ከ30 ኢትዮጵያውያን ሞት ጋር በተያያዘ የታሰረው ግለሰብ በዋስ እንዲፈታ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, MALAWI POLICE
ባለፈው ጥቅምት ማላዊ ውስጥ በጅምላ ተቀብረው ተገኙ ከተባለው የኢትዮጵያውያን አስከሬን ጋር በተያያዘ ተጠርጥሮ የነበረው የቀድሞው ፕሬዝዳንት የእንጀራ ልጅ በዋስ ተለቀቀ።
የቀድሞው የማላዊ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ የእንጀራ ልጅ በከባድ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ለሁለት ወራት በእስር ላይ ቆይቶ ነበር።
ታዲኪላ ማፉብዛ የተባለው የቀድሞው ፕሬዝዳንት የእንጀራ ልጅ፣ ባፈው ጥቅምት ወር ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው የተባሉ እና በጅምላ ተቀብረው ከተገኙ 30 ሰዎች ሞት ጋር በተያያዘ ነው ለእስር የተዳረገው።
ተጠርጣሪው ግን በጅምላ ተቀብረው በተገኙት ሰዎች ሞት ምክንያት የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።
የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ረቡዕ የተጠርጣሪውን ጉዳይ ከተመለከተ በኋላ ሁለት ሚሊዮን ክዋቻ (የማላዊ ገንዘብ) ወይም ሁለት ሺህ ዶላር እንዲያስይዝ፣ እንዲሁም እያንዳንዳቸው የአምስት ሺህ ዶላር ዋስትና የሚሆኑ ሁለት ተያዦች እንዲያቀርብ ወስኗል።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ዋስትናውን በፈቀደበት ጊዜ ተጠርጣሪው ከማላዊ እንዳይወጣ ፓስፖርቱን እና ሌሎች የጉዞ ሰነዶቹን ለፖሊስ እንዲያስረክብ አዟል።
ታዲኪላ ማፉብዛ የዋስትና መብት ሲፈቀድለት በችሎቱ ውስጥ ያልተገኘም ነበር ተብሏል።
ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው ከተከሰሰበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምስክር ሊሆኑ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ እና በየሁለት ሳምንቱ ማክሰኞ ወደ አገሪቱ ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በመቅረብ ሪፖርት እንዲያደርግ አዟል።
ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ ምዚምባ በሚባለው የማላዊ ሰሜናዊ ግዛት በሚገኝ ጥብቅ ደን ውስጥ ነበር የኢትዮጵያውያን ናቸው የተባሉ የሰላሳ ሰዎች አስከሬን በጅምላ ተቀብሮ መገኘቱን ፖሊስ ያሳወቀው።
ፖሊስ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ “ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው” በማለት ዕድሜያቸውም ከ25 እስከ 40 እንደሆን ገልጾ ነበር።
በአስከሬኖቹ ላይ በተደረገው ምርመራ በተገኘው ውጤት ኢትዮጵያውያኑ ለሞት የተዳረጉት በሕገ ወጥ መንገድ በድብቅ እንዲዘዋወሩ በሚደረግበት ጊዜ ባጋጠማቸው መታፈን መሆኑ ታውቋል።
ፖሊስ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት የእንጀራ ልጅ በቁጥጥር ስር ያዋለው 30ዎቹን ሰዎች ለማጓጓዝ የእሱ ንብረት የሆነው መኪና ጥቅም ውሏል በመባሉ ነው። የመኪናው ሾፌርም በፖሊስ ታስሮ እንደነበር ተነግሯል።
ከዚህ ክስተት በኋላም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሟቾቹ ሁኔታ ላይ ምርመራ ለማድረግ እና ከማላዊ ባለሥልጣናት ጋር በመተባባር አስፈላጊውን ነገር ለማከናወን አንድ ቡድን ወደ ወደ ስፍራው አሰማርቶ ነበር።
በተመሳሳይ ባለፈው ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ 27 የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ነው የተባሉ አስከሬኖች ዛምቢያ ውስጥ መንገድ ዳር ተጥለው መገኘታቸው ይታወሳል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት የተለያዩ አገራትን በማቆራረጥ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመድረስ ኬንያን፣ ታንዛኒያን ዛምቢያን እና ሌሎች የደቡባዊ አፍሪካ አገራትን ያቋርጣሉ።
በዚህም ሳቢያ ስደተኞቹ በከባድ ጥቃት እና ማጭበርበር ውስጥ ያልፋሉ፤ በርካቶች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በጅምላ እና በተናጠል ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸው መዘገቡ የታወሳል።
የማላዊ መንግሥት ወንዶችን፣ ሴቶችን እና ልጆችን ሳይቀር በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ወደ አሜሪካ እና ወደ አውሮፓ የሚያዘዋውሩ የተደራጁ የወንጀለኛ ቡድኖችን መቆጣጠር ትልቅ ፈተና ሆኖበታል።












