የአማራ ክልል ቀውስ፡ መደምደሚያው የኃይል የበላይነት ወይስ ድርድር?

አንድ ዓመት ያለፈው በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት በክልሉ አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና በሕዝቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ ከባድ ጫና ማሳደሩ በይፋ እየታየ ነው።
በዚህም ሳቢያ ባለፈው አንድ ዓመት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ ያለው የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ነዋሪዎች እና የክልሉ አስተዳደር ኃላፊዎች እማኝነት አመላካች ነው።
ከአስራ አምስት ወራት በፊት የተቀሰቀሰው ግጭት በተለያዩ ጊዜያት እየተባባሰ እና ጋብ እያለ ወደ ሁለተኛ ዓመቱ ተሸጋግሯል። በክረምቱ ወራት ተቀዛቅዞ የነበረው ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት መልሶ ያገረሸ ሲሆን፣ በተለይ በተለያዩ የጎጃም አካባቢዎች ከባድ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
መንግሥት የፋኖ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር ሰፊ ዘመቻ መጀመሩን የገለጸ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ ደግሞ ባለፈው ዓመት ከነበሩበት አቋም ጋር ሲነጻጸር “በእጅጉ መጠናከራቸውን እና የመንግሥት ኃይል ለመገዳደር የሚያስችል አቅም” መፍጠራቸውን ይናገራሉ።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምሁር በበኩላቸው የፋኖ እንቅስቃሴ በቀጥታ የጦር ሜዳ ውጊያ “መንግሥትን ባይጥል እንኳ፣ ለተጓዳኝ ምክንያቶች በማጋለጥ መንግሥትን ወደ ድርድር እንዲመጣ ወይም ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ ያስገድደዋል” ይላሉ።
ነገር ግን እስካሁን ባለው ሁኔታ ወደ አንድ ወጥ አደረጃጀት ለመምጣት የተቸገሩት የፋኖ ቡድኖች ስለድርድር ያላቸው አቋም፣ የሚያቀርቡት ጥያቄ እና ሊወክላቸው የሚችል ተደራዳሪን በተመለከተ በእርግጠኝነት መናገር የሚያስችል ነገር የለም።
በተጨማሪም አንዳንዶቹ ቡድኖች በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሚሰጧቸው መግለጫዎች መረዳት እንደሚቻለው ለደርድር እምብዛም ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም።
በክልሉ ያለውን ሁኔታ በቅርበት የሚያውቁ ቢቢሲ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የብልጽግና ፓርቲ አባል የነበሩ ምሁር “ፋኖ ያለው ዕድል አሁን የፈጠረውን አቅም ይዞ ለድርድር መቀመጥ” መሆኑን ይናገራሉ።
ነገር ግን ባለፈው አንድ ዓመት በክልሉ ውስጥ መጠነ ሰፊ ጉዳት ባስከተለው ጦርነት የማሸነፍ ግብን ብቻ ይዞ መቀጠልን የሚመርጥ ከሆነ “ፋኖ ሕልውናው አደጋ ላይ ይወድቃል፤ በአንጻሩ መንግሥት ኃይሉ ይጠነክራል” የሚል ሃሳብም ይሰነዝራሉ።
የአንድ ዓመት ጉዞ. . .
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተጠናከረው ፋኖ ከአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ጎን ሆኖ የተዋጋ ሲሆን፣ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ግን ከክልሉ አስተዳር እና ከፌደራል መንግሥት ጋር ቀስ በቀስ ወደ ቅራኔ ገብቷል።
ያልተቋጨው የአማራ እና የትግራይ ክልል የግዛት ይገባኛል ጉዳይ በዘላቂነት መፍትሄ አለማግኘቱ፣ የአማራ ሕዝብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚሰነዘርበት ጥቃት፣ እንዲሁም የክልሉ ልዩ ኃይል እና ፋኖዎች ትጥቅ እንዲፈቱ መወሰኑ ነበር ግጭቱን የፈጠረው።
ፋኖን የሚደግፉት እና በአማራ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ዶ/ር ምስጋናው አንዷለም “የአማራ ሕዝብ ከሚደርስበት ጥቃት የሚከላከለው በሚፈልግበት ጊዜ” ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ልዩ ኃይሉ ሲፈርስ “ጠባቂውን የተነጠቀው ሕዝብ ፋኖ ሆኖ ወጣ” በማለት የጦርነቱን ዋነኛ ምክንያት ይጠቅሳሉ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባሉ አቶ ዓለሙም (ስማቸው የተቀየረ) በክልሉ የሚካሄደው ግጭት “በአማራ ሕዝብ ላይ የመጣበት እንጂ፣ ሕዝቡ ተደራጅቶ እና አስቦበት የተጀመረ አይደለም” በማለት መንግሥትን ይወቅሳሉ።
የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል ሰብሳቢ እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው አስረስ ማረ ደግሞ የጦርነት አዝማሚያ እና ትንኮሳ ከትግራዩ ጦርነት ጎን ለጎንም ይደረግ እንደነበር ይገልጻል።
በወቅቱ አንዳንዶቹ የፋኖ ቡድኖች በሰሜኑ ጦርነት እየተሳተፉ የነበረ ቢሆንም፣ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በጎጃም አንዳንድ አካባቢዎች “ይህንን ኃይል ትጥቅ ለማስፈታት ሲሞከር ነበር” በማለት ያስታውሳል።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያሳየው ዳተኝነት፣ ከእነዚህ ገፊ ምክንያቶች ጋር ተዳምረው አሁን ክልሉ ለገባበት ቀውስ እንደዳረጉትም ይገልጻል።
አንድ ዓመት ያስቆጠረው የፋኖ እና የመንግሥት ኃይሎች ግጭት አንዳንድ ጊዜ በትላልቅ ከተሞች አቅራቢያ ሌላ ጊዜ ደግሞ በገጠር አካባቢዎች እየተካሄደ ነው። በዚህ ሂደት በሰው ኃይል እና በትጥቅ እየተጠናከሩ እንደሆነ የሚናገሩት የፋኖ ታጣቂዎች፣ የመንግሥትን ኃይል የሚገዳደር አቋም ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ።
የብልጽግና አባል የነበሩት ምሁር ግን የፋኖ ኃይሎች የአንድ ዓመት ዕድገት እና ተጽእኖ ፈጣን ቢሆንም መንግሥትን መቀየር የሚያስችል ቁመና ላይ አይደሉም የሚል እምነት አላቸው።
“ፋኖ በተለያዩ መስኮች መጠናከር እና ተገዳዳሪ የመሆን አቅም ፈጥሯል። በግጭቱ መጀመሪያ አካባቢ በየመንደሩ የነበረው መሰባሰብ አሁን ታጣቂ ቡድን ሊኖረው ወደሚገባ አወቃቀር ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ነው” ይላሉ።
ነገር ግን ይህ ሂደት በድክመቶች የተሞላ መሆኑን የሚጠቅሱት ምሁሩ፤ እንቅስቃሴው ወጥ አደረጃጀት አለመኖር፣ የተለያየ አደረጃጀትን መከተል፣ የዲሲፕሊን፣ የማዕከላዊነት እና የመሪ ችግር በፋኖ ኃይሎች ዘንድ በስፋት የሚስተዋል መሆኑን ያነሳሉ።
የአብን አባሉ አቶ ዓለሙ ደግሞ የፋኖ ትግል በአንድ ዓመት ውስጥ ትልቅ አቅም ቢፈጥርም በሕዝቡ ላይ ግን ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማስከተሉን ይናገራሉ።
ጨምረውም በአንድ ዓመት የትጥቅ ግጭት ውስጥ የፋኖ ኃይሎች “በክልሉ መንግሥት ላይ ብልጫ በመውሰድ” የአካባቢ አስተዳደሮች ፈርሰዋል፣ ሕግ የማስከበር እና ግብር የመሰብሰብ ሥልጣኑን ተቀምቷል በማለት የመንግሥት መዋቅር መሽመድመዱን ይገልጻሉ።
ባለፈው አንድ ዓመት የመንግሥትን የታችኛው መዋቅር መፍረሱን የሚናገረው አስረስ ማረ፣ “የመንግሥት ትልቁ መዋቅር ያለው ቀበሌ ላይ ነው፤ አሁን ግን ያ የለም።...ብዙዎቹ ዋና ዋና መንገዶች በፋኖ ቁጥጥር ሥር ናቸው” ይላል።

የውስጥ ክፍፍል እና አንድነት . . .
የፋኖ ታጣቂዎች በአብዛኛው የክልሉን ገጠራማ አካባቢዎች እንደተቆጣጠሩ ቢናገሩም ሁሉንም ቡድኖች የሚያሰባስብ እና የሚመራ ወጥ ማዕከልም ሆነ አመራር እስካሁን የላቸውም።
ከወራት በፊት አንድ ወጥ አመራር ለመፍጠር የፋኖ ኃይሎች የተሳተፉበት ምክክር ቢደረግም፣ በሁሉም የፋኖ ኃይሎች ተቀባይነት ያለው ውጤት ላይ ሳይደርስ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ከፊሎቹ ተመሠረተ በተባለው ድርጅት ውስጥ ሲገቡ፣ ገሚሶቹ ደግሞ ራሳቸውን አግልለዋል።
ይህም በፋኖ መካከል የአቋም እና የፍላጎት ልዩነት እንዳለ ያሳየ መሆኑ ሲነገር ነበር። የድርጅት ምሥረታውን ከተቃወሙት የፋኖ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ የሆነው አስረስ ማረ “የትግል ጥያቄው አንድ እስከሆነ ድረስ ፋኖ ተሰነጠቀ የሚያስብል አይደለም” በማለት ሂደቱን ያስረዳል።
ነገር ግን ሂደቱ አለመቋረጡን “የአንድነት ምሥረታው አሁንም ቢሆን በንግግር ደረጃ በሂደት ላይ ነው። በሆይ ሆይታ እና በዘመቻ ከሚሆን ተፈጥሯዊ ሂደቱን ጠብቆ ይምጣ በሚል የጋራ ሥራዎችን እያከናወንን ቀጥለናል” ብሏል።
በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ በሚንቀሳቀሱት የፋኖ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ምንጩ ሂደቱን “ለመጨረስ በመጣደፋቸው ነው” የሚሉት የቀድሞው የብልጽግና አባል፣ “የሃሳብ ልዩነት መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከውጤቱ በኋላ ደጋፊዎቻቸው ነገሮችን በማጋጋል ወደ አደገኛ ሁኔታ” እንደወሰዱት ይናገራሉ።
የፋኖ ቡድኖችን ወደ አንድ የማምጣቱ ሙከራ ባይሳካም ሂደቱ ፈጣን እና በአንጻራዊነት ስኬታማ እንደነበረ የሚናገሩት ዶ/ር ምስጋናው፤ ነገር ግን በደጋፊዎቻቸው መካከል የተፈጠረው ከፍተኛ የሆነ መወነጃጀል “መሆን ያልነበረበት እና የወደፊቱን አንድነት ግምት ውስጥ ያላስገባ ነበረ” ሲሉ ይተቻሉ።
ነገር ግን በፋኖ ቡድኖች አመራሮች መካከል ያለው የፍላጎት መለያየት በአንድ ለመቆም እንቅፋት እንደሆነ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በተጨማሪም አካባቢያዊ አመለካከት ያላቸው እና እንቅስቃሴውን በበላይነት ለመምራት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ሚናም ሂደቱን እንዳደፈረሰው የሚናገሩ አሉ።
የብልጽግና አባል የነበሩት ምሁር የአማራ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ “ሥር የሰደደውን የጎጥ አመለካከት የፋኖ እንቅስቃሴ እንዲከስም አስተዋጽኦ ቢያደርግም እነሱም አንድ ለመሆን እየተቸገሩ ነው” ይላሉ።
“በሁለት ጎራ የተከፈሉት አደረጃጀቶች አጠቃላይ ክልላዊ ይዘት አላቸው። የመንደርተኝነት እና የሥልጣን ጉዳይ አለ። ከውጭ ያለው ሿሚም በራሱ አይስማማም። ከዚህ ራስን የማስቀደም አባዜ በቅርቡ ይላቀቃሉ የሚል እምነት የለኝም” ብለዋል።
ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ጥምረት . . .
የፋኖ ኃይሎች በተደጋጋሚ እንደሚገልጹት ዋነኛ ዓላማቸው በብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን የመንግሥት ሥርዓት መጣል ቢሆንም፣ በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታን ከግንዛቤ ያስገባ ብቃት እና አደረጃጀት ስለመኖሩ ብዙዎች ይጠይቃሉ። ለዚህም የተለያየ ፖለቲካዊ ፍላጎት እና ዓላማ ያላቸው ኃይሎች ባሉበት አገር እስካሁን ፋኖ አጋር የሚለው ኃይል እንደሌለው በምሳሌነት ያነሳሉ።
“የአማራ ሕዝብ አገዛዙን ይጥለዋል” የሚሉት ዶ/ር ምስጋናው፣ ያ ሲሆን ግን የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል። በዚያን ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ሥርዓት ለመመሥረት የተለያዩ ኃይሎች ወደ ጠረጴዛው ይመጣሉ ብለው ያምናሉ።
አስረስ ማረ በበኩሉ የፋኖ እንቅስቃሴ ብቻውን “ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄዎች መፍትሄ ያመጣል ብለን አናምንም” በማለት፤ ከሌሎች ተመሳሳይ አመለካከት ካላቸው ኃይሎች ጋር በመሆን “ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ለመገንባት” እንደሚሠሩ ይገልጻል።
ለዚህም በጋራ ለመሥራት ጥናቶች እያደረጉ መሆናቸውን እና “ከአንዳንዶቹ ጋ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች አሉ፤ አንዳንዶቹ ጋር ደግሞ ፈጽሞ የማያስማሙ ነገሮች አሉ” ያለው አስረስ፣ ነገር ግን ያንን ለማምጣት “እኛ ተፈላጊ መሆናችንን የሚያሳይ ቁመና ላይ መድረስ አለብን” ብሏል።
የአብን አባሉ አቶ ዓለሙ ፋኖዎች ከሌሎች የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር አጋርነት ለመፍጠር “የውስጥ ጣጣቸውን በፍጥነት መጨረስ አለባቸው” በተጨማሪም ጡንቻቸውን እያፈረጠሙ ከሄዱ “ተፈላጊነታቸው ይጨምራል፤ ሚዛናዊ ድርድር ለማድረግም ይመቻል። የተሻለ ኃይል የፈጠረው አካል ሌሎችን እያሰባሰበ ይሄዳል” በማለት ያክላሉ።
የአማራ ክልልን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት ምሁር እንደሚሉት ደግሞ በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መካከል ፋኖዎች አጋር ሊያገኙ ይችላሉ፤ ነገር ግን እነዚያ አጋሮች የፋኖን ዓላማ ከማሳካት አኳያ ምን ያክል ያግዘዋል የሚለው ዋነኛ ጥያቄ እንደሆነ ያነሳሉ።
አክለውም ፋኖ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ልምድ ካላቸው ኃይሎች ጋር ጥምረት መፍጠር ከቻለ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጥምረት ደግሞ የእንቅስቃሴውን የተጽዕኖ አድማስ ከክልሉ አልፎ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለማስፋት ያስችለዋል።
ፋኖ በአንድ አመራር ሥር መግባት ከቻለ እና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አቅሙን በማቀናጀት የሚያግዝ ጥምረት መፍጠር ከቻለ የእንቅስቃሴው አቅጣጫ በመሠረታዊነት ሊቀየር ይችላል። ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፋኖን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚያግዘው ኃይል ባለመኖሩ የእንቅስቃሴው ዐውድ በቅርቡ ይቀየራል የሚል እምነት የላቸውም።
የሰላም/ድርድር አማራጭ . . .
በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም እስካሁን ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ፍንጭ አልታየም። በዚህም ምክንያት በክልሉ ሕዝብ እና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ምስቅልቅል ፈጥሯል።
ባለፈው ዓመት በክልሉ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ከነበረባቸው 6 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በግጭቱ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። በዚህ ዓመትም ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢታቀድም የተመዘገቡት ከ2 ሚሊዮን በታች መሆናቸውን ክልሉ ገልጿል።
ለአገሪቱ የግብርና ምርት አቅራቢ ከሆኑ አካባቢዎች ከፍተኛ ድርሻ ያለው አማራ ክልል፣ በጦርነቱ ምክንያት ማምረት እና ምርትን ወደ ገበያ ማቅረብ አልቻለም። በጤና ዘርፍም እንዲሁ ተቋማት አስፈላጊውን አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው ለሕዝቡ የሚጠበቀውን አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ይናጋራሉ።
ጦርነቱ በተጨማሪ የበርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወትም ቀጥፏል። መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ ጉዳት ደርሶባቸዋል እንዲሁም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
ክልሉን ቀውስ ውስጥ ያስገባውን ግጭት ለማስቆም የአማራ ክልል እና የፌደራሉ መንግሥት ለንግግር በራቸው ክፍት መሆኑን እንዲሁም ሁለቱን ወገኖች የሚያሸማግል ምክር ቤት ቢቋቋምም አስካሁን በተጨባጭ የተጀመረ ወይም የተካሄደ ጥረት ስለመኖሩ በይፋ የተባለ ነገር የለም።
“የምንታገለው ለፖለቲካ ጥያቄ ነው። ግባችንም ሰላም ማምጣት ነው” የሚለው የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል ሰብሳቢ አስረስ ማረ፣ “ሰላምን በፖለቲካዊ መንገድ ማምጣት ስላልተቻለ በኃይል ለማምጣት የምናደርገው ትግል ነው። የምናልመው ግብ ተሳክቶ ሕዝቡ ማኅበራዊ እረፍት ቢያገኝ ደስታችን ወደር የለውም” በማለት ቡድኑ ሐቀኛ ድርድርን “በመርኅ ደረጃ” እንደሚቀበል ይገልጻል።
ነገር ግን ብልጽግና [መንግሥት] ሐቀኛ ድርድር ስለመፈለጉ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግሯል። በሁሉም “የፖለቲካ ተዋናዮች ዘንድ ተዓማኒ የሆነ እና የአማራ ጥያቄ የሚመለስበት ዕድል ካለ ወደ ድርድር የማንመጣበት ሁኔታ የለም” የሚለው አስረስ፣ ነገር ግን እስካሁን ይፋዊ የድርድር ጥያቄ እንዳልቀረበላቸው ገልጿል።
ዶ/ር ምስጋናው በመንግሥት እና በፋኖ መካከል ድርድር ሊኖር እንደሚችል ያምናሉ። ነገር ግን ፋኖዎቹ ጦርነቱን ቀጥለን ሥር ነቀል ለውጥ እናምጣ ወይስ ሌላ አማራጭ እንከተል የሚል አማራጭ ሊያስቀምጡ ይችላሉ።
እንዲያም ሆኖ ግን የድርድር ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ትንሽ የፈጠነ ነው የሚሉት ዶ/ር ምስጋናው፣ “አሁን ባለው ሁኔታ የፋኖዎች ዓላማ ሥርዓቱን የመቀየር ነው። የተወሰኑት የፋኖ አደረጃጀቶች እንደራደር ቢሉ እንኳን በተናጠል የሚደረግ ድርድር ስለሚሆን የትም አያደርስም” ይላሉ።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈቀዱት ምሁር ግን “ፋኖ አሁኑኑ መደራደር አለበት” በማለት ከድርድር ሃሳቡ ከመሸሽ ይልቅ ስጋታቸውን ለዓለም አቀፍ ተቋማት ማስገንዝብ እና የሦስተኛ ወገን መተማመኛ መጠየቅ ይሻላቸዋል፤ “ምክንያቶች እየተጠቀሱ ሕዝቡ በግጭት ውስጥ መኖር የለበትም” ባይ ናቸው።
“መንግሥት የሚሠራው ፕሮፖጋንዳ እና መሬት ላይ ያለው እውነታ ይለያያል” የሚሉት ምሁሩ፣ በመንግሥት በኩል መድከም እና መሰላቸት እየታየ በመሆኑ መንግሥት ድርድሩን እንደሚፈልገው ያምናሉ።
በአገሪቱ ዙሪያ [በቀጣናው] ያለው ውጥረት እና የጦርነት ደመና እንዲሁም የኑሮ ውድነቱ መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል። በእነዚህ እና በሌሎችም ምክንያቶች መንግሥት ድርድሩን ቢፈልገውም “እየተሽኮረመመ ነው። ካፈርኩ አይመልሰኝ ዓይነት ድብብቆሽ ውስጥ ገብቷል” በማለት ምሁሩ ይተቻሉ።
በዚህም ምክንያት ድርድሩን በክልሉ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል ወይም ሌሎች ወገኖች ገፍተው እንዲያመጡለት ከመሻት ውጪ በራሱ ተነሳሽነት ያመጣዋል የሚል ዕምነት የላቸውም።
መዳረሻው ምን ሊሆን ይችላል . . .
ግጭቱ በክልሉ ውስጥ ከፈጠረው አጠቃላይ ቀውስ አንጻር የሰላም መፍትሄ ቢገኝ ብዙዎች የሚመኙት ነው። እስካሁን ግን ያንን የሰላም አማራጭ የሚያሳዩ ሁኔታዎች አልተፈጠሩም። እንዲያውም ግጭቱ ከዚህም በላይ ሊባባስ እንደሚችል ያሰጋል።
አቶ ዓለሙ እንደሚሉት የፋኖ እንቅስቃሴ ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት ዘንድ መታወቁን ጠቅሰው “በውጭ ተጽእኖ ወይም በሐቀኛ ድርድር የፋኖ ትግል በመንግሥት ላይ ጫና ሊያሳርፍ እንደሚችል” ያምናሉ።
ስለዚህም አሁን በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጉዳይ በተመለከተ የሚያሳስባቸው አካላት መብዛታቸውን በማንሳት፣ መንግሥትም “በአምባገነንነት ሁሉንም ጨፍልቆ የሚገዛበት ጉልበቱ መንምኗል” ይላሉ።
ዶ/ር ምስጋናው በበኩላቸው የፋኖ እንቅስቃሴ የሚፈልገውን ውጤት እያገኘ መሆኑን በመጥቀስ፣ ነገር ግን የተራዘመ ግጭት መካሄዱ ሕዝቡን ዋጋ እንደሚያስከፍል ያምናሉ። ቢሆንም ግን “ትግሉ ዓላማውን ሳያሳካ የሚቀለበስበት ዕድል ባይኖረውም የሚራዘም ከሆነ በሕዝቡ ዘንድ መሰላቸትን ሊያመጣ ይችላል” ይላሉ።
የቀድሞው የብልጽግና አባል የሆኑት ምሁር ደግሞ ከዚህ የተለየ ዕይታ አላቸው። ፋኖዎች ወጥ አመራር አዘጋጅተው በአንድ ላይ በመቆም አሁን በደረሱበት ደረጃ ላይ ሆነው ከመንግሥት ጋር ከተደራደሩ “ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ መልካም ዕድል” እንደሚፈጠር ያምናሉ።
“ይህ ካልሆነ ግን መንግሥት ኃይሉ እየበረታ፣ በተቃራኒው ፋኖ ከሕዝብ እየተነጠለ ሰለሚሄድ በሁኔታዎች ተገዶ ሊደራደር ይችላል” የሚል ሃሳብ አላቸው።
ነገር ግን አሁን በክልሉ ያለው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ቡድኑ አቅሙ እየተዳከመ “በመበታተን የዘመነ መሳፍንት ዓይነት ክስተትን ሊያመጣ ይችላል። ወይም ደግሞ ታጣቂዎቹ ወደ ተራ ሽፍታነት ተቀይረው ሕይወታቸውን ለማቆየት የሚጥሩ ብትን ኃይል ይሆናሉ” በማለት ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
የጎጃም ፋኖው አስረስ ማረ በአንድ ዓመት ያገኙት የትጥቅ እንቅስቃሴ ልምድ የመነሻ ግባቸውን ለማሳካት የሚያስችል አቅም እንደፈጠረላቸው በመጥቀስ “በፖለቲካ ጥያቄ የተሸነፈ ኃይል በትጥቅ ትግል የሚያሸንፍበት አቅም የለውም” በማለት የተነሱለት “የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ” እንቅስቃሴያቸው እንደማይኮላሽ በእርግጠኝነት ይናገራል።
የብልጽግና አባል የነበሩት ምሁር ደግሞ “የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ብሎ ፋኖ የሚያነሳቸው የአማራ ብልጽግና ጥያቄዎችም ናቸው” በማለት የሃሳብ ልዩነት አለመኖሩን ይገልጻሉ።
“ልዩነቱ ጥያቄዎቹ እንዴት ይመለሱ በሚለው ላይ ነው። አንዳንዶቹ በመንግሥት በኩል ለመፈታት ጥረት እየተደረገባቸው ያሉ ናቸው። ፋኖ በመምጣቱ ወይም በመቅረቱ የሚቀር ጥያቄ የለም። ነገር ግን የፋኖ መኖር ዓለም አቀፍ ትኩረት ሊያስገኝ እና ተጨማሪ ግፊት ሊፈጥር ይችላል” በማለት ጥያቄዎቹ የጋራ መሆናቸውን አመልክተዋል።
አክለውም የአማራ ብልጽግና በኃይል ተወግዶ ፋኖ ወደ ሥልጣን ቢመጣ “ጥያቄዎቹ የሚመለሱበትን መንገድ የበለጠ ከማወሳሰቡ ባሻገር ጊዜውንም ያራዝመዋል” የሚሉት ምሁሩ፣ በድርድር ውጊያው ቢቆም ግን ጥያቄዎቹ የሚመለሱበትን ጊዜ ያሳጥረዋል ብለው ያምናሉ።
ስለዚህም ፋኖ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚያካሂደውን የትጥቅ እንቅስቃሴ ከመቀጠል ይልቅ ተደራድሮ ወደ ሰላማዊ ትግል ቢመለስ እና ከክልሉ አስተዳደር ጋር ቢተባበር ትልቅ ተገዳዳሪ ኃይል የመሆን ዕድል ይኖረዋል፤ እንዲሁም ለሕዝቡ ሰላምን ሊያመጣለች ይችላል ይላሉ።
አቶ ዓለሙ ግን በምሁሩ ሃሳብ አይስማሙም፤ “የአማራ ጥያቄዎች ብሎ መንግሥት የሚያቀርበው ለፕሮፖጋንዳ ነው። እንመልሳለን ቢባል እንኳ ዋናውን ጥያቄ ሳይሆን፣ የጥያቄውን ምልክቶች ነው” በማለት ጥያቄዎቹ በሙሉ ሳይሸራረፉ እስካልተመለሱ ድረስ ክልሉ እና አገሪቱ እየተባባሰ የሚሄድ ቀውስ ውስጥ መቆየታቸው አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።












