ወደጋዛ የሚወስደው መንገድ በእስራኤል በመዘጋቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውን ወደቤታቸው መመለስ አልቻሉም

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በጋዛ ሰርጥ ወደሚገኝ ቤታቸው እንዳይመለሱ እስራኤል ዋና መንገዱን መዝጋቷ ተገለጸ።
እስራኤል ዋና መንገዱን የዘጋችው ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን አፍርሷል በሚል ነው።
በእስራኤልና ሐማስ መካከል ውዝግብ የተነሳው ሐማስ አራት እስራኤላዊ ሴት ወታደሮችን ከለቀቀ በኋላ እስራኤል 200 ፍልስጤማው እስረኞችን መልቀቋን ተከትሎ ነው።
እስራኤላዊቷ አርቤል ያሁድ እስከምትለቀቅ ድረስ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ሰሜናዊው ክፍል መጓዝ እንደማይፈቀድላቸው እስራኤል ገልጻለች።
ሐማስ አርቤል በሕይወት እንዳለችና በቀጣይ ሳምንት እንደምትለቀቅ ገልጿል።
ሐማስ ከወታደሮች በፊት ዜጎችን ለመመለስ ተስማምቷል።
ተፈናቃዮች ወደ ጋዛ ሊመለሱበት በነበረው አል-ራሺድ መንገድ ላይ የተኩስ ድምጽ ተሰምቷል።
ሮይተርስ እንደዘገበው አንድ ሰው ተገድሏል። ቢቢሲ ያላረጋገጠው ቪድዮ ላይም ተኩስ ይሰማል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በማዕከላዊ ጋዛ "የተሰባሰቡና ስጋት ናቸው ተብለው የተወሰዱ ሰዎች" ስለታዩ ተኩስ እንደነበር ገልጿል።
ወታደሮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል መተኮሱን አክሏል።
ወደ ጋዛ ለመመለስ እየጠበቁ ካሉት አንዱ የሆነው ሙሐመድ ኢማድ አል-ዲን "ቤቴ ፈርሶ ሊሆን እንደሚችል አውቃለሁ። ፀጉር አስተካካይ ነበርኩ። ወደ ሥራዬ መመለስ አለብኝ። ልጆቼን ማብላት ስላልቻልኩ ብዙ ገንዘብ ተበድሬያለሁ" ብሏል።
የእስራኤልና ሐማስ የ15 ወራት ጦርነት ተቋጭቶ ወደቀያቸው መመለስ እንደሚሹም ተናግሯል።
ናዛትሪም የሚባለው መተላለፊያ ሰባት ኪሎሜትር ይሸፋናል። በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ሲሆን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ የሚወስድ ዋነኛ መንገድ ነው።
በአካባቢው የምትገኘው ሉብና ናስር ከሁለት ልጆቿ ጋር ወደ ቤታቸው ለመሄድ እየተጠባበቁ ነው።
ለ11 ወራት ካላገኘችው ከባለቤቷ ሱልጣን ጋር ለመገናኘት ወደቤታቸው የሚወስዳት አህያ ተከራይታ ብትጠብቅም ማለፍ አልቻለችም።
"ልጆቼ ለወራት አባታቸውን ለማየት ጓጉተው ነበር። እዚሁ መተላለፊያ አካባቢ እጠብቃለሁ። ወደ ጋዛ ለመመለስ የመጀመሪያዋ መሆን እፈልጋለሁ" ትላለች።
የካታርና ግብፅ አደራዳሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
ሆኖም እስራኤል መተላለፊያ መንገዱን ዘግታዋለች።
ሐማስ የታገተችውን ሴት በሕይወት መኖር እንዲያረጋግጥ እስራኤል ጠይቃለች። ማረጋገጫው ለአደራዳሪዋ ግብፅ እንዲሰጥም አሳስባለች።












