ሰዋሰው፡ የአዲሱ ዘመን የኢትዮጵያ ሙዚቃ መድረክ

ሰዋስው መልቲ ሚዲያ

የፎቶው ባለመብት, Sewasew

ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ አፍቃሪዎች ካሴት ገዝተው፣ ሲዲ ሸምተው ሙዚቃ ማድመጥ ካቆሙ ቆይተዋል።

አሳታሚዎች እና አከፋፋዮችም ቢሆኑ ከገበያው ተገፍተው ወጥተዋል።

በዚህ የተነሳም ባለሙያውም እንደ ልቡ እና እንደፍላጎቱ የፈጠራ ሥራውን ለአድማጭ ለማቅረብ ሳይችል ቀርቷል።

በእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ ሥራውን ያጠናቀቀ ባለሙያም ‘ለታዳሚያን እንዴት ይደርስልኛል?’ የሚል ራስ ምታት ይጠብቀዋል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ እንደ መፍትሔ የተገኘው አማራጭ የማኅበራዊ ሚዲያው መድረክ ዩቲዩብ ነው።

ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ የተለያዩ የበይነ መረብ ሙዚቃ ማቅረቢያ (ኦንላየን ስትሪሚንግ) አገልግሎቶች ላይ ሙዚቃቸውን ማስቀመጥ የቻሉ ባለሙያዎች አሉ።

ይህ ግን ከሰፊው የአገር ውስጥ አድናቂያቸው ጋር አራርቋቸው ቆይቷል።

በዚህ መካከል መፍትሔ እሆናለሁ ብሎ ሰዋሰው የተሰኘው የበይነ መረብ የሙዚቃ መድረክ በቅርቡ ዘርፉን ተቀላቅሏል።

በሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ላይ ሥራቸውን ለማስደመጥ ፊርማቸውን ካኖሩ ድምጻውያን መካከል ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ፀደንያ ገብረማርቆስ፣ አብነት አጎናፍር ይጠቀሳሉ።

በቅርቡም በዚሁ መተግበሪያ አማካይነት የአስቴር አወቀ የሙዚቃ አልበም ለአድምጮች እንደሚደርስ ተነግሯል።

ድምጻዊ ግርማ ተፈራ ካሳ፣ ሔኖክ አበበም በሰዋሰው በኩል ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።

ድምጻዊ አብነት አጎናፍር ከሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር በተፈራረመበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, AbateKoraImage

“በአንድ ወር ስድስት የሙዚቃ አልበም”

አቶ ሐብቱ ነጋሽ በሰዋሰው መልቲ ሚዲያ የሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ናቸው።

እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ባለሙያዎችም ሥራዎቻቸውን በሰዋሰው መተግበሪያ በኩል ለመልቀቅ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በቅርቡም አብነት አጎናፍር በሰዋሰው ከሚሚደመጡት ሥራዎች መካከል አንዱ ነው።

ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በዓመት አንድ ወይንም ሁለት የሙዚቃ ሙሉ አልበምን ብቻ ሲያስተናግድ ለኖረው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ይህ አዲስ ትንሳኤ ይመስላል።

አሁን በየተወሰነ ጊዜ ሙሉ አልበሞችን ከድምጻውያን ማግኘት እንደሚቻል አቶ ሐብቱ ያስረዳሉ።

ሰዋሰው በወር ውስጥ ስድስት የሙዚቃ አልበሞችን በመተግበሪያው ላይ ለማስደመጥ አቅዶ እየሰራ ነው።

በየሳምንቱ ቢያንስ አንድ ሙሉ እና ግምሽ አልበም (ኢፒ) እንደሚያወጡም አቶ ሐብቱ አክለው ገልጸዋል።

ሰዋሰው “ፈጠራን የመሸለም” ዓላማ ነው ያለው ያሉት አቶ ሐብቱ፣ በሙዚቃ ውስጥ ላሉ የፈጠራ ባለሙያዎች አድናቆት እና ክብር ባላቸው ግለሰቦች መቋቋሙን ይገልጻሉ።

“በትንሹ አንድ ሚሊዮን እየከፈልን ነው”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሙዚቃ አቀናባሪው እና የዜማና ግጥም ደራሲው ያምሉ ሞላ ከሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር ውል ካሰሩ አቀናባሪዎች እና ፕሮዲውሰሮች መካከል አንዱ ነው።

ያምሉ ከሰዋሰው ጋር የተፈራረመበትን ምክንያት ሲያስረዳ በቀዳሚነት ያነሳው “የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን በሁለት እግሩ ከማቆም አንጻር ትልቅ እርምጃ” ስለመሆኑ ነው።

ለያምሉ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው የኪነጥበብ ባለሙያው የገንዘብ ተጠቃሚነት ነው።

ሰዋሰው ለሙዚቃ ባለሙያው ቅድመ ክፍያ በመክፈል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ያምሉ ይናገራል።

አቶ ሐብቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ “ዩቲዩብ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ” ነበር በማለት፣ ይህም በአገር ግንባታ ላይ ከፍ ያለ ድርሻ ሊጫወት የሚችለውን ዘርፍ “ባለቤት አልባ” አድርጎታል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ የስትሪሚንግ አገልግሎት አለመኖሩ፣ ለሥራቸው ተገቢውን ክፍያ ባለማግኘታቸው ምክንያት ከሙያቸው እየሸሹ የነበሩ ሙዚቀኞችን ታሳቢ በማድረግ ወደ ሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ።

በዚህ ሁሉ ተግዳሮት ውስጥ ሆነው ሥራቸውን ማቅረብ የቻሉ ባለሙያዎችም ቢሆኑ፣ የፈጠራ አቅማቸውን ልክ የሚያሳይ ሳይሆን ገበያው የሚፈልገውን ብቻ ለማቅረብ መገደዳቸውን አቶ ሐብቱ ይጠቅሳሉ።

የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ግጥም እና ዜማ ደራሲ የሆነው ያምሉ ሞላ ስለ መተግበሪያው ሲናገር፣ በቀላሉ በስልክ አማካኝነት አድማጮች ጋር ለመድረስ የሚያስችል ነው ይላል።

አክሎም የሙዚቃ ባለሙያዎችም ሥራቸውን ያለምንም ውጣ ውረድ በመተግበሪያው አማካኝነት ለአድናቂዎቻቸው ማድረስ መቻላቸው እና ውጣ ውረድን ማቅለሉን ይናገራል።

ሰዋሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጻውያንን ለማግኘት በቅድሚያ ከአቀናባሪዎች ጋር ነው ግንኙነቱን የመሠረተው።

ይህም የሆነበት ምክንያት እጃቸው ላይ የማን ሥራ እንዳለ ለማወቅ እና በቀላሉ ወደ ድምጻውያኑ ለመድረስ በማለም ነው።

አቶ ስብሐቱ እንደሚሉት ሰዋሰው የሙዚቃ ባለሙያዎች በልፋታቸው መጠን ተከፋይ እንዲሆኑ ለማድረግ አጥብቆ ይሰራል።

እስካሁንም ለጀማሪ ድምጻውያን “የሮያሊቲ ቅድመ ክፍያ” በሚል በትንሹ አንድ ሚሊዮን ብር እየከፈሉ መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰዋሰው በእርግጥ ለጀማሪ ይህንን ያህል ከከፈለ አንደ አስቴር አወቀ ላሉ ጎምቱ ድምጻውያን ምን ያህል ሊከፍል ይችላል? በማለት ከቢቢሲ ለቀረበው ጥያቄ ግን “እርሱ ምስጢራዊ (ኮንፊደንሺያል) ነው” ሲሉ መልሰዋል።

ነገር ግን ከፍተኛ ገብዘብ መክፈላቸውን አልሸሸጉም።

ለጀማሪ ድምጻውያን የሚከፍሉት የሮያሊቲ ቅድመ ክፍያ በሁለት ዓመት ውስጥ ሊገኝ ይችላል ተብሎ የተሰላ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ያለውን ክፍያ ግን የኢትዮጵያ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት በሥራው ላይ ለተሳተፉ ሁሉም የሙዚቃ ባለሙያዎች እንዲያገኙ እንደሚደረግ ያስረዳሉ።

ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ከእናት ባንክ ጋር የሚሰራ መሆኑን በማንሳት የፋይናንስ ተግዳሮት እንደማይገጥማቸውም ገልፀዋል።

ሰዋስው መልቲ ሚዲያ

የፎቶው ባለመብት, sewasew

አድማጮች ምን ያህል ይከፍላሉ?

ሰዋሰው በሙዚቃው ውስጥ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት በአጠቃላይ በይፋ መመስረቱን ያሳወቀው በቅርቡ ቢሆንም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን በርካታ የምሥረታ ሂደቶችን ማለፉን ይገልጻል።

ድምጻውያን፣ የግጥም እና ዜማ ደራሲያን፣ ፕሮዲውሰሮች እና የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋቾች በተለያየ ደረጃ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ዘርፉ ለዓመታት ያለበትን ችግር በሚገባ በማጥናት መመስረቱንም አቶ ሐብቱ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ገልጸዋል።

ሥራዎቻቸውን በሰዋሰው መልቲ ሚዲያ መተግበሪያ ላይ ለማስቀመጥ የተስማሙ ባለሙያዎች ከድርጅቱ ጋር ተፈራርመዋል።

200 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ መነሻ ካፒታል የተመሰረተው ሰዋሰው ያለቁ ሥራዎችን ከመግዛት ባሻገር፣ እንደ ሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያም አዳዲስ ሥራዎችንም ፕሮዲውስ አድርጎ ያሳትማል።

ድርጅቱ እስካሁንም ከ100 በላይ የሙዚቃ ባለሙያዎችን ማስፈረም መቻሉን ይናገራል።

ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ወደ ሥራ ከገባ ገና ሁለት ወር ያህል ዕድሜ ቢኖረውም፣ በአገር ውስጥ እና በባሕር ማዶ ከሚገኙ አድማጮች ወደ 100 ሺህ ዳውንሎዶችን ማግኘት መቻሉን አቶ ሐብቱ ይናገራሉ።

በቀጣይ ሁለት እና ሦስት ወራት ደግሞ ከ500 ሺህ በላይ ዳውንሎዶች ይደረጋሉ ብለው እንደሚጠብቁም አክለው ተናግረዋል።

መተግበሪያው ለኢትዮጵያውያን የኪነጥበብ ባለሙያዎች የመጣ ነው የሚሉት አቶ ሐብቱ፣ አሁን ከተቀበሏቸው ባለሙያዎች በተጨማሪ በተለያየ ቋንቋ የሚጫወቱ ባለሙያዎችን ለማስፈረምም እየሰሩ ይገኛሉ።

ሰዋሰው ሥራቸውን ጨርሰው የመጡ ባለሙያዎችን ሙዚቃ ከመግዛት ባሻገር ራሱ ፕሮዲውስ የሚያደርግላቸው ሙዚቀኞችም እንደሚኖሩ አቶ ሐብቱ ይናገራሉ።

መተግበሪያው በመላው ዓለም እንደሚሰራ እና ክፍያውንም በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በተለያዩ አማራጮች ለመክፈል ይቻላል።

ሰዋሰውን ከፍለው የሚጠቀሙ እንደሚኖሩ ሁሉ በነጻ መስማት እንደሚቻልም አቶ ስብሐቱ ይናገራሉ።

በነጻ መስማት የሚቻለው ግን የተወሰኑ ሙዚቃዎችን ብቻ ሲሆን፣ የሚከፍሉ ደግሞ የመረጧቸውን ሙዚቃዎች ማስቀመጥ (ሴቭ) ማድረግ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

ከፍለው የሚጠቀሙ አድምጮች ሙዚቃዎችን ሴቭ ከማድረግ ባሻገር የራሳቸውን ፕሌይሊስት (የሙዚቃ ዝርዝር) ማደራጀት ይችላሉ።

አንድ ተጠቃሚ በወር 90 ብር ከፍሎ ያልተገደቡ የሙዚቃ አማራጮችን ማግኘት እና ማድመጥ ይችላል።

በቀን ለመክፈል ለሚፈልግ አምስት ብር፣ በሳምንት 25 ብር በዓመት ደግሞ 900 ብር ከፍሎ የሚፈልጋቸውን ሙዚቃዎች ማድመጥ ይችላል።

መክፈል ያልቻሉ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች ግን ውስን ሙዚቃዎችን ብቻ በነጻ ማድምጥ እንደሚችሉ አቶ ሐብቱ ያስረዳሉ።