“ሕዝብን በድሮን መትተን አናውቅም” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የፎቶው ባለመብት, etv
የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተካሄዱ ባሉት ግጭቶች ውስጥ ሠራዊታቸው ነዋሪዎች ላይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ፈጽሞ እንደማያውቅ ተናገሩ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህንን ያሉት ከብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ከሁለት ሰዓት በላይ በቆየ ቃለ ምልልስ ላይ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እየተካሄዱ ስላሉት ወታደራዊ ግጭቶች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት በግጭቶች አካባቢ በሚወስዳቸው እርምጃዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን መንግሥታዊውን የሰብአዊ መብት ድርጅት ጨምሮ በርካታ ዘገባዎች የወጡ ቢሆንም፣ ኤታማዦር ሹሙ የሚቀርቡትን ክሶች በቃለ ምልልሳቸው ላይ አስተባብለዋል።
በድሮን በሰላማዊ ሰዎች ጥቃት ተፈጽሟል በሚል የሚቀርበውን ክስ ያነሱት የሠራዊቱ አዛዥ “ሕዝብን በድሮን መትተን አናውቅም። እኛ በጥናት ላይ የተመሠረተ ታጥቆ እና ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ፀረ ሰላም ኃይልን ለይተን እንጂ ሕዝብን በድሮን አንመታም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም “ፀረ ሰላም” ያሏቸው ታጣቂዎች ከሕዝቡ ጋር ከተቀላቀሉ ለሕዝቡ ስንል “እያየን ሳንመታ እንሄዳለን” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “እንደዚያማ ባይሆን ኑሮ እስካሁን አይቆዩም ነበር። ዝም ብለን ጨፍልቀን፣ ደባልቀን የምንመታ ቢሆን ኖሮ እስካሁን አይቆዩም ነበር” ብለዋል።
የጦር አዛዡ “የእኛ ድሮን ወይ ሸኔ ላይ ነው ወይ ጃዊሳ ላይ ነው የሚያርፈው እንጂ ሕዝብ ላይ አያርፍም፤ የኦሮሚያም ሆነ የአማራ ሕዝብም ይህንን ያውቃል” ሲሉ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በሚካሄዱ ወታደራዊ ዘመቻዎች የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ዒላማ ታጣቂዎች ብቻ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህንን ቢሉም ነዋሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ግን በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ጥቅምት ወር ባወጣው መግለጫ፤ በአማራ ክልል “የአየር/ድሮን መሳሪያን ጨምሮ በከባድ መሳሪያዎች ጥቃት በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል” ብሏል።
መንግሥታዊው የመብት ተሟጋች ተቋም በዚሁ መግለጫው፤ በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ህጻንን ጨምሮ “በርካታ ሲቪል ሰዎች” መገደላቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በተጨማሪም በደብረ ማርቆስ ከተማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት “ቢያንስ ስምንት ሰዎች እንደተገደሉ” ኢሰመኮ በመግለጫው ጠቁሞ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በተመሳሳይ ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የሰው አልባ አውሮፕላኖች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጿል።
ቢቢሲም ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃ እና ወደራ ወረዳ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያነስ 30 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ጠቅሶ ዘግቧል።
በተመሳሳይ ባለፈው ታኅሣሥ በደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ከተማም እንዲሁ በአምቡላንስ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያነስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የጤና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ “መካለከያ የአማራ ሕዝብን እየጨፈጨፈ ነው፣ ኦሮሞ ሕዝብን እየጨፈጨፈ ነው” በሚል የሚቀርብ ክስ መኖሩን ጠቅሰው፤ “መጨፍጨፍ አለመጨፍጨፋችንን ሂዱ እና ከሕዝቡ አዳምጡ፤ እኛ ሕዝብ አንጨፈጭፍም፣ የሚጨፈጭፈው [ሕዝብ] እየተጨፈጨፈ ነው ባዩ ራሱ ነው” ሲሉ ከሰዋል።
ከአንድ ወር ገደማ በፊት ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች፤ “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት ቢያንስ 45 ሰዎችን “ከሕግ ውጪ መግደላቸውን” አስታውቆ ነበር።
ቢቢሲ በወቅቱ የመርዓዊ ከተማ ነዋሪዎችን በማናገር ባገኘው መረጃ ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቤት ለቤት በተካሄደ አሰሳ በመከላከያ ሠራዊት “መረሸናቸውን” የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦችን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።
የአሜሪካ አምባሳደርን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በመርዓዊ ከተማ በነዋሪዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ እንዳሳሰባቸው ገልጸው፣ ምርመራ ተደርጎ አጥፊዎች እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርበው ነበር።
“የሶማሊያ መንግሥት ሞቃዲሾ እንዲቀመጥ ያደረገው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው”
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በቃለ ምልልሳቸው ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ በጎረቤት አገር ሶማሊያ ያለውን የሰላም ማስከበር ጉዳይ ነው።
በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ላይ መሆኑን ፊልድ ማርሻሉ አስታውሰው፤ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሶማሊያ ግዛት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በሶማሊያ ሰላም ውስጥ ሠራዊታቸው ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተናገሩት የጦር ኣዛዡ፤ “የሶማሊያ መንግሥት ሞቃዲሾ እንዲቀመጥ ያደረገው የኢትዮጵያ መካለከያ ሠራዊት ነው” በማለት “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነገ ቢወጣ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ሞቃዲሾ የሚቀመጥ አይመስለኝም” ብለዋል።
“ከአልሸባብ ጋር በመፋለም እኛ ጥሩ [ሥራ] ሠርተናል” ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፤ “የሶማሊያ ክልሎች ከፍተኛ ጥበቃ ያደርግልናል ብለው የሚያስቡት የኢትዮጵያ መካለከያ ሠራዊትን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ፊልድ ማርሻሉ የሶማሊያ ሕዝብ ለኢትዮጵያ መካለከያ ሠራዊት የሚሰጠውን ክብር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሶማሊያ አመራሮች እየሰጡ አለመሆኑን “[የሶማሊያ ባለሥልጣናት] ሠራዊቱ ምንም እንዳላደረገላቸው ነው ሲያወሩ ነበረው፤ ይህም ውለታ ቢስነት ነው” ሲሉ በኃይለ ቃላት ተነግረዋል።
እንደ ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹሙ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በተመሳሳይ መንግሥታቸው ለሶማሊያ ሰላም እና አንድነት በመሥራት የሚወዳደረው አለመኖሩን “ለሶማሊያ አንድነት እንደዚህ መንግሥት የሠራ የለም” በማለት በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጻቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ከሶማሊላንድ ጋር ባለፈው ታኅሣሥ ወር የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረመች በኋላ ሶማሊያ ስምምነቱ ሉዓላዊነቷን የሚጋፋ መሆኑን በመግለጽ ተቃውማ በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ ተፈጥሮ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በተፈራረሙት ስምምነት ላይ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ አገልግሎት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ጠረፍ በኪራይ እንደምትሰጥ እና በምላሹም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና ትሰጣለች ተብሎ ነበር።
ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና በሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ቢሂ መካከል ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ቢባልም፣ የትግበራ ሁኔታውን በተመለከተ አስካሁን ከሁለቱም ወገኖች የተባለ ነገር የለም።












