በርካታ አገራትን ያለ ቪዛ ማሻገር የሚያስችሉ ፓስፖርቶች ያሏቸው አገራት ይፋ ሆኑ

ፓስፖርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሄንሌይ ኤንድ ፓርትነርስ የተሰኘው ተቋም የ2023 ‘ጠንካራ’ እና ‘ደካማ’ ያላቸውን ፓስፖርቶች ይፋ አደረገ።

ተቋሙ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሪፖርቱ የጃፓናውያን ፓስፖርት ያለ ቪዛ በርካታ ድንበሮችን በማሻገር የዓለማችን ቁጥር አንድ ‘ጠንካራው’ ፓስፖርት በመሆን ቀጥሏል ብሏል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ደካማ ከተባሉት ፓስፖርቶች የአፍጋኒስታን፣ ኢራቅ እና ሶሪያ የመጨረሻ ደረጃን ይዟል።

ሄንሌይ ኤንድ ፓርትነርስ የፓስፖርት ደረጃን የሚያወጣው የዓለም አቀፉን የአየር ትራንስፖርት ማኅበር አሃዞችን በመጠቀም ሲሆን የጃፓንን ፓስፖርት የያዙ ተጓዦች ወደ 193 አገራትና ግዛቶች ያለ ቪዛ መጓዝ ይችላሉ፣ አልያም ቪዛ በመዳረሻቸው ያገኛሉ ብሏል።

ከጃፓን በመቀጠል ሲንጋፖር እና ደቡብ ኮሪያ በ192 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሄንሌይ የፓስፖርቶችን ጥንካሬ የሚለካው፤ ተጓዦች በያዙት ፓስፖርት ምክንያት ቪዛ ቀድሞ ሳያስፈልጋቸው ወደ ስንት አገራት መጓዝ ይችላሉ የሚለውን በማጤን ነው።

በሄንሌይ ሪፖርት ላይ ቀድሞ ቪዛ አለማስፈለግ ማለት ወደ መዳረሻ ለመጓዝ ቪዛ አለመጠየቅ አልያም በመዳረሻ ቪዛ የማግኘት መብት ማለት ነው።

ተቋሙ የፓስፖርት ደረጃን የሚያወጣው ያለ ቪዛ ለሚደረግ የጉዞ መዳረሻ አንድ ነጥብ በመስጠት ነው።

በዚህ የደረጃ ሰንጠረዥ የኢትዮጵያ ፖስፖርት ከ109 ፓስፖርቶች ጋር ተነጻጽሮ በ46 ነጥብ 97ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።ይህ ማለት የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዙ ተጓዦች ቀድሞ ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ 46 መዳረሻዎች መጓዝ ይችላሉ ማለት ነው።

ሄንሌይ የ2022 ሦስተኛው ሩብ ዓመት የፓስፖርት ደረጃዎችን ይፋ ሲያደርግ የጃፓን ፓስፖርትን ቀዳሚ አድርጎ፤ የሲንጋፖር እና ደቡብ ኮሪያ በእኩል ነጥብ የዓለማችን ሁለተኛው ጠንካራ ፓስፖርት ደረጃን ሰጥቶ ነበር።

ጀርመን እና ስፔን በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ነበር። በ2023 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የፓስፖርት ደረጃ ላይ እስከ 3ኛ ያለው ደረጃ ለውጥ አልታየበትም።

የፊንላንድ፣ ጣሊያን እና ላክሰምበርግ ፓስፖርትን የያዙ ተጓዦች ወደ 189 መዳረሻዎች በመጓዝ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ እና ሰዊድን ፓስፖርት ደግሞ በ183 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በፓስፖርት ጥንካሬ የዓለም የመጨረሻው ደረጃ ላይ የተቀመጡት 10 አገራት ደግሞ ሊቢያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኔፓል፣ የፍልስጤም ግዛት፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ ፓኪስታን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ናቸው።

የኢትዮጵያ ፓስፖርት

የፓስፖርት ጥንካሬ የሚወሰነው በምንድን ነው?

የዓለም ባንክ እንደሚለው ከሆነ የአንድ አገርን የፓስፖርት ጥንካሬ ከሚወስኑ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ዜጎች የሚያገኙ የገንዘብ መጠን ነው።

ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው አገራት ከደሃ አገራት በተሻለ ወደ በርካታ አገራት ቪዛ ቀድሞ ማግኘት ሳይጠበቅባቸው መጓዝ ይችላሉ።

ከነፍስ ወከፍ ገቢ በተጨማሪ የአንድ የአገር ሁለንተናዊ ሰላም ከአገሪቱ የፓስፖርት ጥንካሬ ጋር በቀጥታ ይገናኛል።

በአንድ አገር የሽብር ጥቃቶች እና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች የበረከቱ ከሆነ እንዲሁም በተደራጁ ቡድኖች የሚፈጸሙ ወንጀሎች ካሉ የዚያች አገር ዜጎች ዓለም አቀፍ ጉዟቸው የተገደበ ይሆናል።

ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የሌላቸው እና ከፍተኛ ተፈናቃይ ያለባቸው አገራት ዜጎችም በተመሳሳይ ቪዛ የሚጠየቁባቸው መዳረሻዎች ከፍተኛ እንዲሆኑ አድርጓል።

ለማሳያም ምጣኔ ሃብታቸው የደቀቀባቸው፣ ማዕከላዊ መንግሥታቸው የተዳከመባቸው አልያም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የበዙባቸው እንደ የመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ያሉ አገራትን ፓስፖርት የያዙ ዜጎች በብዙ መዳረሻዎች ቪዛ ይጠየቃሉ።