የ9 ዓመቷ ልጅ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዕድሜ ያለው የግዙፍ ዓሣ ነባሪ ቅሪት አገኘች

በፈረንጆች አዲስ ዓመት ይቺ ሕጻን ቅሪት እንደምታገኝ እርግጠኛ ነበረች

የፎቶው ባለመብት, ALICIA SAMPSON

የምስሉ መግለጫ, በፈረንጆች አዲስ ዓመት ይቺ ሕጻን ቅሪት እንደምታገኝ እርግጠኛ ነበረች

በአሜሪካ ሞሊ ሳምሰን የምትባል የ9 ዓመት አዳጊ ባለፈው ሳምንት የፈረንጆች አዲስ ዓመት ቤተሰብ ጥየቃ ወደ ሜሪላንድ ግዛት ሄዳ ነበር።

ባሕር ዳርቻ እየሄደች ቅሪት መሰብሰብ የምትወደው ይቺ አዳጊ ለእናቷ ሁልጊዜም የድሮ ቅርስ እንደምታገኝ ትነግራት ነበር። 

ሕልሟንም አሳክታለች።

በካልቨርት የባሕር ዳርቻ የባሕር ውሃ ውስጥ ጠልቃ ያን ዕለት ጎርጉራ ያወጣችው ቅሪት ግዙፍ የባሕር እንሰሳ የሆነው ሻርክ ጥርስ ሆነ።

ይህ ኦቶደስ (Otodus) የተሰኘው በግዝፈቱ ወደር የማይገኝለት የባሕር እንሰሳ ዝርያ ከምድረ ገጽ ከጠፋ 3 ሚሊዮን 500ሺህ ዓመት አልፎታል።

ወደ ላይ ብቻ 20 ሜትር ይረዝም ነበር የሚባለው ይህ ሻርክ በምድር ላይ ከኖሩ የዓሣ ዝርያዎች ሁሉ በግዝፈቱ ተወዳዳሪ ኖሮት አያውቅም።

አዳጊዋ ሞሊ ያገኘችው የዚህ ግዙፍ አሳ ነባሪ ጥርስ የራሷን መዳፍ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ቁመቱ ሲለካ 12.5 ሴንቲ ሜትር ርዝማኔ አለው።

ይህን ዜና ለዓለም ይፋ ያደረገችው እናቷ አሊቺያ ሳምሰን በክስተቱ መደነቋን በፌስቡክ ገጽ ላይ ጽፋለች።

ከዚህ የበለጠ አስደናቂ የሆነው ደግሞ እናቷ እንደሚሉት ሞሊና እህቷ ናታሊ ወደ ባሕር የሄዱት ጥንታቂ ቅሪት እናገኛለን በሚል ተነሳሽነትና እርግጠኝነት መሆኑ ነው።

ለዚህም እንዲሆናቸው ፕሮፌሽናል ቅርስ ቆፋሪዎች የሚለብሷቸውን ልብሶች አጥልቀው ነበር።

ለአዲስ ዓመት ስጦታ የተሰጧቸውን እነዚህን የቅርስ ፈላጊ ባለሙያዎች የሚለብሷቸውን አልባሳት ካጠለቁ በኋላ፤ ቁርስ በልተው ያቀኑት ወደ ካልቨርት ባሕር ዳርቻ ነበር።

እናታቸው ለቢቢሲ የአሜሪካን አጋር ሲቢኤስ እንተናገሩት “ልጄ ወደ ባሕር ዳርቻው ከደረሰች በኋላ በከፊል ጠልቃ በመግባት ተአምር የሚመስል ነገር ይዛ ወጥታለች።”

እናት ጨምረው እንዳሉት ባለቤታቸው በዚያ አካባቢ ከልጅነት ጀምሮ ቅርስ ሲፈልግ የኖሩ ሲሆን ተሳክቶላቸው ግን አያውቁም።

ልጃቸው ቅሪቱን ካገኘች በኋላ አብረው ወደ ካልቨርት የባሕር ሙዝየም የወሰዱት ሲሆን የሙዝየሙ የባሕር ዓሣዎች ጥናት ክፍል ቅሪቱ እጅግ ጥንታዊና ከሦስት ሚሊዮን ዓመታት በፊት የኖረ ሻርክ ጥርስ እንደሆነ አረጋግጦላቸዋል።