በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት እና የመንገዶች መዘጋት የደቀኑት የጤና ቀውስ

መድኃኒት እና ክትባቶችን ማግኘት አዳጋች መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Health Bureau

የምስሉ መግለጫ, መድኃኒት እና ክትባቶችን ማግኘት አዳጋች መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በአማራ ክልል የተከሰተው አለመረጋጋት ተባብሶ ወደ ለየለት የትጥቅ ግጭት ካመራ ወራት ተቆጥረዋል። በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የሚካሄደው ግጭት በሕዝቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ ከባድ ጫናን እያሳረፈ ነው።

በዚህም ሳቢያ የሕዝቡ መደበኛ እንቅስቃሴዎች የተስተጓጎሉ ሲሆን፣ የመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች፣ የትራንስፖርት፣ የንግድ፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች በጉልህ በሚታይ ሁኔታ መደናቀፍ እንደገጠማቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የሕይወት እና የሞት ጉዳይ የሆነው የጤና አገልግሎት የማግኘት ጉዳይ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል።

ከእነዚህም መካከል መደበኛ ክትትል እና ህክምና የሚያስፈልጋቸው እናቶች እና ህጻናት እንዲሁም የተለያዩ ዘላቂ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት በብዙ ቦታዎች ላይ አስፈላጊ የሆኑ የጤና አገልግሎቶችን ለማግኘት ህሙማን ወደ ጤና ተቋማት መሄድ አለመቻልን ጨምሮ የመድኃኒት እና ሌሎች የህክምና ግብዓት እጥረት እንዲሁም የጤና ተቋማት ሥራ ማቆም እየተስተዋለ ነው።

በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከሚያስፈጽሙ የዕዝ ማዕከላት አንዱ የሆነው የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ከሳምንታት በፊት ከደብረ ብርሃን ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድን ላልተወሰነ ጊዜ በመዝጋት ከእንቅስቃሴ ውጪ ማድረጉ ሌላ ጫናን መፍጠሩን ነዋሪዎች እና የጤና ባሙያዎች ይናገራሉ።

ከየካቲት 16/2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተዘጋው የመንገድ ትራንስፖርት መስመር በደብረ ብርሃን - በሸዋ ሮቢት እና በደሴ መካከል ያለ 267 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የፌደራል አውራ ጎዳና ነው። በዚህም ሳቢያ ነዋሪዎች የተለያዩ ችግሮች እንደገጠሟቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ለወሊድ ወጥቶ ወደ ቤት ለመመለስ መቸገር

ወ/ሮ ሲሳይ* (ስሟ የተቀየረ) ከደብረ ብርሃን - ደሴ የሚወስደው መስመር እስትንፋሱ በሆነው በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኤፍራታና ግድም ወረዳ በምትገኘው የአነስተኛዋ ከተማ ማጀቴ ነዋሪ ናት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚች ከተማ የመንግሥት ሥራተኛ የሆነችው ወ/ሮ ሲሳይ፤ ሁለተኛ ልጇን ለመገላገል የሰዓታት ዕድሜ ሲቀራት ነበር የመንገድ መዘጋት ውሳኔው ይፋ የሆነው።

የመጀመሪያ ልጇን በቀዶ ህክምና (ኦፕራሲዮን) በመውለዷ ሁለተኛ ልጇን ክትትል ስታደርግበት በነበረበው የማጀቴ ጤና ጣቢያ ሳይሆን ከፍ ባለ ሆስፒታል መውለድ እንዳለባት ተነግሯት ነበር።

አርብ የካቲት 15/2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ላይ ምጥ እንደጀመራት የምትናገው ወ/ሮ ሲሳይ፤ “አሁን መውጣት አይቻልም፤ ለሕይወት አስጊ ነው” በመባሏ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል መሄድ አለመቻሏን ትናገራለች።

“ምጥ እንደጀመረኝ [ወደ ሆስፒታል] መሄድ ነበረብኝ ግን አልሄድኩም።...ማታ መሄድ ሲገባኝ አደርኩ” በማለት ሁኔታውን ትገልጻለች።

በአካባቢው አለመረጋጋት ቢኖርም ከነበረችበት የጤና ሁኔታ አንጻር በተገኘው መንገድ ወደ ሆስፒታል መሄዷ የግድ ስለነበረ ሌሊት 10፡00 ሰዓት ላይ ወደ ኮምቦልቻ ሆስፒታል ጉዞ ጀመሩ። መንገድ ላይ ያገኟቸው የፀጥታ ኃይሎች “ከእናንተ ውጭ ማንም አይገባም፤ አይወጣም” ብለዋቸው ጉዟቸውን ቀጠሉ።

ከሰዓታት በኋላም የአማራ ክልል ዞኖች የሆኑትን ሰሜን ሸዋን እና ደቡብ ወሎን የሚያስተሳስረው ዋነኛው መንገድ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱ ተነገረ።

ወ/ሮ ሲሳይ ሆስፒታል ደርሳ ልጇን በሰላም ብትገላገልም ወደ ሞቀው ቤቷ ተመልሳ ለመታረስ ግን አልቻለችም። ለ11 ቀናት ወደ ቤቷ መመለስ ሳትችል በዘመድ ቤት ተጠልላ የአራስነት የመጀመሪያ ሳምንቶችን ለማሳለፍ ተገዳለች።

“አምቡላንስ መጥቶ እንዲወስደኝ ፈቃደኛ አልነበሩም” ስትል ቤቷ ለመመለስ የነበረውን ፈተና የምትገልጸው ወ/ሮ ሲሳይ፤ ውስጥ ለውስጥ ባሉ መንገዶች አቆራርጣ የቀናት ዕድሜ ያለውን ጨቅላ ልጇን ይዛ “በእቃ መጫኛ ባጃጅ” ለቤቷ መብቃቷን ትናገራለች።

የመንገድ መዘጋት ጦስን የተረዱ የማጀቴ ጤና ጣቢያ ባለሙያዎች በተለይ ነፍሰ ጡር እናቶች በሰላም እንዲገላገሉ ከመውለጃ ቀናቸው በፊት ወደ ሆስፒታል እንዲሄዱ ያመቻቻሉ።

ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የጤና ጣቢያው ባለሙያ የእናቶችን ሕይወት ለመታደግ “በኦፕሬሽን የወለዱ የግድ ሆስፒታል መውለድ ያለባቸውን ቀድሞ ምጥ ሳይመጣ እየላክን ነው” ይላሉ።

የእናቶችን ሕይወት ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ለአደጋ በተጋለጠ ሁኔታ፣ አመቺ ባልሆኑ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መጓዝ የግድ መሆኑን የሚናገሩት የጤና ባለሙው፣ የአካባቢው ሕዝብም እናቶች እና በጠና የታመሙ ሰዎችን በዙሪያ ወደሚገኝ ሆስፒታል ለማድረስ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

መንገድ በመዘጋቱ እና ትራንስፖርት ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ወደ ከፍተኛ የህክምና ተቋማት ለመሄድ ፈታኝ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, Amhara Health Bureau

የምስሉ መግለጫ, መንገድ በመዘጋቱ እና ትራንስፖርት ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ወደ ከፍተኛ የህክምና ተቋማት ለመሄድ ፈታኝ ሆኗል

መድኃኒት አጥቶ ሞትን መጠበቅ

በአማራ ክልል ግጭት በሚካሄድባቸው በርካታ አካባቢዎች የሚደርስ ጉዳትን በመፍራት ተሽከርካሪዎች ከእንቅስቃሴ የሚቆጠቡባቸው ጊዜያት በርካታ በመሆናቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ያዝ ለቀቅ እንደሚል ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የደብረ ብርሃን - ደሴ መንገድ ግን በአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ውሳኔ መሠረት “ለሕዝቡ ደኅንነት” ሲባል በይፋ የተዘጋ መንገድ ነው።

በዚህም ሳቢያ የተዘጋውን መንገድ ለዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚጠቀሙት የአካባቢው ነዋሪዎች ወደሌሎች ቦታዎች በመሄድ በርካታ አገልግሎቶችን ከማግኘት መስተጓጎላቸውን ይገልጻሉ። በተለይ የጤና ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በከፍተኛ የጤና ተቋማት መታከም ያለባቸው ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አቶ አሳልፍ ከሁለት ዓመት በፊት በገጠማቸው የነርቭ ህመም ምክንያት አካላቸው ማንቀሳቀስ ከማይችሉበት ደረጃ (ፓራላይዝድ) ላይ ደርሰው ነበር።

ጤናቸውን ለመመለስ በሐኪም የታዘዘላቸው መድኃኒትም ከደሴ ሆስፒታል ይመጣላቸው እንደነበር የሚናገሩት አቶ አሳልፍ፤ አሁን መንገድ በመዘጋቱ “ክትትል ማድረግም፣ በጣም አስፈላጊ የሆነውን መድኃኒትም መግኘት አልቻልኩም። አሁን አልጋ ላይ ነኝ” ይላሉ።

ከግጭቱ መባባስ በኋላ መድኃኒታቸውን በመጨረሳቸው ለመቋረጥ ተገደዋል። አማራጭ በማታጣቸውም አሁን መራመድ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው የአልጋ ቁራኛ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ጦርነት አለ። መንቀሳቀስ አይቻልም። እንኳን እንደ እኔ ዓይነቱ በሽተኛ ይቅርና እግርም ያለው መራመድ አይችልም። ሞት ነው የሚጠብቀን። በሽታው ቶሎ ቢገድል ጥሩ ነበር፤ ግን አይደለም” በማለት ተስፋ መቁረጣቸውን ይገልጻሉ።

በመድኃኒት እጦት የእናትና ልጅ ስቃይ

የ18 ዓመት ልጃቸው የአዕምሮ መታወክ ችግር እንዳለበት የሚናገሩት ወ/ሮ ተዋበች፤ ልጃቸው ከ15 ዓመቱ ጀምሮ የሚወስደውን መድኃኒት ከደሴ አሊያም ከደብረ ብርሃን ያገኙ እንደነበር ያነሳሉ።

አሁን ግን ወደ ሁለቱም ከተሞች የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ ለልጃቸው ጤንነት እጅግ አስፈላጊ የሆነውን መድኃኒት ባለማግኘታቸው በማቋረጡ “በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መድኃኒቱ ለልጃቸው ጤና ወሳኝ መሆኑን “መድኃኒቱን ካጣ ምንም አይረጋጋም፤ እረፍት የለውም” ሲሉ የልጃቸውን የጤና ሁኔታ የሚገልጹት እናት፤ እሳቸውም ሆኑ ልጃቸው “ስቃይ” ላይ መሆናቸውን በምሬት ይናገራሉ።

በተለያዩ የጤና ችግር ውስጥ ያሉ እና አስፈላጊ ክትትል የሚያስፈልጋቸው የማጀቴ ነዋሪዎች ወሳኝ የጤና አገልግሎቶችን ከሆስፒታሎች ለማግኘት የተለያዩ ጥረት እንደሚያደርጉ የአካባቢው የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ለዚህም የሚደረገው ጉዞ ከዋናው መንገድ ውጪ በመሆኑ ክፍያው ኪስን በሚፈትኑ እንዲሁም አድካሚ በሆኑ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መድኃኒት እና ህክምና ለማግኘት ዋጋ እየከፈሉ ነው።

ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ለዓመታት ሲወስደው የቆየው መድኃኒት ለተቋረጠበት ልጃቸው መድኃኒት ለማግኘት ይህንን መንገድ መከተል ለእሳቸው ዓይነቱ “ደሃ የማይሆን ነው” ይላሉ ወ/ሮ ተዋበች።

“እስከ አምስት ሺህ ብር ድረስ ያስፈልጋል፤ ለእንደኔ ዓይነቱ ብዙ ነው። በአንድ ቀን ደርሶ መልስ መምጣት ስለማይቻል ማደሩ ደግሞ ተጨማሪ ወጪ አለው። ይህን ሁሉ ወጪ ደግሞ እኔ አልችለውም” ሲሉ አቅም እንደሚገድባቸው ይናገራሉ።

የጠፉ በሽታዎች ዳግም የማገርሸት ስጋት

በአማራ ክልል ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ የሚገኙ በርካታ አካባቢዎችን የሚያካልለው ዋነኛው መንገድ በመዘጋቱ፣ የሚያጋጥሙ የጤና እክሎችን በከፍተኛ የጤና ተቋማት አማካይነት ለመከላከል እና ለማከም ያሉ አማራጮችን እንዳጠበበው ነዋሪዎች እና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የመንገዱን መዘጋት “ኃላፊነት የጎደለው” ነው የሚሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የጤና ባለሙያ “በሕይወት እና በሞት መካከል ያለ ሰው ካለ ዐይናችን እያየ ነው የሚሞተው” በማለት ከነፍሰ ጡር እናቶች እና ቁስለኞች ውጪ ላሉ በሽታዎች ህክምና ማግኘት “የቅንጦት ያህል ነው” ይላሉ።

“የክትባት፣ የፀረ ኤችአይቪ እና የቲቢ መድኃኒቶች እያገኘን አይደለም። ስለዚህ እኛ ጋር [መድኃኒት] ከሌለ ሪፈር ነው የምንላቸው። በተለያዩ መንገዶች ወደ ሆስፒታል ለመድረስ ደግሞ አስከ አምስት ሺህ ብር ያስወጣል” በማለት የሕብረተሰቡን የጤና ውጣ ውረድ ያስረዳሉ።

የመድኃኒት አቅርቦት ችግሩ በሽታዎች እንዲስፋፉ ያደርጋል የሚል ስጋት ያላቸው የጤና ባለሙያው፤ አሁን ካሉ አሳሳቢ የጤና ችግሮች በተጨማሪ የጠፉ ወይም ከመጥፋት ደረጃ ላይ የደረሱ በሽታዎች መልሰው ሊከሰቱ ይችላሉ በሚል ስጋት መጪው ጊዜ የበለጠ ያሳስበዋቸዋል።

በተለይም ከዚህ ቀደም በተደረጉ ዘመቻዎች ጠፉ የተባሉ በሽታዎች ሊያገረሹ ይችላሉ ሲሉም የህጻናትን ክትባት አቅርቦት መቋረጥን ያነሳሉ።

“የክትባት መድኃኒቶች መምጣት ያለበት ጊዜ አልፏል። በዚህ ሁኔታ የማይመጣ ከሆነ እና ለወራት የሚቀጥል ከሆነ ጠፉ የተባሉት እንደ ኩፍኝ፣ የሳምባ ምች፣ ፖሊዮ ማገርሸታቸው የማይቀር ነው።”

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በክልሉ ያለው ጦርነት የጤና ሥርዓቱን ፈትኗል የሚለው የአማራ ክልል ጤና ቢሮ፤ የህጻናት ክትባት ከ60 በመቶ እንደማይሻገር እና ክትባትን ጨምሮ የኤችአይቪ፣ የቲቢ፣ የወባ እና የሌሎችም በሽታዎች መድኃኒቶች አቅርቦት እየተቋረጡ መሆናቸውን ከጥቂት ወራት በፊት ለክልሉ የመገናኛ ብዙኃን ተናግሮ ነበር።