ሐማስ ስድስት ታጋቾችን ለመልቀቅ ሲስማማ እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ሰሜን እንዲገቡ ፈቀደች

አርቤል የሁድ

የፎቶው ባለመብት, Bring Them Home Now

የምስሉ መግለጫ, አርቤል የሄድ በሕይወት መኖሯን አደራዳሪዎች አረጋግጠዋል

በያዝነው ሳምንት ሐማስ ስድስት ታጋቾችን የሚለቅ ሲሆን እስራኤል ደግሞ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ሰሜናዊው ክፍል ወደሚገኘው ቀያቸው እንዲሄዱ እንደምትፈቅድ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ተናገሩ።

ከታጋቾቹ መካከል አርቤል የሁድ የተባለች እስራኤላዊት የምትገኝበት ሲሆን እስራኤል አርቤ ካልተለቀቀች ፍልስጤማዊያን ወደ ሰሜን ጋዛ እንዳያልፉ ከልክላ ነበር።

ባለፈው ቅዳሜ ሐማስ አራት ወታደሮች ለቋል። ነገር ግን አርቤል እስካሁን አልተለቀቀችም። ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሷል ስትል እስራኤል ወቅሳለች።

በስምምነቱ መሠረት ሲቪል እስራኤላዊያን ታጋቾች ከወታደሮች ቀድመው መፈታት በምትኩ በእስራኤል እስር ቤት የተያዙ ፍልስጤማዊያን መፈታት አለባቸው።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባር ላይ መዋል ከጀመረ ወዲህ ሰባት ታጋቾች እና ከ200 በላይ የተያዙ ፍልስጤማዊያን ተለቀዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩት ፍልስጤማዊያን ወደ ሰሜን ጋዛ መሻገር ፈልገው በእስራኤል ወታደሮች ክልከላ ተጥሎባቸው ቆይተዋል።

እስራኤል እና ሐማስ እስረኞችንና ታጋቾችን ለመልቀቅ እና ተኩስ አቁም ለማድረግ የተስማሙት በአውሮፓውያኑ ጥር 19 ሲሆን እስካሁን ሁለት ጊዜ ልውውጥ አድርገዋል።

ፍልስጤማዊት እናት ልጇን ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፍልስጤማዊን ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ወደ ሰሜን ጋዛ ለመግባት ሲጠባበቁ ነበር

በሶስተኛው ዙር ሐማስ አርቤል የሁድ እና ሌሎች ሁለት ታጋቾችን አርብ ዕለት ይለቃል። ቅዳሜ ደግሞ ሶስት ተጨማሪ ሰዎች ይለቃል ሲሉ ኔታኒያሁ እና የስምምነቱ አደራዳሪ ኳታር ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል ከሰኞ ጀምሮ ፍልስጤማዊያን ወደ ሰሜን ጋዛ እንዲገቡ ትፈቅዳለች። በተጨማሪም እስር ቤት ያሉ ፍልስጤማዊያንን ትለቃለች።

በስምምነቱ መሠረት ፍልስጤማዊያን ወደ ኔትዛሪም ኮሪደር ሰሜናዊ ክፍል መግባት ይችላሉ። ኔትዛሪም ኮሪደር በእስራኤል ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ሰባት ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሰርጥ ነው። ይህ ኮሪደር ጋዛን ከሌላው የፍልስጤም ግዛት ይለያል።

ምስሎች እንደሚያሳዩት በርካታ ሰዎች ወደ ሰሜን ጋዛ ለመግባት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

"መንገድ ላይ ነው እያደርን ያለነው" ስትል ኒሪም ሙሳቤህ ለቢቢሲ ትናገራለች። "ወደ ቤታችን መሄድ አንችልም። ወደ ቤታችን ለመሄድ ስንሞክር ይተኩሱብናል።"

የ42 ዓመቷ ፍልስጤማዊት ማዕከላዊ ጋዛ ከሚገኘው ዴር አል-ባላህ ተጉዛ ነው የመጣችው። ደቡባዊ ጋዛ ከሚገኘው ሼጃያ መንደር ተፈናቅላለች።

ዲያብ ሼህባሪ ደግሞ ቅዳሜ በአካካቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2፡30 ጀምሮ ለማለፍ ሲጠብቁ እንደነበር ይናገራል።

"ምሽቱን ሙሉ ሕፃናት በብርድ ምክንያት ሲያለቅሱ ነው ያደሩት። እሳት ለኩሰን ያገኘነው ደራርበን ነው ያስተኛናቸው።"

በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ስምምነቱ እንዲፈረም ያደራደሩት ኳታር እና ግብፅ በአርቤል ጉዳይ የተነሳውን እሰጥ አገባ ማሸማገላቸው ተሰምቷል።

እስራኤል አርቤል የሁድ በሕይወት ስለመኖሯ ማረጋገጫ እፈልጋለሁ ማለቷን ተከትሎ የግብፅ አደራዳሪዎች ይህን ለእስራኤል ማረጋገጣቸውን ቢቢሲ ተገንዝቧል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እሑድ በሰጡት አስተያየት ግብፅ እና ጆርዳን ፍለስጤማዊያንን ከጋዛ እንዲወስዱ ጠይቀዋል። ፕሬዝደንቱ ጋዛን "የወደመ ሥፍራ" ሲሉ ገልፀውታል።

ሐማስ እና የፍልስጤም አስተዳደር ይህን የትራምፕ ሐሳብ የነቀፉት ሲሆን ግብፅና ጆርዳንም እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።

ሐማስ በእስራኤል ምድር ጥቃት አድርሶ 1200 ሰዎ ገድሎ 251 ታጋቾች ይዞ መሄዱን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጦርነት ከ47 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።