ከድብታ መድኃኒቶች ውጤታማነት አንጻር እየተካሄዱ ያሉ ክርክሮች እና አማራጮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሐኪሞች ድብታ የሚመጣው ከኬሚካሎች ሚዛን መዛባት ነው ሲሉ ኖረዋል።
በአጭሩ ለማስቀመጥ፣ በአእምሮ ውስጥ ‘የደስታ ሆርሞን’ አለ። ሴሮቶኒን ይባላል።
የዚህ ኬሚካል መጠኑ አነስተኛ ሲሆን ከባድ ድባቴ ውስጥ እንዘፈቃለን።
ስለዚህ መጠኑን ለማስተካከል መድኃኒት እንወስዳለን።
በቅርብ ግን አዲስ ጥናት ወጣ። እንዲህ ብሎ ነገር የለም የሚል ነው የጥናቱ ድምዳሜ።
ይህ ነገር አሁን በስፋት እያነጋገረ ነው።
እርግጥ ነው ይህ ጥናት የድብታ መድኃኒቶች ጨርሶውኑ ውሸት ስለመሆናቸው አላረጋገጠም።
ነገር ግን ጥናቱ ያን አለማረጋገጡ ክርክሩን አላበረደውም።
ነገሩን ከሥር መሠረቱ እንድንረዳ የሳራን ታሪክ እንመልከት።

ሳራ በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለች ጭንቀት እንዳለባት ተነገራት። የደስታ ሆርሞኖቿ አነስተኛ እንደሆነ ተረዳች።
ቶሎ ቶሎ ድብታ ውስጥ ትዘፈቃለች።
ሐኪም ዘንድ ሄደች። እንክብሎች ተሰጧት።
ከማስጠንቀቂያ ጋር።
የስኳር ህሙማን ኢንሱሊን እንደሚወጉት ሁሉ አንቺም እኒህን እንክብሎች በሥነ ሥርዓት ውሰጂ ተባለች።
ጭንቅላትሽ ውስጥ የተዛባውን ሆርሞን የሚያስተካክልልሽ ብቸኛው ነገር ይህ መድኃኒት ነው ተብሎ ተነገራት።
እናቷ የስኳር ሕመምተኛ ነበሩ፤ ስለዚህ ሐኪሞች ምን እያሏት እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባትም።
ስለዚህ የሐኪሙን ምክር እንደ ዋዛ አልወሰደችውም።
ይሁንና መድኃኒቶቹ ከድብታ አላዳኗትም። አልፎ አልፎ ራሷን የማጥፋት ስሜት ውልብ ይልባታል።
እነዚህን መድኃኒቶች እንደ ስኳር ሕመምተኛ ያለምንም ወለም ዘለምታ ትውሰዳቸው የተባለው ነገር በኋላ ላይ ጥናቶች የሚደግፉት እንዳልሆነ ደረሰችበት።
ይህን ዜና ስትሰማ ነው፣ “በምታምናቸው ሰዎች የመካድ ያህል ነው” ያለችው።
አዲሱ ጥናት ምንድነው የሚለው?
ብዙ የሳይካትሪ አዋቂዎች አሁን አሁን የሴሮቶኒን መጠን ማነስ የድብታ ዋንኛ ምክንያት እንዳልሆነ ያውቁ እንደነበር ይፋ እያደረጉ ነው።
ይህ ማለት አሁን አዲስ የወጣው ጥናት ብዙም አዲስ ነገር እየነገረን አይደለም ማለት ነው።
ይሁንና ጥናቱ ከወጣ በኋላ በርካታ ሕዝብ እየተቀባበለው መሆኑ ነገሩ ለብዙዎች አዲስ ዜና እንደሆነባቸው የሚገልጽ ነው።
ይህ አዲስ የተቀሰቀሰ ውይይት አንዳንዶች ፀረ ድብታ መድኃኒቶች ጨርሶውኑ አይሠሩም ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ አድጓል።
ሐኪሞች ይህ ነገር አስፈርቷቸዋል። ሰዎች በድንገት እየወሰዱ ካሉት መድኃኒት ሲወጡ ሌላ ራሱን የቻለ ጣጣ ይዞ ይመጣል እያሉ ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብሔራዊ የጤና ድርጅት ይህ መድኃኒት ድንገት ከቆመ ዳፋው ብዙ ነው እያለ ነው።
ይህ ጥናት 17 አዳዲስ ጥናቶችን የፈተሸ ነው። በድምዳሜውም ድብታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ድብታ የተፈጠረባቸው በጭንቅላታቸው ውስጥ ያለው ሴሮቶኒን ሆርሞናቸው ዝቅተኛ ስለሆነ አይደለም ብሏል።
ዶክተር ማይክል ብሉምፊልድ ነገሩ በአጭሩ ሲያስቀምጡት እንዲህ ይላሉ፤ "ፓራሲታሞል ለራስ ምታት ጥሩ ነው፤ ነገር ግን አንዳችንም ራስ ምታት የሚመጣው ፓራስታሞል ባለመዋጥ ብለን አናምንም።"
ድብታም እንደዚያው ነው፤ መድኃኒቶቹ ያግዙ ይሆናል። ነገር ግን ድብታ የመጣው በደስታ ሆርሞኖች ማነስ አልነበረም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፀረ ድብታ መድኃኒቶች ይሠራሉ?
አሁን ጥያቄው አንድ ነው። ለመሆኑ ፀረ ድብታ እንክብሎች ይሠራሉ ወይስ እንዲሁ በከንቱ ነው ስንቅማቸው የኖርነው?
ጥናት እንዳረጋገጠው እነዚህ መድኃኒቶች ሠሩ ከተባለ ራሱ ልክ እንደ ሐሰተኛ መድኃኒቶች በእምነት ብቻ ነው።
ፕሌሰቦስ (placebos) የሚባሉት በመድኃኒት ቅርጽ የተሠሩ፣ ሰዎች እንድናለን ብለው እምነት እንዲያሳድሩ ብቻ ተደርገው የሚዘጋጁ በብዛት ለጥናት የሚሰናዱ ሐሰተኛ መድኃኒቶች ናቸው።
ይሁንና በዚህ የጥናት ውጤት ዙርያ ክርክሮች አሉ። እነዚህ የፀረ ድብታ መድኃኒቶች እጅግ ውጤታማ የሚሆኑላቸው ሰዎች አሉ። ይሁንና ሐኪሞች እነዚህን ሰዎች ለመለየት መላና ዘዴው የላቸውም።
ፕሮፌሰር ሊንዳ ጋስክ በሮያል ኮሌጅ ሳይካትሪስት ናቸው። “የፀረ ድብታ መድኃኒቶች ብዙ ሰዎች ወዲያውኑ ጥሩ ስሜት ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው” ይላሉ።
ፕሮፌሰር ጆናና ሞንክሪፍ በበኩላቸው በዚህ በሴሮቶኒን ጥናት ውስጥ የተሳተፉ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በመድኃኒት አምራቾች ዘንድ የሚደረጉ ብዙዎቹ ጥናቶች የይድረስ ይድረስ ናቸው። ውጤታቸውም በአጭር ጊዜ የሚለካ ነው። ስለዚህ ሰዎች ላይ በረዥም ጊዜ የሚያመጣውን ውጤት አያስረዱም።
ይህን ሲሉ ፀረ ድብታ መድኃኒት ወስደው ለጊዜው ጥሩ ስሜት ውስጥ የገቡት ታማሚዎች ምን ያህል ዘላቂ ሆነላቸው የሚለው አንኳር ነጥብ ነው።
ድብታን ሳይታከሙ መቆየት አደጋ አለው። ይሁንና የፀረ ድብታ መድኃኒት እየወሰዱ ያሉ ሰዎች የጎንዮሽ ጉዳቶችን በብዛት ያስተናግዳሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ዋንኞቹ ራስን የማጥፋት ሐሳብ ውልብ ማለት እና እንቅልፍ ማጣት ናቸው።
ሌሎች ደግሞ ስንፈተ ወሲብ ይገጥማቸዋል።
ይህን ጥናት ተከትሎ ታዲያ የዩኬ ሐኪሞች መድኃኒቶቹን ከማዘዛቸው በፊት፣ ጥሞና፣ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ ሜዲቴሽን እንዲሞክሩ እየተበረታቱ ነው።
ዞሮ ዞሮ የሐኪሞች ምክር አንድ ነው። ፀረ ድብታ መድኃኒቶች ቢያንስ ለጊዜው የተሻለ ስሜት ይሰጣሉ። ዘላቂ ግን አይደሉም።
ክርክሩ ግን ቀጥሏል። ድብታ እኛ ለአካባቢያችን የምንሰጠው ምላሽ ይሆን? በዘረ መል የሚወረስ ይሆን? ወይስ እንደሚባለው ጭንቅላታችን ውስጥ የሆርሞን መዛባት የፈጠረው?
ጥናቱ ቀጥሏል።
ግን አሁንም ሁሉም የሚስማሙት ከባለሙያ ጋር መማከር እና እነሱ የሚያስቀምጡትን የመፍትሄ ሃሳብ ሳያስተጓጉሉ ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ነው።












