አሜሪካ በመርዓዊ ከተማ ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀች

አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ

የፎቶው ባለመብት, @AsstSecStateAF

የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ

በአማራ ክልል መርዓዊ ከተማ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ በማድረግ ግድያ የፈጸሙ ላይ ምርመራ ተደርጎ ለፍርድ እንዲቀርቡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጠየቁ።

አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በኤምባሲው የኤክስ ገጽ ላይ ባወጡት መልዕክት በመርዓዊ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በሚመለከት የወጡ ሪፖርቶች የአሜሪካ መንግሥትን እንደሚያሳስበው ገልጸዋል።

ከ11 ቀናት በፊት ሰኞ፣ ጥር 20/2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን፣ በመንግሥት ኃይሎች መርዓዊ ከተማ በተፈጸመ ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ቤተሰቦች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ማክሰኞ ጥር 28/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በከተማዋ በታጣቂ ቡድኖች እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል የተከሰተን ግጭት ተከትሎ በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸው ከ80 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ማሲንጋ፣ የክስተቱን አሳሳቢነት ከመግለጻቸው ባሻገር “የግድያውን ፈጻሚዎች ለሕግ ለማቅረብ” ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪዎች ምንም ገደብ ሳይደረግባቸው ወደ ሥፍራው እንዲንቀሳቀሱ እንዲፈቀድላቸው እንዲሁም በግድያው ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በአገሪቱ ባሉት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ በሌሎችም ቦታዎች ላይ “በመንግሥት እና ከመንግሥት ውጪ በሆኑ ኃይሎች በተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች እና ጥቃቶችን መፈጸማቸውን የሚያመልክቱ በርካታ የሚረብሹ” ሪፖርቶች እየወጡ መሆናቸውንም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም መደረጉ አሳስቦኛል በማለት ባለፈው ሳምንት የገለጹት አምባሳደር ማሲንጋ፣ ዛሬ የካቲት 1/2016 ዓ.ም. በኤምባሲው ማኅበራዊ ገጽ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “ኃይል ሳይሆን ውይይት ብቸኛው አማራጭ ነው” ብለዋል።

በመርዓዊ ከተማ በበርካታ ሰዎች ላይ ግድያው የተፈፀመው በግጭቱ በነበረው ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እና በቤት ለቤት አሰሳ መሆኑን የገለጸው ኢሰመጉ፣ ወንዶችን ቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ ወደ መንገድ በማውጣት የጅምላ ግድያ መፈፀሙን ከዐይን እማኞች ሰምቻለሁ ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጉባኤው እንዳለው ከሟቾቹ መካከል ሁለት ሴቶች እና አንድ የ17 ዓመት ታዳጊ ይገኙበታል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያው የተፈጸመው በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተደረገ ውጊያን ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።

ከክልሉ መዲና ባሕር ዳር በ35 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው መርዓዊ ከተማ የአብዛኞቹ ነዋሪዎች ግድያ የተፈጸመው በቤታቸው እና በመንገድ ላይ በተገኙ ሰላማዊ ሰዎች ላይ መሆኑን ቤተሰቦች እና የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

ጥቃቱ ረፋድ 5፡00 ሰዓት አካባቢ የፋኖ ኃይሎች ከተማዋን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ “መከላከያ ሠራዊት ቤት ለቤት በመዞር እና መንገድ ላይ ያገኛቸውን ሰዎች መረሸኑን” የተናገሩት የዐይን እማኞቹ፣ ጥቃቱ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት የዘለቀ ነበር ብለዋል።

ቢቢሲ በወቅቱ ያናገራቸው የህክምና ባለሙያን ጨምሮ ነዋሪዎች የተመለከቷቸውን አስከሬኖች መሠረት በማድረግ “ከስድስት ዓመት ህጻን እስከ 75 ዓመት አዛውንት” ድረስ ያሉባቸው ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ብዙዎቹ የሟቾች ቁጥር ከ100 በላይ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ነበር።

በመርዓዊ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ ተከትሎ ስጋት የገባቸው አንዳንድ ነዋሪዎች ወደ ባሕር ዳር እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሸሻቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።

የክልሉ መስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ ሁለት ሳምንት ሊሞላው ስለተቃረበው የመራዊ ከተማ ክስተት እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።

ካለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም. ባወጣው ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖች ውስጥ በተለያየ ደረጃ እና ጊዜ የትጥቅ ግጭት መካሄዱን ገልጾ፣ በዚህም ሳቢያ በርካታ ሲቪሎች እንደተገደሉ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቶ ነበር።