ትራምፕ በወታደራዊ አውሮፕላን የተላኩ ስደተኞችን አልቀበልም ባለችው ኮሎምቢያ ላይ ታሪፍ ጣሉ

ኮሎምቢያውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, US Government

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች የላኳቸውን ስደተኞችን አልቀበልም ባለችው ኮሎምቢያ ላይ 25 በመቶ ታሪፍ እጥላለሁ አሉ።

የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት አሜሪካ ያባረረቻቸውን ስደተኞች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተከትሎ ነው ይሄ ውሳኔ የተላለፈው።

በዚህም መሰረት ከኮሎምቢያ ወደ አሜሪካ በሚገቡ "ሁሉም እቃዎች ላይ" የሚጣለው 25 በመቶ ታሪፍ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንደሚሆን የተናገሩት ትራምፕ ከሳምንት በኋላ ወደ 50 በመቶ ከፍ እንደሚል አስጠንቅቀዋል።

የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት ጉስታቮ ፔትሮ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚሰጡ አስጠንቅቀው በአሜሪካ ላይ 25 በመቶ ታሪፍ እጥላለሁ ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ታሪፍ ከመጫኑ ቀደም ብሎ እሁድ ዕለት አሜሪካ ያባረረቻቸውን በሁለት ወታደራዊ አውሮፕላን የተጫኑ ስደተኞችን ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተናግረው ነበር። "

ዜጎቻችን እንደ ወንጀለኛ ሳይቆጠሩ በሲቪል አውሮፕላኖች ተጭነው ቢመጡ" እንደሚቀበሏቸው የተናገሩት የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት ስደተኞች ሲመለሱም ቢሆን ሰብዓዊነታቸውን በጠበቀ እና በክብር ሊሆን ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከሳንዲያጎ የተነሱ ስደተኞችን የጫኑ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች እሁድ ዕለት በኮሎምቢያ እንዲያርፉ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት ሊሳካ አለመቻሉን የአሜሪካ ባለስልጣናት ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

በምላሹ ትራምፕ "አስቸኳይ እና ወሳኝ የሚባሉ የበቀል እርምጃዎችን" እንደሚወስዱ በትሩዝ የማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ ለጥፈዋል።

አሜሪካ በኮሎምቢያ መንግሥት ባለስልጣናት፣ አጋሮቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው ላይ የጉዞ እገዳ እና አፋጣኝ የቪዛ ስረዛ እንደምታደርግ አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ በኮሎምቢያ መንግሥት ደጋፊዎች ላይ የቪዛ ማዕቀብ እንደሚኖር አስጠንቅቀው የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ መስሪያ ቤት "ሁሉም የኮሎምቢያ ዜጎችን እና ጭነቶችን" በብሔራዊ ደህንነት ዕይታ ውስጥ እንዲያስገቧቸው መመሪያ ሰጥተዋል።

"እነዚህ እርምጃዎች ገና እየጀመሩ ነው" ያሉት ትራምፕ አስተዳደራቸው የኮሎምቢያ መንግሥት "ወደ አሜሪካ የገቡትን ወንጀለኞቻቸውን መመለስ በተመለከተ ህጋዊ ግዴታዎቹን እንዲተላለፍ አይፈቅድም" ብለዋል።

የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት ፔትሮ በበኩላቸው በአሜሪካ ላይ ታሪፍ እጭናለሁ በማለት የአገራቸውን ቅርስ እና አይበገሬነት በገለጸ መልኩ በኤክስ ገጻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

"ክልከላህ አያስደነግጠኝም ምክንያቱም ኮሎምቢያ ውብ ሀገር ከመሆኗ በተጨማሪ የአለም ልብ ነች" ሲሉ ለትራምፕ መልዕክታቸውን አስተላልፈውላቸዋል።

ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቻቸው ክብሩን በጠበቀ ሁኔታ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ፔትሮ ፕሬዚዳንታዊ አውሮፕላን አቅርበዋል።

በኮሎምቢያ ከ15,666 በላይ አሜሪካውያን በህገወጥ መንገድ እንደሚገኙ ፕሬዚዳንት የተናገሩ ሲሆን ቢቢሲ ይህንን አሃዝ በተናጥል ማረጋገጥ አልቻለም።

ፕሬዚዳንቱ እነዚህ ህገወጥ የአሜሪካ ስደተኞች ለመመለስ እንደ ትራምፕ አስተዳደር "ወረራ አይፈጽምም" ብለዋል።

አሜሪካ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ፣ 20 በመቶ የሚሆነውን ቡና እንዲሁም ሙዝ፣ ድፍድፍ ነዳጅ፣ አቮካዶ እና አበባ ያሉ ምርቶችን የምታስገባው ከኮሎምቢያ ነው።