የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት እና ሌሎች ኃይሎችን ማስወጣት በይፋ መጀመሩ ተገለጸ

የጦር መሳሪያ ርክክብ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defence Force

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የትጥቅ ማስፈታት እና ከፌደራሉ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎችን የማስወጣት ሂደት በይፋ መጀመሩን የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ አካል ገልጸ።

ሁለቱ ወገኖች በፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ ላይ የደረሱትን ስምምነት ተግባራዊነት በተመለከተ የኅብረቱ ተቆጣጣሪ ቡድን ማክሰኞ ዕለት መቀለ ላይ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ በዚህም ከሁለቱም ወገኖች የሚጠበቀው ተግባር መጀመሩን አሳውቋል።

በተመሳሳይ የአገር መከላከያ ሠራዊት በስምምነቱ መሠረት የከባድ መሳሪያዎች ርክክብ ተጀምሯል ብሏል።

በቀጠናው የተሰማራው ሠራዊት አመራር ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ የተለያዩ ዓይነት ከባድ መሳሪያዎችን መረከባቸውን መግለጻቸውን ጦሩ አስታውቋል።

ህወሓት ለመከላከያ ሠራዊት ካስረከባቸው መሳሪዎች መካከል ብረት ለበስ ታንኮች፣ የተለያዩ ሚሊ ሜትር መድፎች፣ ሮኬቶች፣ ዙዎች፣ ሞርታሮች እና ፐምፐን ይጨምራል ተብሏል።

የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት ጌታቸው ረዳ በተመሳሳይ የትግራይ ኃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን ማስረከባቸውን አረጋግጠዋል።

የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዘገባው የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ ቡድን “ወታደራዊ ቁሳቁሶች ርክክብ ሲከናወን ታዝበናል” ማለታቸውን ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ትግራይ ቴሌቪዥን፣ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች፣ ከባድ መሳሪያ የተገጠመባቸው ተሽከርካሪዎች፣ መድፎች፣ ጸረ ታንክ መሳሪያዎች ጨምሮ ርክክብር ሲደረግ አሳይቷል።

የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ለሁለት ዓመት የዘለቀውን የርስ በርስ ጦርነት በዘላቂነት ለማቆም በደረሱት የሰላም ስምምነት፤ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቃቸውን በመፍታት ለፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እንደሚያስረክቡ እና ከፌደራሉ መንግሥት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ አካባቢዎች እንደሚወጡ መገለጹ ይታወቃል።

በዚሁ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ኃይሎች ተወካዮች በበኩላቸው ትጥቅ የማስፈታት፣ ተዋጊዎችን የመበተን እና መልሶ የማቋቋም ሥራው በይፋ መጀመሩን መናገራቸው ተዘግቧል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ ቡድን ባለበት ከመቀለ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አጉላ ከተማ የከባድ ጦር መሳሪያ ርክክብር ተካሂዷል ሲል ዘግቧል።

ሌሎች ኃይሎችን ከትግራይ ማስወጣት

በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች ከትጥቅ ማስፈታቱ ጎን ለጎን ይከናወናል የተባለው የፌደራሉ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ የመውጣቱ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ግጭት ከቆመ ሁለት ወራት ያለፉት ቢሆንም የትጥቅ መፍታቱ እና ሌሎች ኃይሎችን የማስዋጠት ሂደቱ ጊዜ ፈልጎ ቆይቷል።

በኬንያ ናይሮቢ ለሁለት ጊዜ በተደረገው ውይይት ሁለቱ ወገኖች ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የትግበራ ስምምነቶች ማድረጋቸው ይታወሳል።

ለዚህም በሽምግልና ቁልፍ ሚና የነበረው የአፍሪካ ኅብረት የስምምነቱን አተገባበር ለመከታተል የዘረጋው የመከታተያ፣ የመቆጣጠሪያ እና የማረጋገጫ ሥርዓት መዋቀሩ ይፋ የሆነው ከሁለት ሳምንት በፊት መቀለ ላይ ነበር።

በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊነት እንዲያስፈጽሙም ሦስት አፍሪካውያን መኮንኖች በአፍሪካ ኅብረት ተሰይመው ሥራ ከጀመሩ በኋላ ነው ማክሰኞ ዕለት ስለሂደቱ መጀመር መቀለ ላይ መግለጫ የሰጡት።

ከባድ ጦር መሳሪያ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defence Force

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የወደመ ታንክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የወደመ ታንክ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኅብረቱ ያዋቀረው የመከታተያ፣ የመቆጣጠሪያ እና የማረጋገጫ ሥርዓት በኬንያዊው ሜጀር ጄኔራል ራዲና ስቲፈን፣ በናይጀሪያዊው ኮሎኔል ኡመር ማይራጋ እና በደቡብ አፍሪካው ኮሎኔል ቴፎ ሰኮል የሚመራ ነው።

የተደረሰው ስምምነት እና የተቆጣጣሪ ቡድኑ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው ስምምነት አንቀጽ 6 መሠረት፣ ተዋጊ ወገኖች ከጦርነት ቀጠና እንዲርቁ እንደሚደረግና ይህንንም ተከትሎ፣ የህወሓት ኃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን ሲፈቱ፣ የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ ይወጣሉ። በተጨማሪም ቀላል መሳሪያ የመፍታት ሂደትን በተመለከተ ዝርዝር የአፈጻጸም ዕቅድ ይወጣል ይላል።

ለሁለት ጊዜ ናይሮቢ ላይ ከተደረገው ንግግር በኋላም ከፌደራል መንግሥቱ እና ከህወሓት የተወጣጡ አባላት ያሉበት ኮሚቴ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የባለሙያዎች ቡድንን ያካተት የቁጥጥር፣ የማረጋገጫ እና የስምምነቱ መከበሩን የሚከታተል ሥርዓት እንዲኖር ከስምምነት ደርሰዋል።

በዚህ ቡድን ውስጥ መንግሥት እና ህወሓት፣ ድርድሩን ሲመራ የቆየው የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ቡድን እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) እያንዳንዳቸው አንዳንድ ተወካዮች የሚኖራቸው ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት ተወካዩ የቡድኑ ሊቀ መንበር ይሆናል።

የመንግሥት፣ የህወሓት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ ተወካዮችን እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የባለሙያዎች ቡድን ያጣመረው ቡድን መንግሥት እና ህወሓት የደረሱትን የሰላም ስምምነት እንዲሁም የጦር መኮንኖቹ የተፈራረሙትን የአፈጻጸም ስምምነት የሚጥስ ተግባር በየአፍሪካ የባለሙያዎች ቡድን አማካይነት ሪፖርት ሲደረግ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ መፍትሄ የሚሰጥ ነው።

ተቆጣጣሪ ቡድኑ በሰላም ስምምነቱ መሠረት የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሂደት መጠናቀቁን እና የህወሓት ተዋጊዎች ዳግም የጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ እንዳይዙ እና ያልተፈቀ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዳያደርጉ የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።

በተጨማሪም የህወሓት ተዋጊዎች የሚፈቱት ትጥቅ የሚቀመጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በለያቸው ቦታዎች መሆኑን ማረጋገጥ የሚሉት ኃላፊነቶች ለዚህ ጥምር ቡድን ተሰጥቶታል።

ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገ ድርድር ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ በሚያስችሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።