔ ነው በፈሳሽ የሚሰጠውን የመቀመጫ ማሳደጊያ ኢንስታግራም ላይ ያገኘችው። ይህ ሕክምና ሊኪዊድ ቢቢኤል ይባላል።

ኢንስታግራም ላይ ያገኘችው ማስታወቂያ ይህ ሕክምና በ1200 ፓውንድ እንደሚሰጥ ይናገራል።

ማስታወቂያውን ካየች ከ24 ሰዓታት በኋላ ለንደን ወደሚገኝ አንድ አፓርትማ ለሕክምናው ተገኘች።

ይህን ሕክምና የሚሰጣት ግለሰብ ፕሮፌሽናል ስለመሆኑ ያረጋገጠችው ነገር የለም። “ማስታወቂያውን ሳየው ፕሮፌሽናል ይሆናሉ ብዬ ገምትኩ” ትላለች።

ቢቢሲ ለካይሮ ይህን ሕክምና የሰጣትን ግለሰብ ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ካይሮ እንደምትለው ሕክምናው በተሰጣት ወቅት “ሕመም” ተሰምቷት ነበር። ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ መርፌው በገባበት ቆዳዋ አካባቢ ፈሳሽ ነገር ተመልክታለች። ከዚህ ውጭ ምንም ጉዳት አልገጠመኝም ትላለች።

ነገር ግን የአሊስ ዌብ መሞትን ስትሰማ ስለሕክምናው የጎንዮሽ ጉዳት ማጥናት ጀመረች። ምንም እንኳ እስካሁን የጎንዮሽ ጉዳት ባይገጥማትም፤ ሕክምናውን መውሰዷ እንደሚቆጫት ትናገራለች።

“በውጤቱ ደስተኛ ነኝ። ርካሽ ነበር። ነገር ግን አሁን ብዙ ጥያቄ እየተፈጠረብኝ ነው።”

አሊስ ዌብ

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, አሊስ ዌብ መሞቷን ተከትሎ በሕክምናው ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ያለቀዶ ጥገና የሚሰጥ ቢቢኤል

ያለቀዶ ጥገና የሚሰጥ ቢቢኤል ማለት እንደስሙ ቀዶ ጥገና ሳይደረግ በመርፌ ብቻ የሚሰጥ ነው።

ይህ ሕክምና በክሊኒክ ሊሰጥ የሚችል ቢሆንም ዩኬ እና የተለያዩ ሀገራት ውስጥ በሆቴል ክፍሎች ጭምር እየተሰጠ እንደሆነ ይነገራል።

ሴቭ ፌስ የተባለ አንድ ተቋም ያጠናው ጥናት እንደሚለው በርካታ ሰዎች የሚወጉት ነገር ምን እንደሆነ አያውቁትም።

ይህ ፈሳሽ ሀይሉሮኒክ አሲድ እና ፖሊ ኤል ላክቲክ አሲድ ሊሆን ይችላል። የእንግሊዙ የጤና አገልግሎት ኤንኤችኤስ ያለቀዶ ጥገና የሚሰጥ ቢቢኤል አይመከርም ይላል።

በቀዶ ጥገና የሚሰጥ ቢቢኤል ከአንድ የሰውነት ክፍል ስብ በመምጠጥ ወደ መቀመጫ ማዘዋወር ሊሆን ይችላል። ይህ ሕክምና ብዙውን ጊዜ የሚሰጠው በቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ ነው።

በቀዶ ጥገና ሕክምና የሚሰጥ ቢቢኤል እያስከተለ ያለውን ሞት ተከትሎ የብሪታኒያ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ማሕበር በአውሮፓውያኑ 2018 ለአራት ዓመታት እንዲታገድ ብሎ ነበር።

ማሕበሩ በ2022 አዲስ የቢቢኤል ቀዶ ጥገና መመሪያ ቢያወጣ ይህ ሕክምና አሁንም አደጋ እንዳለው ያስጠነቅቃል።

ለደንበኞቿ የቢቢኤል ቀዶ ሕክምና የምትሰጠው ዶክተር ሶፊ ሾተር “አብዛኛዎቹ ደንበኞቼ ሕክምናው ምን እንደሆነ አያውቁትም” ትላለች።

ያለቀዶ ጥገና የሚሰጠውን ሕክምና አልፈፀምም የምትለው ዶክተሯ ምንም እንኳ ካይሮ እስካሁን ምንም ባትሆንም አደጋ እንዳለው ግን መታወቅ አለበት ባይ ናት።

ፈሳሹ መቀመጫ ላይ በሚወጋበት ወቅት የደም መዘዋወርን ሊዘጋ እንደሚችል እና ይህ የደም መርጋት ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

ይህ ደግሞ ለሞት ሊያጋልጥ ይችላል።

ቁስለት፣ ጠባሳ፣ የሰውነት ቅርቀፅ መቀያየር እንዲሁም ከሕክምናው የሚመነጩ የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶችም ሊከተሉ ይችላሉ።

የብሪታኒያው የቀዶ ጥገና ባለሙያዎች ማኅበር እንደሚለው ከሌሎች ያለቀዶ ጥገና ከሚሰጡ ሕክምናዎች በላቀ ቢቢኤል ለሞት የማጋለጥ ዕድሉ የሰፋ ነው።

ላቪዳ ሎካ በተሰኘ የመድረክ ስሟ የምትታወቀው ካይሮ በተለይ ሴቶች “በሂፕ-ሆፕ ሙዚቃ ኢንዱስትሪው መቀመጫቸው ተለቅ እንዲል ይጠበቃል” ትላለች።

የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ሕክምና አካላዊ ጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ የፍቅር ግንኙነትን ሊያፍርስ እና የአእምሮ ጤናንም የማቃወስ አቅም አለው።