በጥሎሽ ሕግ ምክንያት ራሱን ያጠፋው ባል

ራሱን ያጠፋው አቱልና ቤተሰቡ
የምስሉ መግለጫ, ራሱን ያጠፋው አቱል እና ቤተሰቡ

ባለፈው ኅዳር ወር መጀመሪያ ገደማ የ34 ዓመቱ ሕንዳዊ ራሱን አጠፋ። አስክሬኑ አጠገብም 'ፍትሕ ዘግይቷል' የሚል ጽሑፍ ተገኝቷል።

አቱል ሱባሽ ይባላል። ለምን ራሱን ለማጥፋት እንደወሰነ 24 ገጽ መልዕክት የተወ ሲሆን፣ 81 ደቂቃ ቪዲዮም ቀርጿል።

ለሞት ያበቃው ምስቅልቅል የትዳር እና የፍቺ ሕይወቱ እንደሆነ ተናግሯል።

ያስቀመጠው ደብዳቤ እና ቪዲዮ በሕንድ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ መነጋገሪያ ሆኗል። ብዙዎችም በደረሰበት ነገር ተቆጥተዋል።

አቱል በቤንጋሉሩ ግዛት የሶፍትዌር መሃንዲስ ነበር።

የቀድሞ ባለቤቱ ኒኪታ ሲንጋና እንዲሁም እናቷ እና ወንድሟ በተደጋጋሚ ትንኮሳ እና እንግልት እንዳደረሱበት ተናግሯል።

እነሱ ግን ይህ ሐሰት ነው ብለዋል። እራሱን ካጠፋው አማቻቸው ሞት ጋር በተያያዘም ኋላ ላይ ሦስቱም ታስረው በዋስ ተለቀዋል።

የአቱል ሞት የሕንድን የጥሎሽ ሕግ በተመለከተ ክርክር አስነስቷል።

ሕጉ ሴቶችን ከጥቃት እና ከግድያ ለመከላከል ያለመ ቢሆንም፤ አንዳንድ ሴቶች ባሎቻቸውን ለማንገላታት እየተጠቀሙበት ነው የሚል ትችት ተሰንዝሯል።

በዚህም ምክንያት ራሳቸውን ለማጥፋት የተገደዱ ባሎችም አሉ።

የሕንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በጉዳዩ ጣልቃ ገብቷል።

ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ የወንዶች መብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

አንድ ዳኛ ሁኔታውን "ሕጋዊ ሽብር" ሲሉ ነው የገለጹት።

የሴቶች መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ግን፣ የባሎች ቤተሰቦች ከፍተኛ ጥሎሽ መጠየቃቸው በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል።

አቱል እና ኒኪታ የተጋቡት በአውሮፓውያኑ 2019 ነው። ለሦስት ዓመታት ለየብቻ ኖረዋል።

የአራት ዓመት ልጃቸውን ማየት መከልከሉን አቱል ይናገራል።

በተጨማሪም ባለቤቱ "ሐሰተኛ የፍርድ ቤት ወረቀቶች" በማቅረብ በጭካኔ፣ በማሰቃየት እና ሌሎችም እኩይ ድርጊቶች እንደከሰሰችው ተናግሯል።

የቀድሞ ባለቤቱ ኒኪታ ሲንጋና እንዲሁም እናቷና ወንድሟ

የፎቶው ባለመብት, Bengaluru police

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ ባለቤቱ ኒኪታ ሲንጋና እንዲሁም እናቷ እና ወንድሟ ታስረው ነበር

አቱል የባለቤቱ ቤተሰቦች "የገንዘብ ብዝበዛ" እንዳደረሱበትም ገልጿል።

የመሠረቱበትን ክስ ለማቋረጥ 30 ሚሊዮን ሩፒ (የሕንድ ገንዘብ)፣ ልጁን መጎብኘት እንዲችል 3 ሚሊዮን ሩፒ እንዲከፍል እና ወርሃዊ የዕድሳት ወጪውን ከ40 ሺህ ሩፒ ወደ 200 ሺህ ሩፒ ከፍ እንዲያደርግም አስገድደውታል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመከታተል ረዥም ርቀት ለመጓዝ መገደዱንም ገልጿል።

ዳኛው ጉቦ እንደጠየቀው እና ይቀልድበት እንደነበርም ተናግሯል።

ዳኛው ግን ክሱን "መሠረት ቢስ ስም ማጥፋት" ሲል አጣጥሏል።

የወንዶች መብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
የምስሉ መግለጫ, የወንዶች መብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

አቱል ራሱን የማጥፋቱ ዜና ሲሰማ በብዙ የሕንድ ከተሞች ተቃውሞ ተካሂዷል። በማኅበራዊ ሚዲያም የተቃውሞ ድምጾች ተስተጋብተዋል።

ራሱን ማጥፋቱ በሚስቱ እንደተፈጸመ ግድያ እንዲወሰድም ተጠይቋል። የቀድሞ ባለቤቱ ታስራ ዕድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድባትም ተቃዋሚዎች ጠይቀዋል።

ከምትሠራበት የአሜሪካ ተቋም እንድትባረር በኤክስ ላይ የጠየቁም አሉ።

የቤንጋሉሩ ፖሊስም በጉዳዩ ላይ ምርመራ ከፍቷል። አቱል ራሱን ያጠፋበትን ደብዳቤ ማስረጃ በማድረግ የቀድሞ ባለቤቱ፣ እናቷ እና ወንድሟ አቱልን "ራሱን እንዲያጠፋ በመገፋፋት" ተከሰዋል።

የቀድሞ ባለቤቱ ለገንዘብ ብላ ብዝበዛ እንዳላደረሰችበት ተናግራለች።

ቤተሰቦቿ በሰጡት ጥሎሽ ስላልተስማሙ 1 ሚሊዮን ሩፒ እንዲጨምር መጠየቃቸውን ገልጻለች።

ከዚህ ቀደም ባለቤቷ ላይ ጠንካራ ክስ ሰንዝራለች። በ2022 ደግሞ ለፍቺ አመልክታለች።

የባሏ ቤተሰቦች እና ወንድሞች በጥሎሽ ምክንያት ትንኮሳ እንዳደረሱባትም ተናግራለች።

በሕንድ ከ1961 ወዲህ ጥሎሽ በሕግ ታግዷል። ሆኖም ግን የሚስት ቤተሰቦች ለባልየው ቤተሰቦች ጥሎሽ እንዲሰጡ ይጠበቃል።

አቱል እና እናቱ
የምስሉ መግለጫ, አቱል እና እናቱ

በሕንድ ከ1950 እስከ 1999 ባሉት ዓመታት ለጥሎሽ የተሰጠ ገንዘብ ሩብ ትሪሊዮን ዶላር እንደሚሆን በቅርቡ የተሠራ ጥናት ጠቁሟል። ከሕንድ ጋብቻዎች 90 በመቶው ጥሎሽ አላቸው።

ከ2017 እስከ 2022 ድረስ 35 ሺህ 493 ሴቶች (በቀን በአማካይ 20 ሴቶች) ከጥሎሽ ጋር በተያያዘ ተገድለዋል።

በ2022 ውስጥ 6,450 ሴቶች ተገድለዋል።

ኒኪታ እንደምትለው ባሏ ተጨማሪ ጥሎሽ ሲጠይቅ አባቷ በድንጋጤ ሞተዋል።

ባለቤቷ ያስፈራራት እና ይደበድባት እንደነበረም ተናግራለች።

"እየጠጣ ይደበድበኝ ነበር። ተፈጥሯዊ ያልሆነ ወሲብ እንድንፈጽም ይጠይቅ ነበር" ብላለች።

ባለቤቷ ይህንን ክስ አስተባብሏል።

ፖሊስ የባል እና ሚስቱን ጉዳይ እየመረመረ ሳለ ነው ባልየው ራሱን ያጠፋው።

አቱል ራሱን የማጥፋቱ ዜና ሲሰማ በብዙ ከተሞች ተቃውሞ ተካሂዷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አቱል ራሱን የማጥፋቱ ዜና ሲሰማ በብዙ ከተሞች ተቃውሞ ተካሂዷል።

የሕንድ የጥሎሽ ሕግ እአአ በ1983 የተቀየረው ከጥሎሽ ጋር በተያያዘ ሚስቶች በየቀኑ በባሎቻቸው እና በባሎቻቸው ቤተሰቦች በእሳት እየተቃጠሉ እና እየተገደሉ ስለነበር ነው።

የሕንድ ሴት የሕዝብ እንደራሴዎች ናቸው ሕጉን ያስለወጡት።

ጠበቃዋ ሱኪቲ ቻውን "ሕጉ የተቀየረው ከረዥም ትግል በኋላ ነው። ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው ጥቃት ሲፈጸምባቸው ፍትሕ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው" ትላለች።

የወንዶች መብት ተሟጋቾች ግን ሕጉን ሚስቶች ባሎቻቸውን ለማንገላታት እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ ይከሳሉ።

የሕንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሕጉ እንዳይበዘበዝ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

በሙምባይ ለወንዶች መብት የሚታገል ተቋም የመሠረተው አሚት ዲሽፓንዴ ሕጉ "ወንዶችን ይጎዳል" ይላል።

በተቋሙ የነጻ የስልክ መስመር ዘርግቶ በየዓመቱ 86,000 አቤቱታዎች እንደደረሱት ተናግሯል።

"ከ18 እስከ 20 ሰዎች ይከሰሱ እና ሁሉም ጠበቃ ማቆም ግዴታቸው ይሆናል። የሁለት ወር ሕጻናት ሳይቀሩ የጥሎሽ ሕግ ክስ ውስጥ ገብተው ያውቃሉ። ፖሊስ እና ፍርድ ቤትም ችግራችንን ችላ ብሎታል" ይላል።

ከ50 ዓመታት በላይ በአብዛኛው ራሳቸውን የሚያጠፉት ወንዶች መሆናቸውን ይናገራል።

"ሴቶች ይታዘንላቸዋል። ወንዶች በሚስቶቻቸው መደብደባቸውን ሲናገሩ ግን ይሳቅባቸዋል። ሕጉ ፆታ መለየት የለበትም። ወንዶችም ፍትሕ ይሻሉ" ሲልም አክሏል።

የሕግ ባለሙያዋ ሱኪቲም ሕጉ ሊበዘበዝ እንደሚችል ትናገራለች።

"ሕጉ ፆታ አይለይ የሚለውን ግን አልስማማበትም። ይሄ አስተሳሰብ ኋላ ቀር ነው። በጥቃት በዋነኛነት የሚጎዱት ሴቶች ናቸው። ለሴቶች የወጣ ሕግ ስለሆነ አባታዊው ሥርዓት ሊያስወግደው ይፈልጋል" ስትል ትከራከራለች።