መስከረም አበራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለች

የፎቶው ባለመብት, social media
“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ መሥራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ ዛሬ ማክሰኞ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋሏን ባለቤቷ ለቢቢሲ ተናገረ።
መንግሥትን አጥብቃ በመተቸት የምትታወቀው መስከረም አበራ ባለቤት አቶ ፍጹም ገ/ሚካኤል ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሰዓት 10፡30 አካባቢ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አብረው ሳሉ ሲቪል እና የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች መጥተው መስከረምን ይዘው ሄደዋል።
መስከረም የግለሰቦቹን ማንነት ስትጠይቅ የፌደራል ፖሊስ አባላት መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መሥሪያ ቤት ይዘዋት እንደሚሄዱ ተናግረው በመኪና እንደወሰዷት ባለቤቷ ፍጹም ገ/ሚካኤል አስረድቷል።
ፍጹም እንደሚለው ባለቤቱ ታስራ ወደምትገኝበት ሜክሲኮ የፌደራል ወንጀል ምርመራ አቀንቶ መስከረምን ማግኘቱን እና በምን ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር እንደዋለች እንደማታውቅ ጨምሮ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ቢቢሲ መስከረም በምን ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር እንደዋለች ከፌደራል ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የፌደራል እና የክልል መንግሥታትን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጥብቃ በመተችት የምትታቀው መስከረም አበራ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ስትውል ይህ የመጀሪያዋ አይደለም።
ባለፈው ዓመት ግንቦት 2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ በ30ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መለቀቋን ባለቤቷ ፍጹም አስታውሷል።
በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ መምህርት የነበረችው መስከረም ግንቦት አጋማሽ 2014 ዓ.ም. ሕዝባዊ አመፅ በመቀስቀስ ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርባ ነበር።
ባለቤቷ ፍጹም እንዳለው መሰከረም የመምህርነት ሥራዋን በማቆም ሙሉ ትኩረቷ በሚዲያ ሥራ ላይ አደርጋ እንደምትገኝ ጨምሮ ለቢቢሲ ተናግሯል።












