የአፍሪካ መሪዎች ባልተጋበዙበት በትራምፕ በዓለ ሲመት እንዲታደሙ የተመረጡት ናይጄሪያውያን ፓስተሮች

የፎቶው ባለመብት, Global Crusade with Kumuyi/Kevin Smart Media
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን የመጡት ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ሰኞ፣ ጥር 12/ 2017 ዓ.ም. በደመቀ ሁኔታ በተካሄደበት ወቅት ሁለት ታዋቂ ናይጄሪያውያን ፓስተሮች እንዲታደሙ ተጋብዘዋል።
የትኛውም የአፍሪካዊ መሪ ባልተጋበዘበት ሁኔታ ነው ሁለቱ ናይጄሪያውያን ፓስተሮች በበዓለ ሲመቱ ላይ እንዲታደሙ ተመርጠው የተጋበዙት።
የሁለቱ ናይጄሪውያን ፓስተሮች ዊልያም ኩሙዬ እና ናትናኤል ባሴ በዚህ የኃያሏ ሀገር መሪ በዓለ ሲመት ላይ መታደም በኢቫንጀሊካን አብያ ክርስቲያናት እና በአሜሪካ አስተዳደር መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ማሳያ ነው ተብሏል።
ትራምፕ በአህጉሪቷ በሚገኙ ክርስቲያኖች ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በሌሎች ስፍራዎች ተጽእኗቸው እንዲጎላ ለማድረግ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አንድ ተንታኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፓስተር ዊልያም በፈታኝ የአየር ሁኔታ ምክንያት በቤት ውስጥ እንዲካሄድ በተደረገው የትራምፕ የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ላይ ቢጋበዙም መገኘት አልቻሉም።
በምትኩ ለፕሬዚዳንቱ በተዘጋጀው የጸሎት አገልግሎት እንዲሁም ከተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በመገናኘት ነበር ጊዜያቸውን ያሳለፉት።
ፓስተሩ በዚህ የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ላይ መጋበዛቸው ያልተለመደ ነበር።
በአሜሪካ የፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት መሪዎችንም ቢሆን መጋበዝ ያልተለመደ አሠራር ነው።
ምንም እንኳን ትራምፕ የቻይና፣ የጣሊያን እና የአርጀንቲናን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎችን በመጋበዝ ባህሉን ቢጥሱም በግብዣቸው ዝርዝር ውስጥ የአፍሪካ መሪዎች አልተካተቱም።
በይፋ ከተያዘው የበዓለ ሲመቱ ሥነ ሥርዓት የጊዜ ሰሌዳ ውጪ እውቁ የናይጄሪያ ፓስተር ናትናኤል ባሴይ ሰኞ ጥዋት በነበረው የፕሬዚዳንቱ የሲመተ በዓል የቁርስ ጸሎት ፕሮግራም ላይ ጸሎት አድርጓል።
ከፖለቲካ ጋር ያልተገናኘ፣ ዕምነትን መሠረት ያደረገው ዝግጅት የተካሄደው ከፕሬዚዳንቱ ቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ቀደም ብሎ ነበር የተካሄደው። የበዓለ ሲመቱ አካል እንዳልሆነ በተነገረው በዚህ ዝግጅት ላይ ተመራጩ ፕሬዚዳንት አልተገኙም።

የፎቶው ባለመብት, Global Crusade with Kumuyi/Kevin Smart Media
ፓስተር ዊልያም ኩሙዬ ማን ናቸው?
የቀድሞ የሂሳብ ፕሮፌሰር የነበሩት ፓስተር ዊልያም 'ዲፐር ላይፍ ባይብል' (የጠለቀ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት) የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን መሥራች ናቸው።
በተጨማሪም የዓለም አቀፉ የወንጌል አገልግሎት ሰብሳቢ እንዲሁም ግሎባል ክሩሴድ ዊዝ ኩሙዬ የተሰኘ የስብከት አገልግሎትን ይመራሉ።
ግሎባል ክሩሴድ ቤተክርስቲያኗ በየሳምንቱ 120 ሺህ የሚሆኑ ታዳሚዎችን ታስተናግዳለች ብሏል።
በትራምፕ ጋባዥነት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያቀኑት ፓስተር ዊልያም ከወግ አጥባቂ የምክር ቤት አባላት ጋር እንደተገናኙ እና "በዓለም አቀፍ ደረጃ ወንጌል የሚስፋፋበትን" ሁኔታ በጋራ ለመሥራት እንዴት እንደሚተባበሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
እሁድ ዕለት አሜሪካውያኑ ፓስተሮች ጂም ጋርሎው እና ቶኒ ፐርኪንስ ባዘጋጁት የበዓለ ሲመቱ የምስጋና እና የጸሎት ዝግጅት ተሳትፈው የጸሎት ፕሮግራም መርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Nathaniel Bassey/Instagram
ናትናኤል ባሴይ ማን ነው?
ፓስተሩ ናትናኤል ባሴይ ናይጄሪያዊ ሙዚቀኛ፣ ፓስተር፣ የትራምፔት ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች፣ የሙዚቃ አዘጋጅ እና የመዝሙር ገጣሚ ነው። ፓስተሩ ትውልዱ በደቡባዊ ናይጄሪያ አክዋ ኢቦም በተሰኘችው ግዛት ነው።
ፓስተሩ በዓለም ዙሪያ ዝናው የናኘው በሙዚቃው እንዲሁም 'ሃሌሉያ ቻለንጅ' በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያደርገው የአምልኮ ፕሮግራሙ ነው።
በኢንስታግራም ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮችን ማፍራት ችሏል። ሙዚቀኛው በዓለም ዙሪያ ያሉ ክርስቲያኖችን ለማገናኘት በአውሮፓውያኑ 2017 የኢንተርኔት የምስጋና እና የጸሎት ፕሮግራሙን መጀመሩን ገልጿል።
ራሱን እንደ ፓስተር ቢጠራም በበለጠ የሚታወቀው በዘማሪነቱ ነው። በናይጄሪያ መዲና ሌጎስ በሚገኘው 'ሪዲምድ ክሪስቲያን' በተሰኘው ቤተክርስቲያን የወጣቶች ፓስተር እና የመዝሙር አገልጋይ ነው።
ፓስተር ናትናኤል ለፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ለምክትላቸው ቫንስ አክብሮት ለመግለጽ በተካሄደው የጸሎት የቁርስ ፕሮግራም ላይ የዘመረ ብቸኛው አፍሪካዊ አርቲስት ነው።
ፓስተሮቹ በፕሬዚዳንቱ በዓለ ሲመት ላይ ለምን ተገኙ?
ፓስተር ዊልያም በበዓለ ሲመቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉት "በአሜሪካ የሃይማኖት ነጻነት መመለሱን እና ሌሎችም አገራት ይህንን በሃይማኖት ላይ እየተደረገ ያለን ጥቃት እንዲዋጉ ድጋፍ ለማድረግ" እንደሆነ የወንጌል ስብከት አገልግሎታቸው በግሎባል ክሩሴድ ላይ የወጣው መግለጫቸው አትቷል።
ትራምፕ በኢቫንጀሊካን ክርስቲያን መራጮች ዘንድ ተወዳጅ ሲሆኑ፣ እሳቸውም የክርስቲያን ዕሴቶችን ለማስጠበቅ ቃል ገብተዋል።
በመጀመሪያ የፕሬዚዳንት ዘመናቸው ወቅት በአውሮፓውያኑ 2019 ትራምፕ በሃይማኖት ነጻነት ላይ ብቻ ያተኮረ የመጀመሪያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አስተናግደዋል።
በቀጣዩ ዓመትም፣ በአውሮፓውያኑ 2020 "በዓለም ዙሪያ ለሁሉም ሕዝብ የሃይማኖት ነጻነት መኖር የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ቀዳሚ ተግባር ነው" ሲሉ መመሪያ በማስተላለፍ ጽሁፋቸውን አስፍረዋል።
ፓስተር ዊልያም ኩሙዬ በዚህ ሲመተ በዓል ላይ በመጋበዛቸው ፓስተሩም ሆነ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚናገሩት በአምስተርዳም ቪርጀ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት ፕሮፌሰር የሆኑት ዲዮን ፎርስተር ናቸው።
ፓስተር ዊልያም በዓለም ላይ ካሉት ኃያል ሰው ጋር ጓደኛ ለመሆናቸው ማሳያ ይሆናቸዋል ይላሉ። ትራምፕ እና ቡድናቸው በበኩሉ የፓስተሩን ተወዳጅነት ተጠቅመው ተጽዕኖ መፍጠር ይችላሉ ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
"ትራምፕ ከብሔራዊ ፖለቲካ መዋቅር ውጪ እንዴት ነገሮች እንደሚሠሩ በትክክል ያውቃሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።
"[ የቀድሞው ፕሬዚዳንት] ጆ ባይደን ከአምባሳደሮች እና ከከፍተኛ የንግድ መሪዎች ጋር ግንኙነትን በመመሥረት ነው የሚታወቁት። ትራምፕ በበኩላቸው ሥልጣን ከእነዚያ መዋቅሮች ውጪ ያለው የት ነው የሚለውን በመፈተሽ እነዚያን ዓይነት ሰዎች ወደ እኔ እንዴት አቀርባለሁ ብለው የሚጠይቁ ሰው ናቸው" ይላሉ።
ማይኖሪቲ አፍሪካ የተሰኘው ያልተነገሩ ታሪኮችን የሚያጎላው በኦንላይን የሚታተም ድረገጽ መሥራች እና አዘጋጅ ካሌብ ኦኬሬኬ በበኩላቸው እንደ ፓስተር ዊልያም እና ናትናኤል ያሉ ታዋቂ የሃይማኖት ሰዎች ድጋፍ ለትራምፕ በአህጉሪቷ ሕዝባዊ ድጋፍ እንዲያገኙ እንዲሚረዳቸው ይናገራሉ።
የአሜሪካ ወግ አጥባቂዎች እና የአፍሪካ ኢቫንጀሊስቶች ያላቸው የጋራ የፖለቲካ አመለካከቶች ተመሳሳይ እንደሚያደርጋቸው ያምናሉ።
"የዓለም አቀፍ ወግ አጥባቂነት በሰፊው እየተሳሰረ ይገኛል። ፓስተሮቹ ዊልያም እና ናትናኤል የአሜሪካን ፖለቲካ እና የአህጉሪቱን ፖለቲካን ያጣመረውን ይህንን ወግ አጥባቂነት የሚወክሉ ናቸው ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።
"ከዚህም ባለፈ ስር የሰደዱ ነገሮችን የሚወክሉ ናቸው፣ ለምሳሌ በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት ላይ ያለውን ጥላቻ ትርክት አጀንዳን የመሳሰሉ አሰላለፍን ማመሳሰል ነው" ይላሉ።
ሆኖም በአፍሪካ ውስጥ ትራምፕን በተመለከተ "የሚጋጩ አስተያየቶች" እንዳለ ያምናሉ።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም በነበረው የሥልጣን ጊዜያቸው የአፍሪካ አገራትን በአጸያፊ ስድብ ዘልፈዋል። በተጨማሪም ናይጄሪያን ጨምሮ በአህጉሪቱ የሚገኙ በርካታ አገራትን ፍልሰትን በመገደብ አወዛጋቢ የሆነ የጉዞ እገዳ መደንገጋቸው ይጠቀሳል። ሆኖም በርካታ የአፍሪካ ፓስተሮች የትራምፕ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት እና በመሳሰሉ ዕይታቸው ምክንያት ይደግፏቸዋል።
ይህንንም አስመልክቶ "የሥርዓተ ፆታ አወቃቀር፣ የፍቅር/ወሲብ ዝንባሌ በርካቶች ሌሎች ነገሮችን እንዳያዩ እና ጭፍን እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው መመልከቴ አስገርሞኛል" ይላሉ ካሌብ።















