የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የኤም 23 አማፂያን በኳታር የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተወካይ ሱምቡ ሲታ ማምቡ እና የ ኤም 23 ቡድን ዋና ፀሃፊ ቤንጃሚን (በቀኝ) ምቦኒምፓ በኳታር ስምምነት ተፈራርመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የኤም 23 አማፂያን በኳታር በተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል።

ቢቢሲ የተመለከተው እና የመርሆዎች መግለጫ የሚል ስያሜ የተሰጠው የቅዳሜው ስምምነት ሁለቱም ወገኖች ከጥቃት፣ "የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ" እና "በመሬት ላይ ያሉ አዳዲስ ቦታዎችን በኃይል ለመያዝ ከሚደረጉ ሙከራዎች" መቆጠብ አለባቸው ይላል።

መግለጫው ወደ ቋሚ ስምምነት ያደርሳል ተብሎ የታሰበ ፍኖተ ካርታ ነው።

ሁለቱ ወገኖች የስምምነቱን ውሎች እስከ ሐምሌ 22 ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል።

የመጨረሻው የሰላም ስምምነት በነሐሴ 12 የሚጠናቀቅ ሲሆን ባለፈው ወር በአሜሪካ አደራዳሪነት በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ኤም 23 ትደግፋለች የሚለውን ውንጀላ ውድቅ ካደረገችው በሩዋንዳ መካከል ከነበረው ስምምነት ጋር መጣጣም አለበት።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኤም 23 አማፂያን በማዕድን የበለፀገውን ምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ጎማን፣ የቡካቩ ከተማን እና ሁለቱን አየር ማረፊያዎችን ሲቆጣጠሩ ለአስር ዓመታት የዘለቀው ግጭት ተባብሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው እንደተፈናቀሉ ተናግሯል።

ኤም 23 በበኩሉ 1,000 ያነሱ ሰዎች ሞተዋል ሲል የመንግሥታቱን ድርጅት አሃዝ አጣጥሎታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ እንዳሉት ስምምነቱ ኤም 23 ከያዛቸው አካባቢዎች "ያል ድርድር እንዲወጣ" ማድረግን ጨምሮ የመንግሥትን "ቀይ መስመር" ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።

ነገር ግን በኤክስ ላይ በተለጠፈው ቪዲዮ ላይ የኤም 23 ተደራዳሪ ቤንጃሚን ምቦኒምፓ ስምምነቱ እንደዚህ ያለ [ከአካባቢዎች] መውጣትን አልጠቀሰም ብለዋል።

ይህ ስምምንት አማፂያኑ በዓመቱ መባቻ ላይ ጥቃታቸውን ከከፈቱ በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል የመጀመሪያው ቀጥተኛ ስምምነት ነው።

ኳታር ድርድሩ እንደሚቀጥል ተናግራለች።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መግለጫውን በቀጣናው ዘላቂ የሰላም ጥረት እና ፀጥታን ለማስፈን ትልቅ ምዕራፍ ነው ብሎታል።

መግለጫው በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመንግሥት ስልጣንን ወደነበረበት ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነትም ይዘረዝራል።

ይህ በቀጠናው ከተደረጉ የከሸፉ የሰላም ስምምነቶች ውስጥ የመጨረሻው ነው።

በአሁኑ ግጭት ዋነኛ ተዋናዮች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የኤም 23 አማፂያን የተፈለፈለው ከ16 ዓመታት በፊት ከከሸፈው የሰላም ስምምነት ነው።

በመጋቢት ወር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ እና የሩዋንዳው አቻቸው ፖል ካጋሜ በኳታር ተገናኝተው ሁለቱም አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በቀጣዩ ወር የዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ኤም 23 ቡድን በኳታር አመቻችነት በተደረገው ስምምነት የተኩስ ለማቆም ቢስማሙም ግጭቱ ግን ቀጥሎ ነበር።

በሰኔ ወር የተፈጸመው የዋሽንግተን ስምምነት ለአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ቁልፍ ማበረታቻ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ሰፊ የማዕድን ሀብት ማግኘት በመሆኑ ሰፊ ትችት አስተናግዷል።

ምንም እንኳን ቀን ባይወሰንም ቲሺሴኪዲ እና የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ትራምፕን ለማግኘት ወደ ዋሽንግተን እንደሚሄዱ ተነግሯል።