“የቀረበብኝ ክስ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ ነው” መስከረም አበራ

መስከረም አበራ

የፎቶው ባለመብት, ethio-nikat

የምስሉ መግለጫ, መስከረም አበራ

ከሦስት ሳምንታት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ በዋስ የተለቀቀችው የ“ኢትዮ ንቃት” የማኅበራዊ ሚዲያ መስራች እና ባለቤት መስከረም አበራ የቀረበባት ክስ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ ነው አለች።

ለሁለተኛ ጊዜ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. በፖሊስ ተይዛ በእስር ላይ የቆየችው መስከረም አበራ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ዓ.ም. አንቀጽ 14ን በመተላለፍ በዐቃቤ ሕግ ክስ እንደተመሰረተባት ከጠበቆቿ መካከል አንዱ የሆኑት ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለችው መስከረም፣ የአሁኑ እስር ያልጠበቀችው እና “ዱብዕዳ” እንደሆነባት ለቢቢሲ ተናግራለች።

የጨቅላ ልጅ እናት የሆነችው መስከረም ክሱ በመጀመሪያ ላይ ከሽብር ጋር የተያያዘ እንደነበር፣ ቀጥሎ ደግሞ ከኮምፒውተር ጋር የተያያዘ ወንጀል መሆኑን እንደተነገራት ገልጻ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ጽሁፏን በድምጽ ያቀረበው ግለሰብ ከእሷ ጋር መከሰሱን መስማቷ የበለጠ ግራ አጋብቷታል።

ጠበቃዋ አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ በዝርዝር እንዳስረዱት ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ መስከረም በሥራዋ በሕዝብ ደኅንነት ላይ ወንጀል ለመፈጸም በማሰብ፤ ጥላቻን፣ አመጽን፣ ሁከትን እና ግጭትን በማሰብ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን በብሔር ለመከፋፈል እና አገር ለማፍረስ ማሰብ የሚል እንደሆነ አመለክተዋል።

መስከረም አበራ ግን “በኢትዮ ንቃት” የዩቲዩብ ቻናሏ አማካይነት የምትሰራው ሥራ በመረጃ ላይ በመመስረት የምትሰጠው ትንታኔ “በአቅሜ ለአገሬ የምችለውን ለማዋጣት” እንጂ የተጠቀሰውን ወንጀል ለመፈጸም አስባ እንዳልሆነ በመጥቀስ “ይህ ክስ ሃሳብን የመግለጽ መብትን ይጋፋል” በማለት ሃሳብን የመግለጽ መብት አደጋ ላይ መሆኑን ተናግራለች።

ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ እንዳሉት ዐቃቤ ሕግ ሐሙስ ታኅሣሥ 27/2015 ዓ.ም. ከ15 ገጽ በላይ የሆነውን ክስ ለችሎቱ ማቅረቡን፤ ነገር ግን ዝርዝር የክርክር ሃሳብ ለመስጠት ጊዜ ስለሚያስፈልጋቸው በዚህ ሂደት መካከል መስከረም አበራ በእስር እንዳትቆይ የዋስትና መብት እንዲፈቅድላት ጠይቀዋል።

በዚህም መሠረት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የልዩ ልዩ የወንጀል ችሎት ጥያቄውን ተቀብሎ የዐቃቤ ሕግን አስተያየት ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግም የዋስትና ጥያቄው ላይ ተቃውሞ እንደሌለው በመግለጽ መስከረም አበራ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ለመለቀቅ በቅታለች።

በመስከረም አበራ ላይ ከቀረበው ክስ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ተከሳሽ መኖሩን የጠቀሱት ጠበቃ ሰለሞን፣ በሌለበት በሁለተኛ ተከሳሽነት አቶ አመሃ ደገፋ የተባለ ግለሰብ የተጠቀሰ ሲሆን ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስና በቀጣይ ቀጠሮ ላይ እንዲቀርብ አዟል።

መስከረም አበራ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ከእሷ ጋር የተከሰሰው አመሃ ደገፋ የእሷን ጽሑፍ በድምጽ በማቅረቡ መከሰሱን ጠቅሳ፣ እሷም አብሯት መከሰሱን ያወቀችው ዛሬ መሆኑን እና ግለሰቡም ስለክሱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግራለች።

ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለች ከሁለት ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት የቀረበችው “ኢትዮ-ንቃት” በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኳ ላይ ፖለቲካዊ ትንታኔዎች እና ጠንካራ ትችቶችን በመሰንዘር የምትታወቀው መስከረም አበራ፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት 2014 ዓ.ም. ለእስር ተዳርጋ ነበር።

መስከረም በወቅቱ በተመሳሳይ ለሳምንታት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከቆየች በኋላ በፍርድ ቤት ውሳኔ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ነበር ከእስር የወጣችው።

መስከረም የጨቅላ ልጅ እናት በመሆኗ ከልጇ እና ከቤተሰቧ ከመለየቷ ውጪ ዛሬ ከመለቀቋ በፊት በእስር በቆየችበት ጊዜ ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠማትና አያያዙም “የሚያማርር” እንዳልሆ ጠቅሳ፣ ነገር ግን ከእናቷ እና ከባለቤቷ ውጪ ሌላ ሰው እንዲጠይቃት አለመፈቀዱን ለቢቢሲ ተናግራለች።

መስከረም አበራ ለ23 ቀናት ከቆየችበት እስር ቤት በዋስ ወጥታ ጉዳይዋን ከውጪ ሆና እንድትከታተል የወሰነው ፍርድ ቤት፣ ለቀጣይ ችሎት ጥር 15/2015 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኽኝ ተናግረዋል።