የቀድሞው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝደንት በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰሱ

ጆሴፍ ካቢላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጆሴፍ ካቢላ የኤም 23 አማፂያንን ይደግፋሉ በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀድሞ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላ ላይ የተመሠረተው የአገር ክህደት ወንጀል ክስ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ በሚገኝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት መታየት ጀመረ።

በቀድሞ ፕሬዝደንቱ ላይ የቀረበው ኤም23 የተባሉትን አማፂያን ይደግፋሉ ከሚለው ክስ ጋር የተያያዙ እንደ ግድያ ያሉ ሌሎች ክሶች ተጨምረዋል።

ኤም23 አማፂያን በበርካታ ማዕድን የበለፀገውን የአገሪቱን ምሥራቃዊ ክፍል ይቆጣጠራሉ።

ጆሴፍ ካቢላ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገው ችሎቱን ተችተዋል።

አገሪቱን የሚመሩት ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ የቀድሞውን ፕሬዝደንት ከአማፂያኑ ጀርባ በመሆን ድጋፍ ይሰጣሉ ሲሉ ይወነጅሏቸዋል።

ጆሴፍ ካቢላ ክሱን "በዘፈቀደ" የቀረበ ሲሉ ውድቅ አድርገው፣ ፍርድ ቤቶች "ለጭቆና መሳሪያ" በመሆን እያገለገሉ ነው ብለዋል።

ባለፈው ሳምነት በአማፂያኑ እና በመንግሥት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢሆንም ውጊያ ግን እንደቀጠለ ነው።

ካቢላ በደቡብ አፍሪካ በስደት ለሁለት ዓመታት ሲኖሩ ቆይተው በግንቦት ወር በአማፂያን ቁጥጥር ስር ወደ ምትገኘው ጎማ ከተማ ተመልሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እጅግ በጣም ብዙ ማስረጃዎችን በመጥቀስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በርካታ ምዕራባውያን እና ጎረቤት አገር ሩዋንዳን የኤም23 አማፂያንን ትደግፋለች፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ልካለች ሲሉ ይከስሷታል።

ነገር ግን ኪጋሊ ግጭቱ ወደ ግዛቷ እንዳይስፋፋ ለመከላከል እየጣረች መሆኑን በመጥቀስ ክሱን ውድቅ አድርጋለች።

በግንቦት ወር የዶሞክራቲክ ኮንጎ የላይኛው የሕግ አውጪ ምክር ቤት በአገር ክህደት፣ በግድያ፣ በአመጽ እንቅስቃሴ እና የጎማ ከተማ ላይ ወረራ ሲፈጸም በመሳተፍ ክስ እንዲመሠረትባቸው በሚል የካቢላን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።

የ53 ዓመቱ ካቢላ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ለ18 ዓመታት መርተዋል።

ካቢላ የፕሬዝደትነት ሥልጣኑን የተረከቡት በአውሮፓውያኑ 2001 አባታቸው ሎረን ካቢላ በጠባቂያቸው መገደላቸውን ተከትሎ ነበር።

ጆሴፍ ካቢላ ሥልጣኑን ሲረከቡ የ29 ዓመት ወጣት ነበሩ።

በ2019 የተደረገ አከራካሪ ምርጫን ተከትሎ ሥልጣኑን ለፕሬዝደንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ ያስረከቡ ቢሆንም በኋላ ግን በመካከላቸው ቅራኔ ተፈጥሯል።

በግንቦት ወር በተለቀቀው እና አሁን በጠፋ የዩቲዩብ ቪዲዮ ላይ ካቢላ የኮንጐ መንግሥትን "አምባገነን" በማለት ነቅፈውበአገሪቱ "የዲሞክራሲ ማሽቆልቆል" መኖሩን ተናግረዋል።

በወቅቱ የኮንጎ መንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ የካቢላን ውንጀላ ውድቅ በማድረግ "ለአገሪቱ የሚያበረክቱት ምንም ነገር የለም" ብለው ነበር።

ከአርብ ከተካሄደው ችሎት በፊት የካቢላ የቅርብ አጋር የነበሩት እና አሁን የታገደው ፒፒአርዲ ፓርቲ መሪ፣ መንግሥትን "አድሏዊ" ሲሉ ከስሰዋል።

መንግሥት በሰላም ስምምነቱ ላይ በጣም ለስላሳ ቢሆንም፣ በካቢላ ላይ በጣም ከፍቷል በማለት ክሱ ካቢላን ከአገሪቱ ፖለቲካ የማግለል መንገድ ነው ብለዋል።