ኢትዮጵያ፡ ‘የማይናገሩት’ እና ‘የማይነገርለት’ የተንሰራፋው የወጣቶች ጭንቀት

አንዲት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በብዙ ምክንያቶች ማንነቷ እንዲታወቅ አትፈልግም።

እኛም እንዳትታወቅ በሚል ‘ቅድስት’ በሚል ስም እንጠራታለን።

ቅድስት ዘንድሮ ነው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናዋን የወሰደችው።

ከቢቢሲ ጋር ዛሬ ያገናኛት ጉዳይ ግን የተከሰተው ከሁለት ዓመት በፊት ነው።

ገና አስረኛ ክፍል እያለች።

“አንድ እኛ ትምህርት ቤት ከሚማር ልጅ ጋር የዐይን ፍቅር ይዞኝ ነበር” ስትል ትጀምራለች።

አፍላ ፍቅር።

በጓደኞቿ ግፊት ፈራ ተባ እያለች ‘የልቤን’ ያለችውን ነገረችው።

ምላሹ ግን የልቧን አላደረሰውም።

አዘነች። ተከፋች።

የማዘን እና የመከፋቱ ጉዳይ መልከ ብዙ ነው።

“አንዳንዴ ለምን ለጓደኞቼ ነገርኳቸው? እላለሁ” ትላለች።

ጓደኞቿ እሷን ሲያዩ ርዕሰ ጉዳይ የሚሆነው የእሷ ‘የፍቅር ጥያቄ’ ሆኗል።

ጓደኞቿ እሱን ሲያዩም ርዕስ የሚሆነው አሁንም የእሷ ‘የፍቅር ጥያቄ’ ነው።

ጭንቀቱ ትምህርት ቤት ተወልዶ ቤት ድረስ ዘለቀ።

“ቤተሰቦቼ ስለጉዳዩ አያውቁም” ትላለች።

ቤተሰቦቿ የማያውቁትን ጉዳይ ግን የቤተሰቡ አባል አደረገችው።

ስታጠናም አልጋ ላይ ተጋድማም ስለ ‘ትምህርት ቤቱ ልጅ’ ብቻ ሆነ ሃሳቧ።

እንዳሁኑ አይሁን እንጂ ሌላም ሃሳብ ነበረባት።

በትምህርቷ ጥሩ የምትባል ናት። ቤተሰቦቿም ለትልቅ ደረጃ የሚጠብቋት።

በትምህርት ጥሩ ራመድ ካለ ቤተሰብም ነው የተገኘችው።

በተለይ አባት ዲግሪውን አንድ ሁለት ሦስት እያሉ ደራርበውታል።

ለዚህም ነው አባት የእኔን መንገድ ትከተላለች ብለው የሚኮሩባት ጭምር የሆነችው።

ይህ በቀጥታም ሆነ በዘወርዋራ ትምህርትሽ ላይ አተኩሪ የሚል ግፊ ነበረው።

ለእሷ ግን ሌላ የምታብሰለስለው ሌላ ምትጨነቅበት ጉዳይ ሆነባት።

የምትወደውን ልጅ ማጣቷን እና ቤተሰቦቿ በሚፈልጓት ደረጃ አለመራመዷ ያስጨንቋት ገቡ።

ቤትም ትምህርት ቤትም የሚያሳስቧት ነገሮች ሆኑ።

ከቤት ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤት ደግሞ ቤት ለምትለው ቅድስት ሌላ ማምለጫ መንገድ ጠፋ።

“ሌላ ሰው የሆንኩ ያህል ተሰማኝ። የሚያስደስተኝ ነገር አጣሁ። እንቅልፍ በዓይኔ አልዞር አለ። ሌላ ሰው ሆንኩኝ” ትላለች።

በዚህ ጊዜ ትንሽ እረፍት የሚሰጣት ‘የእኔ’ ከምትላቸው ጓደኞቿ ጋር መሆን ነው።

ይህ ደግሞ ሁሌም አይሳካም።

እሷ ብዙም እንድትወጣ አይፈቀድላትም። ጓደኞቿ ቤታቸው ሲሄዱ ደግሞ የልባቸውን ለማውራት አይመቻቸውም።

በዚህ ውጣ ውረድ ሳምንታት ከነፉ።

ቤተሰቦቿ ሳይሰሙ መፍትሔ ያመጡልኛል ያለቻቸውን መንገዶች አማተረች።

መፍትሔ የለም።

መጽሐፍትን አነበበች።

መፍትሔ የለም።

ዩቲዩብ ላይ ተጣደች።

አሁንም መፍትሔ የለም።

* * *

የመጨረሻው መፍትሔ ወደ ህክምና ማዕከል ለመሄድ ሆነ።

አንዲት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ጭንቀት. . .እየጨመረ ነው”

ይህም ግን ቀላል ውሳኔ አልነበረም።

ለቤተሰብ ሳይናገሩ ህክምና መሄድ ከባድ ነው።

ብዙ መዘዞችም አሉት።

ብዙ ጥያቄ ያስከትላል።

እሷ ደግሞ አንኳን ለብዙ ለአንድም ጥያቄ መልስ የላትም።

ያለቤተሰብ ሐኪም ዘንድ መሄድ የድጋፍ ማጣት ስሜት ይፈጥራል። ለተማሪ ደግሞ ሌላ ፈተና አለው - ገንዘብ አለማግኘት።

‘ቁጥጥር ለሚበዛባት’ ቅድስት ከትምህርት ቤት ቀርቶ ሐኪም ዘንድ መሔድ በራሱ ከባድ ነበር።

አውጥታ አውርዳ ግን አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰች። ለብቻዋ ወደ ህክምና መሔድ።

“እኔም የሚሰጠኝን [የኪስ ገንዘብ] አጠራቅሜ ጓደኞቼም ሰጥተውኝ ሐኪም ቤት ሄድኩኝ” ትላለች።

ሐኪሙ ጭንቀት እንዳለባት ነገራት።

አሁን ወደ አቶ ብርሃኑ ራቦ እናቅና። አቶ ብርሃኑ የሞሽን የማማከር እና የሥልጠና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

“በብዙ ፀሐፊዎች ወይም ፈላስፋዎች አረዳድ ውጥረት ወይም ጭንቀት ሰው አሁን ያለበት እና በመድረሻው መካከል ያለው ርቀት ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ በሚፈጠር ተስፋ ማጣት የሚከሰት ነው ይላሉ” ሲሉ ይገልጻሉ።

ቅድስት ስላሳለፈችበት የሕይወት መስመር ለአቶ ብርሃኑ ስናጫውታቸውም “ውጥረት ወይም ጭንቀት በተለይ ዕድሜያቸው 20 እና ከዚያ በታች የሆኑ ልጆች ዘንድ እየጨመረ ነው። ቤተሰብ፣ መምህራን እና ማኅበረሰቡ ሳያውቁ ስር እየሰደደ እየተሰቃዩበት ነው። ማንም ስለማይረዳቸውም በራሳቸው መንገድ መፍትሔ ለመፈለግ ይጥራሉ” ብለዋል።

“መንግሥት፣ ቤተሰብ፣ ፈጣሪ . . . እያለ ለምን?”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምክንያቱ ምን ይሆን ሲባሉ መልከ ብዙ መሆኑን ይጠቁማሉ ባለሙያው። አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ችግሮች ፍርሃት እንዲያድርባቸውና ተስፋ እንዲቆርጡ ያደርጋቸዋል።

“ጤና፣ ችግር፣ የሠላም እጦት ችግር አለ። የሰዎችን ሞት መስማት ኖርማል (የተለመደ) ሆኗል” የሚሉት አማካሪው አቶ ብርሃኑ፣ ስለዚህ ወጣቶች ተስፋ የማይታያቸው በጣም የሚጨነቁ እና ውጥረት ውስጥ የሚገቡ ሆነዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ማን ከጎኔ አለ ሳይባል ስለዘረኝነት፣ ስለሃይማኖት. . . ጦርነት ይወራል። ወጣቶችን እና ህጻናትና ሳያማክል መኖራቸውን እንኳን ከግምት ሳይገባ ይወራል። ትርፉ ልጆችን መጉዳት ነው ሲሉ አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ።

በተጨማሪ ደግሞ የቴክኖሎጂ በረከት የትዬ ለሌ ነው።

ከህጻን እስከ አዋቂ መዳፍ ላይ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም፣ ዩቲዩብ . . . በቀላሉ የሚገኝበት ዘመን ነው።

የሚታጨደው በረከት ግን መልካሙም ብቻ አይደለም። እንክርዳዱም ጥቂት አይደለም።

አቶ ብርሃኑ ሩብ ክፍለ ዘመን በማማከር እና በማሠልጠን አሳልፈዋል።

ዓመት ዓመትን ሲተካ በጭንቀት እና ድባቴ የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር መናሩን ይናገራሉ።

ምክንያቱን ለማወቅ ደግሞ አነስተኛ ጥናት አከናውነዋል።

“ዘመኑ ሰዎች የማይረኩበት። በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ነገሮች የፈጣሪን ህላዌ ራሱ የሚጠራጠሩበት፤ ‘ፈጣሪ እያለ ለምን ይሔ ሆነ?’ የሚል ሊመልሷቸው የማይችሏቸው ጥያቄዎች ውስጥ የመግባት ዕድል አለ።”

“ቤተሰብ፣ እናት እና አባት እያለኝ ለምን ይሔ ደረሰብኝ? ለምን ይሔ ሆነብኝ? መንግሥት እያለ ለምን ይሔ ሆነ?” እያሉ ከሚተማመኑበት ነገር እየራቁ ሲሄዱ መፍትሔ፣ ረዳት እና አቅም የማጣት ሁኔታ ይመጣል።

“በተስፋ ከመሞላት ወደ ተስፋ መቁረጥ ይሄዳሉ።”

በቀጠሮ ሕይወትን ከማጥፋት እስከ “ሚመላለሰው ጦርነት. . .”

መፍትሔ የሚሉት ደግሞ ከባህል፣ ከእምነት እና ከእሴት የወጡ ነገሮችን ማድረግ ነው። “በመቀጠል በራሳቸውም በሌላውም ላይ መጨከን ነው” ይላሉ።

በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ራሳቸውን እንደሚያጠፉ ተናግረው ራሳቸውን ያጠፉ መኖራቸውን አስታውሰው “ይህ አስደንጋጭ ነው” ሲሉ አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ።

“ሞትን የመሰለ ከባድ ነገር በቀጠሮ ወስነህ ስታደርገው ውጥረታችን እና ጭንቀታችን በሰው፣ በምድር እና በሰማይ ተስፋ መቁረጣችን ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ይገለጻል። ልጆችን ተሰናብቶ ወደ ሞት መሄድ ወደየት እየሄድን እንደሆነ ያሳያል” ሲሉ ያክላሉ።

“እንደተከታታይ ፊልም በላያችን ላይ የሚመላለሰው ጦርነት፣ አካላዊ እና ቁሳዊ ጉዳቱን እንጂ ሥነልቦናዊ አደጋው ታስቦ እየተሠራበት አይደለም” ይላሉ።

ይህም ልጆች ተስፋ እንዲቆርጡ፣ ነገን እንዳያስቡ፣ እንዳያልሙ፣ የሰውነት ክብርን እና ሰብዓዊነትን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል በሚል ይገልጻሉ።

“የሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ በኢኮኖሚው ላይ ተደምሮ የምንይዘው የምንጨብጠው አጥተናል” በማለት የእለት ከዕለት ሕይወት ጫናም የእራሱ አሉታዊ ውጤት አለው ይላሉ።

“የመኖር ትርጉም ሲያጣባቸው የማያውቁትን ዓለም መሞትን ወደ መምረጥ ይሄዳሉ” የሚሉት አቶ ብርሃኑ “ከዚህ አንጻር እንደባለሙያ የሚያሳስበን ትኩረት ማጣት ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ይህ ‘ጊዜ ቦንብ’ ነው የሚሉት አቶ ብርሃኑ ያውም ‘ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ’ ይላሉ።

ቤተሰብ በሙሉ ቴክኖሎጂ ላይ ተጥዶ ሰው አፍ ለአፍ የማይነጋገርበት ሁኔታ እያደገ ነው።

አንዲት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ልጆቻቸውን የማይሰሙ ወላጆች”

ሰው ችግሩን የሚነግረው ለሚሰማው ለሚያዳምጠው ነው።

ወላጆች የራሳቸውን ችግር ለማለፍ ወይም ዓላማቸውን ለማሳካት እንጂ ልጆችን ለመስማት ጊዜ የላቸውም።

“ወላጆች ልጆቻቸውን፣ መምህራን የተማሪዎቻቸው ችግር ከማዳመጥ የራሳቸውን ችግር ነው የሚያሰላስሉት። ‘እኔ ለመግባችሁ ስሯሯጥ’ በሚል የልጆቹን ችግር እንደምቾት እና ድሎት ነው የሚያዩት” ይላሉ አቶ ብርሃኑ።

ልጆቹ ችግራቸውን ያጠራቅሙና ከወላጆች። ከመመህራን እና ከማኅበረሰቡ ደብቀው በራሳቸው መንገድ ለመፍታት ይሞክራሉ።

ያውም “ጥሩ ባልሆነ፣ በማይመከር እና ችግሩን በሚያባበስ መልኩ ለመፍታት ይሯሯጣሉ።”

“ይህንን አድርገው ሲያቅታቸው ደግሞ ራሳቸውን ይጠላሉ፣ እንቅለፍ ያጣሉ። እያደረ ፍርሃት ውስጥ ይከታቸዋል። ሁሉም እያወቀበቸው መሆኑን ከፍተኛ እርምጃ ይወስዳሉ” ይላሉ።

የቅድስት ወላጆች ልጃቸው ያላትን ለውጥ መከታተል ነበረባቸው። ለእሷም ከባድ ቢሆንም ችግሩን ለቤተሰቦቿ ማሳወቅ የተሻለ ቀላል ያደርግላት ነበር።

“እነዲህ ዓይነት ነገር በብዛት ያጋጥማል። ከትንንሽ ልጆች ጀምሮ በማይታወቅ ድባቴ ውስጥ ያሉ አሉ” ይላሉ ባለሙያው።

ስለ ቅድስት ያጫወትናቸው አቶ ብርሃኑ እሳቸውም በርካታ ተመሳሳይ ታሪክ እንደሚያውቁ ይናገራሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱን አውግተውናል።

“አንድ በጣም ጎበዝ ወጣት ነበር። በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ነው። ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ችግሩን የሚሰማው ስለሌለ ይጨነቅ ጀመረ። ቤተሰቡ ለእሱ ያላቸው ግምት ትልቅ በመሆኑ፣ ትምህርቱን መከታታል አልቻለም። በኋላም ትምህርቱን አቋረጠ። ወላጆቹ ይህን ሁሉ አያውቁም።”

ነጻ አገልግሎትም የሚሰጡት አቶ ብርሃኑ ተማሪው ቢሯቸው ሲደርስ ፊታቸውን አላዞሩበትም።

“እና ተገቢውን ድጋፍ ሰጥተነው ወደ ትምህርቱ ተመልሶ ዓላማው እንዲያሳካ እገዛ አደረግንለት” ሲሉ ያስታውሳሉ።

“የሚዘገንን መረጃ የሚሰጡት ቲቪዎች እና ስልኮች”

“ብዙ ወላጅ ልጆቼ ጥሩ ናቸው። ጎበዝ እና ሥነ ምግባር ያላቸው ናቸው ይላሉ እንጂ ብዙ ወጣቶች በከፍተኛ ሁኔታ ድባቴ ውስጥ ነው ያሉት።”

“በአገራችን ብዙ ነገር ተስፋ የሚያስቀርጥ ይሆንባቸዋል። ወላጆች ትልልቅ ርዕሶችን ቤት እና መኪና ውስጥ ያወራሉ። ቲቪው እና ስልካቸው የሚዘገንን መረጃ ይሰጣል። ልጆቹ ትምህርት ቤት ሌላ፣ ቤት ሌላ ናቸው። ጓደኞቻው ጋርም ሌላ ናቸው። በዚህ ምክንያትም የተለያየ ስብዕና ያዳብራሉ” ይላሉ አቶ ብርሃኑ።

ለአቶ ብርሃኑ እነዚህን ከፍተኛ ችግሮች በአነስተኛ ድርጅቶች ብቻ መፍታት ከባድ ነው።

“ከቁስ እና ኢኮኖሚው በላይም በዘመቻ ከምንም በላይ መሠራት አለበት ብለን የምናምነው የሰው አዕምሮ ላይ ነው” ይላሉ።

ይህ ሕብረተሰቡ እና መንግሥት ኃላፊነት ነው።

ወጣቶች ደግሞ ሌላ ኃላፊነት አለባቸው።

“ወጣቶች እውቀት ላይ ትኩረት ያድረጉ። አካላዊ እንቅስቃሴ አለባቸው። ከዲጂታል ይልቅ መጽሐፎችን በእጅ ይዞ እያገላበጡ ማንበብ። በተቻለ መጠንም ከቴክኖሎጂ ጋር የሚቆዩበትን ጊዜ መቀነስ አለባቸው” ይላሉ አቶ ብርሃኑ።

በተጨማሪም በቀን ስንት ሰዓት ማየት እንዳለባቸው መለየት እና ከቻሉ በሳምንት አንድ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ከቴክኖሎጂ ውጪ መሆን ያስፈልጋል። ከተፈጥሮ ጋር መገናኘት፣ ስፖርት መስራት፣ በበጎ አድራጎት መሳተፍ እና ህይወታቸውን በተቻለ መጠን መንፈሳዊ ማድረግ እንደሚያስፈለግ ባለሙያው አጥብቀው ይመክራሉ።

“ዘመኑ ፈጣን ነው። ይህን ሊታደግ የሚችል ፈጣሪ እንዳላቸው በማየት ለሕይወታቸው ቅርጽ መስጠት። በሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎች እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል።

“ከረዥም ጊዜ በኋለ ጥሩ እንቅልፍ ተኛሁኝ”

በተለይ ደግሞ ወጣቶች የትምህርት፣ የሥራ እና ሌሎች መከወን ያለባቸው ነገሮች መብዛት ሳይሆን ለበርካቶች የጭንቀት ምንጭ የሚሆነው፣ እያንዳንዱን ሥራ በጊዜ አለመሥራት መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል።

ስለዚህ ወላጆች እና ልጆች ያላቸውን ጊዜ እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው መልመድ ይገባል የሚሉት አቶ ብርሃኑ “የሰዓት አስተዳርን ከቤት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።”

ወደተነሳንበት ታሪክ እንመለስ።

አሁን ቅድስት በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።

ህክምናዋን በደንብ ተከታትላለች።

“ሐኪም ቤት ደርሼ የተመለስኩ ቀን ነው የሆነ ነገር የቀለለኝ” ስትል ታስታውሳለች።

“ቤት የደረስኩት ፈገግ ብዬ ነበር። ከረዥም ጊዜ በኋለ ጥሩ እንቅልፍም ተኛሁኝ” ብላለች።

ሕክምናውም ቢሆን ግን መዘዝ ነበረው።

በተለይ ቤተሰብ ሳያውቅ መድኃኒት ደብቆ መዋጥ ፈተና ነው።

አንዴ ወስና የገባችበት በመሆኑ ግን ተወጣችው።

ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት በመዘጋጀት ላይ ትገኛለች።

ቤተሰቦቿ እንደሚጠብቋት በትምህርቷ መግፋት ትፈልጋለች።

ያውም አባቷ በሚፈልጉት የትምህርት ዘርፍ ነው መቀጠል የምትፈልገው።

አባት እና ልጅ በአንድ የትምህርት መስክ ሊጓዙ ነው።

አሁንም ግን ከስጋት ነጻ አይደለችም።

ጉዳዩን ለቤተሰቦቿ አለመንገሯ ያሳስባታል። ቢያውቁስ የሚል ስጋት አለባት።

ግን ከቀድሞው የተሻለ ጥንካሬ ስላላት ምንም ቢመጣ ከቤተሰቦቿ ጋር እንደምታልፈው ታምናለች።