ሎክ፡ አሜሪካ ውስጥ በቻይናውያን ለቻይናውያን የተገነባችው ከተማ

በሎክ የጎዳና ስሞች በእንግሊዘኛ እና ቻይና ቋንቋ ነው የሚጻፉት

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, በሎክ የጎዳና ስሞች በእንግሊዘኛ እና ቻይና ቋንቋ ነው የሚጻፉት

ቻይናውያን ምንም ያልነበረበትን መካከለኛው ካሊፎርኒያን ጥረው ግረው በአንድ ወቅት “የካሊፎርኒያ ሞንቴ ካርሎ” ተብላ የምትጠራ ከተማን ፈጥረው ነበር።

ከሳክራሜንቶ በስተደቡብ አቅጣጫ ከሳክራሜንቶ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኘው ለም መሬት በጊዜ ሂደት ስደተኞች የሚሰፍሩበት አካባቢ ሆኖ ቆይቷል።

በቦታው የምትገኘው ሎክ ከተማ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ለቻይናውያን፤ በቻይናውያን የተገነባች ከተማ ተደርጋ ቦታ ተሰጥቷታል።

ሎክ ከተማ በጠባብ መንገዶቿ እና ከጠንባብ መንገዶቿ ፊት ለፊት በተሰደሩት ከእንጨት በተሰሩ መኖሪያ ቤቶች በስፋት ትታወቃለች።

ከተማዋ ዛሬ ላይም ቢሆን ጥንታዊነቷን ጠብቃ የኖረች የቻይና መንደር የሚል ስያሜን ይዛለች። ከተማዋን የመሠረቱ ቻይናውያን ትውልዶች ኑሯቸውን ያደረጉባት እና ንግዳቸውን ያንቀሳቀሱባት ሆና ለዓመታት ዘልቃለች።

በ1848 በካሊፎርኒያ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት የመኖሩ ዜና በስፋት ሲሠራጭ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአሜሪካ እና ከተቀረው ዓለም ወደ ካሊፎርኒያ ተመው ነበር።

ከእነዚህ መካከል ወርቅ አምርተው ባለጸጋ መሆንን ያለሙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቻይናውያን ወደ ካሊፎርኒያ አቅንተዋል።

ቻይናውያኑ “የወርቅ ተራራ” ብለው በሚጠሯት ካሊፎርኒያ እንደደረሱ ስኬታማ መሆን ችለው ነበር።

ይሁን እንጂ የአካባቢው ተወላጆች ቻይናውያኑን ከአካባቢው ለማፈናቀል ግብር ከመጣል አልፈው ሌሎች ማዕድን አውጪዎች ቻይናውያን ላይ ዒላማ ያደረገ የኃይል ጥቃት መፈጸም ጀመሩ።

ሎክ በጠባብ መንገዶቿ እና ከእንጨት በተሰሩት መኖሪያ ቤቶች ትታወቃለች።

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, ሎክ በጠባብ መንገዶቿ እና ከእንጨት በተሰሩት መኖሪያ ቤቶች ትታወቃለች።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህም ምክንያት ቻይናውያኑ ወርቅ ከማምረት ይልቅ ፊታቸውን ወደ ግብርና እና ወደ የባበሩ ሐዲድ ግንባታ አዞሩ።

በግብርና ሥራቸው ለእርሻ ምቹ ያልነበሩ ረግረጋማ መሬቶችን በጠንካራ ጥረት ምቹ ወደ ሆኑ የእርሻ ስፍራዎች መቀየር ቻሉ። በወርቅ ያጡትን ገንዘብ በእርሻ ማግኘት ቻሉ።

ይህ የቻይናውያኑ ስኬት ረግረጋማ ከሆነ መሬት ውሃን በማውጣት የግንባታ ሥራን በመሥራት የተካኑ ተጨማሪ ቻይናውያን ከጉዋንግዶንግ ግዛት ወደ ካሊፎርኒያ እንዲሰደዱ አደረገ።

ቻይናውያኑ በግብርና ሥራቸው ስኬታማ ሆኑ። ለመኖር ምቹ ያልነበሩ አካባቢዎችን መንጥረው እና ረግረጋማውን መሬት አስተካክለው መንደር እና ከተማን መሠረቱ።

ነጮቹ የአገሬው ሰዎች ግን ሥራ እና መሬታችን በመጤዎች ተወሰደብን በማለት ቻይናውያንን ማጥቃት ጀመሩ።

መንግሥትም የቻይናውያንን መብት በእጅጉ የገደቡ ሕጎችን ማርቀቅ ጀመረ።

እአአ 1872 ላይ ካሊፎርኒያ ቻይናውያን የመሬት ባለቤት እንዳይሆኑ እንዲሁም የንግድ ፍቃድ እንዳያወጡ የሚከለክል ሕግ አረቀቀች።

በመቀጠልም የአሜሪካ መንግሥት እአአ 1941 ላይ የተሠረዘውን ቻይናውያን ወደ አሜሪካ በስደት እንዳይገቡ እና ዜግነት እንዳያገኙ የሚከለክል ሕግ እአአ 1882 ላይ አወጣ።

ምንም እንኳ ክልከላው ቢበዛባቸው ቻይናውያን በዋልነት ግሮቭ የቻይናውያን ከተማን መገንባት ቻሉ። ይህ ከተማ በ1880ዎቹ ከ800 በላይ ቻይናውያንን እና ጥቂት ጃፓናውያን ስደተኞችን ያኖር ነበር።

እአአ 1915 ላይ ግን ድንገተኛ እሳት ተነስቶ ከተማዋን ወደ አመድነት ቀየራት።

እሳት የብዙ ዓመት ጥረታቸውን ካወደመባቸው ቻይናውያንን መካከል ታዋቂው ሊ ቢንግ አንዱ ነበር።

ቻርሊ በመባል የሚታወቀው ሊ ቢንግ፤ በዋልነት ግሮቭ ባሉት የንግድ ድርጅቶቹ እና እንግሊዝኛ በመናገር በብዙዎች ይታወቅ ነበር።

በ1900 መጀመሪያዎች አሜሪካ ከደረሰ በኋላ ከቁማር ቤት እስከ ፀጉር ቤት፤ ከቻይና ባሕላዊ መድኃኒት መደብር መሸጫ እስከ የግንባታ ግብዓቶች መሸጫ ሱቅ ነበረው። 1915 ላይ የተነሳው እሳት ለዓመታት በላቡ የገነባውን ሐብት ወደ አመድነት ቀየረበት።

መሬት በስማቸው መግዛት የማይችሉት እና የንግድ ፍቃድ ማውጣት የማይፈቀድላቸው ቻይናውያን ከነጭ አሜሪካውያን ጋር ውል በማሰር ዳግም ቤቶችን መገንባት ጀመሩ።

በቢንግ የሚመራ የቻይናውያን ኮሚቴ ጆርጅ ሎከር ከሚባል ነጭ አሜሪካዊ ነጋዴ ጋር ከስምምነት በመድረስ ቻይናውያኑ ቤት ለሚገነቡበት መሬት ኪራይ በየወሩ ከ5 አስከ 10 ዶላር ለመክፈል ተስማሙ።

ሎክ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የንግድ ቤት ገንብቶ መሬት ለመጠቀም 10 ዶላር እንዲሁም ለመኖሪያ ቤት ለሚሆን መሬት 5 ዶላር ወረሃዊ ክፍያ በመፈጸም በአሜሪካዊው ነጋዴ እና በቻይናውያኑ መካከል የተደረሰው ስምምነት ለዓመታት ዘለቀ።

ቻይናውያኑ በሎክ ከተማ ልጆቻቸው የቻይናን ባሕል እና ቋንቋ የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ጭምር ማቋቋም ችለዋል።

እአአ 1940 ላይ ከተማ በግምት ወደ 600 የሚጠጉ ነዋሪዎች ነበሯት። አብዛኞቹ ነዋሪዎች ቻይናውያን ሲሆኑ፣ በከተማዋ 6 ምግብ ቤቶች፣ 6 መደብሮች፣ 1 ሆቴል እና 1 ወፍጮ ቤት ነበረው። ከተማዋ ሌላ የምትታወቅበት ነገር ሕገ-ወጥ በሆኑ የቁማር ቤቶቿ ነበር።

በአንድ ወቅት የሳክራሜቶ ጋዜጦች ከተማዋን የካሊፎርኒያ ሞንቴ ካርሎ ሲሉ ይገልጿት ነበር።

እአአ 1960ዎቹ ላይ የሎክ ነዋሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ቀነሰ። ቻይናውያን ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እአአ 1943 ላይ ሲነሳ በርካታ ቻይናውያን የተሻለ ዕድልን ፍለጋ ወደ ሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ተሰደዱ።

አሁን ላይ የነዋሪዎቿ ቁጥር ከ60 ሰዎች አይዘልም። ከእነዚህ መካከልም ቻይናውያን የሆኑት በጣም ጥቂቶች ናቸው።

1990 ላይ ሎክ የአሜሪካ ብሔራዊ ታሪካዊ ስፍራ ተብላ በአገሪቱ መንግሥት ተመዝግባለች።

በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ለዓመታት የመሬት ባለቤትነት መብት ሳይኖራቸው ቤት ለገነቡበት መሬት ወርሃዊ ክፍያ ሲከፍሉ ለኖሩ ቻይናውያን የልጅ ልጆች የመሬት የባለቤትነት መብት ተሰጥቷቸዋል።

በድሮው ዘመን በቻይናውያኑ የተገነቡ ሕንጻዎች ዛሬም ድረስ ጥቅም ላይ ይውላሉ።

የቀድሞ ቁማር ቤቶች ዛሬ ላይ ሙዚየም ሆነዋል። የቻይናውያን ትምህርት ቤት የነበረው ሕንጻ ዛሬ ላይ ወደ ሙዚየምነት ተቀይሯል። በሙዚየሙ ውስጥ ከ100 ዓመት በፊት ቻይናውያን ልጆች ሲጠቀሙበት የነበረው ወንበር እና ጠረጴዛን ማየት ይቻላል።