በግብፅ 10 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን ጥንታዊ ሐውልትን ሊሰርቁ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ግብፅ ውስጥ 10 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን ግዙፍ ከአለት የተጠረበ የጥንታዊ ፈርኦን ሐውልትን ሊሰርቁ የነበሩ ሦስት ሰዎች መያዛቸው ተገለጸ።
ግለሰቦቹ 10 ቶን የሚመዝነውን ግዙፍ ጥንታዊ የፈረንኦን ራምሴስ ሁለተኛን ሐውልት ካለበት ለመንቀል እና ለመውሰድ ባደረጉት ሙከራ የከባድ ዕቃዎች ማንሻ የሆነ ክሬን መጠቀማቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ከዋና ከተማዋ ካይሮ በስተደቡብ 675 ኪሎሜትር ላይ ከምትገኘው አስዋን ውስጥ ጥንታዊውን ቅርስ ለመስረቅ የሞከሩት ሦስቱ ሰዎች “የፈርኦን ሐውልትን ለመስረቅ በመሞከር” ተከሰዋል።
ፖሊስ በግለሰቦቹ ላይ የሚያካሂደውን ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስም ለአራት ቀናት በእስር ላይ እንዲቆዩ መታዘዙን የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ከዐቃቤ ሕግ የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ከሦስቱ ግለሰቦች ጋር “ሐውልቱን ከስሩ ቆፍሮ ለማውጣት እና ለማንጠልጠል የሚያገለግሉ የመቆፈሪያ መሳሪያዎች እና ክሬን” በፖሊስ ቁጥጥር ውሏል።
የአስዋን አካባቢ ጥንታዊ ቅርሶች ባለሥልጣን እንዳረጋገጠው ግለሰቦቹ ነቅለው ሊወስዱት የነበረው ሐውልት “የራምሴስ ሁለተኛ ሲሆን፣ ክብደቱም ወደ አስር ቶን የሚጠጋ ነው” ብሏል ባወጣው መግለጫ።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደዘገበው የግብፅ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት “በዚህ የቅርስ ዘረፋ ሙከራ ወንጀል ውስጥ ተሳትፈዋል የሚባሉ ሌሎች ሰዎች ካሉ በአስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግ” አዟል።
በዘራፊዎች ተነቅሎ ሊወሰድ የነበረው ሐውልት የቆመለት ራምሴስ ሁለተኛ፣ የ19ኛው ሥርወ መንግሥት ዝነኛ ፈርኦን ለ67 ዓመታት በገዢነት የቆየ ሲሆን፣ ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት መሞቱ ይነገራል።
በተጨማሪም ራምሴስ ሁለተኛ በታላቅ ጦረኛነት እና በመላዋ ግብፅ በርካታ ቤተ መቅደሶች እንዲገነቡ ያደረገ ጥንታዊ ገዢ በመሆኑ ይታወቃል።
በርካታ ጥንታዊ ቅርሶች ከግብፅ እየተሰረቁ ወደ ሌሎች አገራት ሲወሰዱ መቆየታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ባለፉት 10 ዓመታት ከአገሪቱ በሕገወጥ መንገድ ተወስደዋል የተባሉ 29ሺህ የሚሆኑ ጥንታዊ ቅርሶችን ለማስመለስ እንደተቻለ ይነገራል።












