የኢሰመጉ ሠራተኞች “በአስቸኳይ” እና “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” እንዲፈቱ አምነስቲ ጠየቀ

እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አምነስቲ በሥራ ላይ ሳሉ በኢትዮጵያ የጸጥታ አካላት የታሰሩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ባልደረቦች “በአስቸኳይ” እና “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” እንዲፈቱ እና በእነርሱ ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲነሳ ጠየቀ።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ጥር 2/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ የኢሰመጉ ሠራተኞች የታሰሩት በአዲስ አበባ በኃይል ከመኖሪያቸው እንዲነሱ ስለተደረጉ ሰዎች መረጃዎችን እያሰባሰቡ ሳለ ነው ብሏል።

ዳንኤል ተስፋዬ፣ ብዙአየሁ ወንድሙ፣ በረከት ዳንኤል እና ናሆም ሁሴን የተባሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ ሠራተኞች ታኅሳስ 27/ 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ አለም ባንክ አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አምነስቲ በመግለጫው ጠቅሷል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ታይግሪ ቻጉታህ አራቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይህ ነው የሚባል ወንጀል እንዳልሰሩና በአዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ከቀያቸው በግድ መፈናቀላቸውን ተከትሎ መረጃዎችን እያሰባሰቡ እንደነበር ገልጸዋል።

"መጀመሪያውኑ መታሰር ባይገባቸውም በአስቸኴይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው። ማንም ሰው የሰብዓዊ መብት ሥራ በመስራቱ ሊወነጀል አይገባም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ባልደረቦቹ በአዲስ አበባ ያለ አግባብ ቤታቸው እየፈረሰባቸው እንደሆነ የገለጹ ግለሰቦችን ቅሬታ ለመመርመር ሦስት ሠራተኞቹ እና አሽከርካሪው ወደ አለም ባንክ አካባቢ ማምራታቸውን አስታውሷል።

ከዚያ በኋላ የት እንዳሉ ማወቅ ሳይችል ቆይቶ ከብዙ ጥረት በኋላ አለም ገና 02 ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንዳገኛቸው ገልጿል።

ጉባኤው አክሎም በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በርካታ ማስፈራሪያዎች እና ጫናዎች እየደረሰብኝ ነው ብሏል።

ድርጊቱ ሕገ-ወጥ እና ጉባኤው የሚሰራቸውን የሰብዓዊ መብት ሥራዎች ለማደናቀፍ የሚደረግ ጥረት ነው ሲልም ኮንኖታል።

መንግሥት ከዚህ መሰል “ሕገ-ወጥ እስርና የተለያዩ ጫናዎችን ከማድረስ እንዲቆጠብ እና ባልደረቦቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጉባኤው አሳስቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኞችን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችንና የሰብዓዊ መብት ሠራተኞችን በማሰርና በማንገላታት በተደጋጋሚ ክስ ይቀርብበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዳይሬክተሯ ድርጊቱን “አሳፋሪ” ያሉት ሲሆን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአዲስ አበባ በመንግሥት እየተካሄደ ያለውን ነዋሪዎችን ከቀያቸው በግድ የማስነሳት ጭካኔን እንዳይጋለጥ በግልጽ እየከለከሉ እና ሌሎችም በሰብዓዊ መብት ሥራዎች ላይ እንዳይሳተፉ እያደረጉ ነው ሲሉም ከሰዋል።

አራቱ ሠራተኞች ከፖሊስ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሥራቸውን በመሥራት ክስ የቀረበባቸው መሆኑን የገለጸው አምነስቲ፣ ይህ ግን በኢትዮጵያ ሕግ ወንጀል አይደለም ብሏል።

ተሽከርካሪያቸውን ጭምር የያዘው ፖሊስ ግን ግለሰቦቹ ከሚሰሩበት ድርጅት የድጋፍ ደብዳቤ ሳይዙ ከቀያቸው የተነሱ ተጎጂዎችን ሲያነጋግሩ ነበር ብሏል።

ግለሰቦቹ አሁን ላይ በገናን ጉዳ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙም አምነስቲ ገልጿል።

እንደ አምነስቲ ከሆነ ግለሶቹ ታኅሳስ 28 ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ ግለሰቦቹ በእስር እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ በዋስ እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል።

ምንም እንኳን ፖሊስ ግለሰቦቹ ሰሩት ያሉትን ወንጀል እና በእስር እንዲቆዩ የሚያስችለውን ሕግ ያልጠቀሱ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ እስከ ዛሬ ድረስ በእስር እንዲቆዩ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣በክልሉ የሰብዓዊ መብት ምርመራዎችን እንዲያከናውን እንዳልተፈቀደለት ፖሊስ ነግሮኛል ብሏል።

ዳይሬክተሯ ታይግሪ ቻጉታህ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አራቱን የሰብዓዊ መብት ሠራተኞች በአስቸኴይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና ለሰሩት ሥራ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይገጥማቸው ማረጋገጫ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ጨምረውም ባለሥልጣናት የሰብዓዊ መብት ሠራተኞች ላይ የሚያደርሱትን ትንኮሳ እንዲያቆሙ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንዲሰሩ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።